Saturday, 05 December 2015 09:34

በአፍሪካ ከፍተኛው ሙስና የሚፈጸመው በባለጸጎች ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ፖሊሶችና የመንግስት ባለስልጣናት ይከተላሉ
                     - በአመቱ ከ75 ሚ በላይ የ28 አገራት ዜጎች በሙስና ገንዘብ ከፍለዋል
    በአፍሪካ በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በ2015 በሙስና ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዙት፣ በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ባለጸጎችና የኩባንያ ስራ አስፈጻሚዎች መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጣው አመታዊ የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ በአህጉሪቱ ከባለጸጎች በመቀጠል በሙስና ሁለተኛውንና ሶስተኛውን ደረጃ የሚይዙት የፖሊስ መኮንኖችና የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው፡፡
በ28 የአፍሪካ አገራት ላይ በተሰራው በዚህ ጥናት፣ ከ43 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ቃለመጠይቅ እንደተደረገላቸው የጠቆመው ዘገባው፤በዚህም ሙስና በአህጉሪቱ ክፉኛ መስፋፋቱንና በአመቱ ከ75 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን ከፖሊስ ወይም ከፍርድ ቤት ቅጣት ለመዳንና መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉላቸው ለማስቻል፣ በሙስና መልክ ገንዘብ እንደከፈሉ ተደርሶበታል ብሏል፡፡
ጥናቱ ከተሰራባቸው የአፍሪካ አገራት በአመቱ የከፋው ሙስና የተመዘገበው በላይቤሪያ ሲሆን፣ ካሜሩን፣ ናይጀሪያና ሴራሊዮን ይከተላሉ ተብሏል። ከምስራቅ አፍሪካ አገራትም ኡጋንዳና ኬንያ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ተነግሯል፡፡
በላይቤሪያ ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው የአገሪቱ ዜጎች መካከል 69 በመቶ የሚሆኑት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲሉ ለስራ ሃላፊዎች ገንዘብ በሙስና መልክ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ በቦስትዋና እና በሞሪሺየስ 1 በመቶ ያህሉ ሰዎች ብቻ ሙስና እንደሰጡ የገለጸው ዘገባው፤በጥናቱ ከተዳሰሱ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አነስተኛውን ሙስና ሰርተው የተገኙት የሃይማኖት መሪዎች መሆናቸውን ገልጧል፡፡ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ድህነትን ከማባባስ በተጨማሪ የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዳይሟሉ ያግዳል ያለው ተቋሙ፤በመገባደድ ላይ ባለው የፈረንጆች አመት ስልጣናቸውን ያለአግባብ በሚጠቀሙ አካላት ሳቢያ ክፉኛ የተጎዱት ሙስና መስጠት አቅም የሌላቸው አፍሪካውያን ድሆች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

Read 2257 times