Saturday, 05 December 2015 09:32

በቻይና የቆሸሹ መኪኖችን የሚያሽከረክሩ ሾፌሮች ሊቀጡ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 - በዱባይ በበኩሏ ጤናማ
             አኗኗር የሚከተሉትን ልትሸልም ነው
    የጂያንግሱ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውና በምስራቃዊ ቻይና የምትገኘው የናንጂንግ ከተማ የቆሸሹ መኪኖችን ሲያሽከረክሩ የተገኙ ሾፌሮችን በገንዘብ የምትቀጣበትን አዲስ አሰራር ተግባራዊ ልታደርግ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከተማዋ ገጽታዋን ለመገንባት የጀመረችው እንቅስቃሴ አካል የሆነው ይህ የቅጣት መመሪያ እንደሚለው፣ አካላቸውና ጎማቸው የቆሸሸ መኪኖች 16 ዶላር፣ የታርጋ ቁጥራቸው በቆሻሻ የደበዘዘ ወይም ህጋዊ ፍቃድ የሌለው ማስታወቂያ የተለጠፈባቸው መኪኖች እስከ 320 ዶላር የሚደርስ ቅጣት ይጣልባቸዋል ይላል፡፡
ኒጃንግ ዴይሊ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ አዲሱን መመሪያ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ ቻይናውያን የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች “የእኛ መኪና ለቆሸሸ፣ መንግስትን ምን ጥልቅ አደረገው” ሲሉ የከተማዋ አስተዳደር ያቀደውን የቅጣት አሰራር ክፉኛ እየተቹት እንደሚገኙ ዘገባው ገልጧል፡፡
አንዳንዶቹ የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎችም የቅጣት አሰራሩን መንግስት ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲል የቀየሰው ተገቢ ያልሆነ ስልት ነው ሲሉ መተቸታቸው ተነግሯል፡፡ዱባይ በበኩሏ! ነዋሪዎቿን ንቁና ጤናማ እንዲሆኑ ለማበረታታት በማሰብ የሲኒማ መግቢያ ትኬትና ነጻ የጂምናዚየም አባልነት መታወቂያ ልትሰጥ ማቀዷን ገልፍ ኒውስ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ የዱባይ የጤና ባለስልጣን መስሪያ ቤት ያወጣው አዲስ የማበረታቻ ዕቅድ እንደሚለው፣ አዘውትረው ጤናማ ምግብ የሚመገቡና የሰውነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በሁሉም የዕድሜ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች በየጊዜው በድረገጽ አማካይነት የሚሰጡት ሳምንታዊ ውጤት ተመዝግቦ የማበረታቻ ሽልማቱን ያገኛሉ፡፡
69 በመቶ የዱባይ ነዋሪ የሆኑ አዋቂዎች ከመጠን ያለፈ የውፍረት ችግር ተጠቂ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ከተማዋ ከዚህ በፊትም ክብደታቸውን ለመቀነስ የቻሉ ነዋሪዎቿን ወርቅ የምትሸልምበት አሰራር ተግባራዊ አድርጋ እንደነበር አስታውሷል፡፡

Read 1911 times