Saturday, 12 December 2015 11:04

ለኢቢሲ 50ኛ ዓመት በዓል የተመደበው 9 ሚሊየን ብር ተቀነሰ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(12 votes)

ፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ ጉዳዩ እኔ ጋ አልደረሰም ብሏል

    ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) 50ኛ ዓመት በዓል ማድመቂያ የተመደበው 9 ሚሊዮን ብር፤ ሰሞኑን በትችት ሲያወዛግብ የሰነበተ ሲሆን፤ ገንዘቡ ወደ 3 ሚሊዮን ብር መቀነሱ ታወቀ፡፡
ከኢቢሲ ጋር የ9 ሚ. ብር ውል የተፈራረመው የአቶ ሰራዊት ፍቅሬ ድርጅት (“ሰራዊት መልቲሚዲያ”፤ “የበዓሉን ዝግጅቶች እንዳይሰራ በፀረ ሙስና ታግዷል” የሚሉ መረጃዎች ተሰራጭቷል፡፡ መረጃውን ለማጣራት አዲስ አድማስ ላቀረበው ጥያቄ፤ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ “ጉዳዩ እኔ ጋ አልደረሰም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
“ሰራዊት መልቲሚዲያ”፣ የበዓሉን ዝግጅቶች እንዳይሰራ ባይታገድም፤ የዝግጅቶቹ ብዛትና የገንዘቡ መጠን ተቀንሶበታል፡፡ ምንጮች እንደገለፁት፤ ከረሀቡ አደጋ ጋር በተያያዘ ለበዓል ማድመቂያ ተብሎ በየጊዜው የሚወጣ ገንዘብ ላይ የሚሰነዘሩ ጠንካራ ትችቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፤ ኢቢሲ ወጪውን እንዲቀንስ አስገድደውታል፡፡
 ”ኢቢሲ በዓሉን ለማክበር ባወጣው ጨረታ ላይ እንድንሳተፍ በደብዳቤ ስለደረሰን ነው የመወዳደሪያ ሃሳብ ያቀረብነው ያሉ አቶ ሰራዊት ፍቅሬ፤ ተቀባይነት አግኝተን ሰኔ ወር ከኢቢሲ ጋር ውል ተፈራርመናል ብለዋል፡፡
“ታግዷል የሚል ወሬ እኔም ሰምቻለሁ፤ ግን የታገደ ነገር የለም” ብለዋል አቶ ሰራዊት፡፡ ሆኖም የተለወጠ ነገር መኖሩን ገልፀዋል፡፡
“በቅርቡ ኢቢሲ ውሉን እንድናሻሽል ጠይቆናል” ያሉት አቶ ሰራዊት፤ የማጠቃለያ ድግሶችና መሰል ዝግጅቶች፤ በተለያዩ ምክንያቶች አስፈላጊ ሆነው ባለመገኘታቸው ከውሉ ላይ ተቀንሰዋል ብለዋል፡፡ ማስታወቂያዎችን ራሱ ኢቢሲ ሊሰራቸው እንደወሰነ አቶ ሰራዊት ገልፀው፤ አሁን እኛ የምናዘጋጀው ኤግዚቢሽኑን እንዲሁም ለስጦታ ከውጪ የታዘዙን ነገሮች ማፋጠንና መሰል ስራዎችን ነው፤ ወጪውም ከ9 ሚሊየን ብር ወደ 2.9 ሚሊዮን ብር ተቀንሷል ብለዋል፡፡

Read 6472 times