Saturday, 05 December 2015 09:30

የቀድሞው የጊኒ መሪ 64ሺህ ዶላር በኮንትሮባንድ አሜሪካ እንዳስገቡ አመኑ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

        የቀድሞው የጊኒ ፕሬዚዳንት ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴ፤ ከሁለት አመታት በፊት በኢትዮጵያ በኩል ወደ አሜሪካ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ከ64ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ደብቀው ማሸሻቸውን ባለፈው ማክሰኞ በኖርዝ ካሮሊና ፍርድ ቤት ቀርበው እንዳመኑ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴ በወቅቱ ዋሽንግተን በሚገኘው ዱሌስ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ፣ ከ10 ሺህ ዶላር በታች እንደያዙ በመናገር ቀሪውን ገንዘብ በሻንጣቸው ውስጥ ደብቀው ለማሳለፍ መሞከራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ይህ ድርጊታቸው በጥበቃ ሃይሎች ተደርሶበት ክስ እንደተመሰረተባቸው ገልጧል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ለፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ቃላቸውን በሰጡበት ወቅትም፣ በቋንቋ ችግር ምክንያት በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ያለውን የጉምሩክ አሰራር በአግባቡ መረዳት አልቻልኩም ብለው ሊያመልጡ መሞከራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር እንዳለው፤ የ51 አመቱ ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴን ጉዳይ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት በመጪው የካቲት በሚሰየም ችሎት በግለሰቡ ላይ እስከ አምስት አመት የሚደርስ እስራት ቅጣት ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሴኩባ ኮናቴ በጊኒ የ50 አመታት ታሪክ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በተባለውና እ.ኤ.አ በ2010 በተከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ ስልጣን እንደለቀቁ ያስታወሰው ዘገባው፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም የአፍሪካ ህብረት የጸጥታ ሃይል ጄኔራል ኮማንደር ሆነው ሲያገለግሉ እንደቆዩ ጠቁሟል፡፡

Read 1861 times