Saturday, 05 December 2015 09:35

ህንድ የክፍለ ዘመኑ ከፍተኛው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ተመታች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

         ህንድ ባለፉት ከ100 በላይ አመታት ከተመዘገቡት የዝናብ መጠኖች ከፍተኛው የተባለውን ሃይለኛ ዝናብ ባለፈው ረቡዕ በደቡባዊ ክፍሏ ያስተናገደች ሲሆን ዝናቡ ባስከተለው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ክፉኛ መመታቷን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ታሚል ናዱ በተባለው የአገሪቱ ግዛት የዘነበው ሃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ማፈናቀሉን የጠቆመው ዘገባው፤ የግዛቱ መዲና በሆነችው ቼናይ፣ ፋብሪካዎች መዘጋታቸውንና አውሮፕላን ማረፊያውም ስራ ማቋረጡን ገልጧል። በአካባቢው ወሩን ሙሉ ይዘንባል ተብሎ ከሚጠበቀው አማካይ የዝናብ መጠን በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ዝናብ በ24 ሰዓታት ውስጥ መዝነቡንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
በህንድ አራተኛዋ ትልቅ ከተማ የሆነችው ቼናይ፣ ከአገሪቱ ዋነኛ የመኪና አምራችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከላት አንዷ እንደሆነች ዘገባው ጠቁሞ ከተማዋ ጎርፉ ባስከተለው የመብራት መቋረጥ እንቅስቃሴዋ ሙሉ ለሙሉ መገታቱን አስረድቷል። የጎርፍ አደጋው ያስከተለውን ጥፋት ለማከምና ተረጂዎችን ለማቋቋም አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ግብረ ሃይል ተቋሙሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡

Read 2616 times