Print this page
Saturday, 05 December 2015 09:24

አምጦ መውለድ ወይስ በቀዶ ህክምና?

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(11 votes)

        በቀዶ ህክምና ልጅን የመገላገል ዘዴ (ሴስሪያን ሴክሽን) እንዲህ እንደዛሬው ምጥን በመፍራት አምጦ መውለድን በማይሹ ሴቶች ሁሉ ተመራጭ ከመሆኑ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጥሮአዊ መንገድ መውለድ ተስኖአቸው፣ ህይወታቸው ለአደጋ ለተጋለጠ ሴቶች ብቻ ነበር ተግባራዊ የሚደረገው፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ለመጀመሪያ ጊዜ በቀዶ ህክምና የተወለደው ጁሊየስ ቄሳር ነው፡፡ የጁሊየስ እናት በሆዷ የያዘችውን ፅንስ ለመገላገል ቀናትን የፈጀና አድካሚ የምጥ ጊዜን ብታሳልፍም ልጇ በተፈጥሮአዊ መንገድ ሊወለድ ባለመቻሉ፣በህክምና ባለሙያዎች ሆዷ በስለት ተቀዶ ልጇን እንድትገላገል ተደርጋለች። ህክምናውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ  ሴሴሪያን ሴክሽን (ቄሳራዊ ቅድ) የሚል ስያሜ እንደተሰጠው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ሴሴሪያን ሴክሽን (በቀዶ ህክምና ልጅን የመገላገል ዘዴ) በሆድ ላይ ከሚከናወኑ የቀዶ ህክምናዎች መካከል ዋንኛው እንደሆነ የሚገልፁት ዶክተር ተስፋዬ ታከለ፤ህክምናው በአግባቡና አስፈላጊ በሆነ ጊዜ በባለሙያው ሲከወን ህይወትን ሊታደግ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ይህንን ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ ከሚገደዱባቸው ምክንያቶች ዋንኞቹ የምጥ በአግባቡ አለመምጣት (ዴስቶኪያ)፣ የፅንሱ አቀማመጥ የተስተካከለ አለመሆን፣ የማህፀን በር መጥበብ፣ መንታ ፅንስ ሲኖሩ፣ በፅንሱ ላይ የጤና እክሎች መኖር፣ ነፍሰጡሯ ሴት ከፍተኛ የደም ግፊትና የስኳር ህመም ያለባት መሆኗ ይገኙበታል። በነፍሰጡሯ ሴት ላይ እንዲህ አይነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት የጤና ባለሙያዎች በቀዶ ህክምና የማዋለዱን ዘዴ ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚገባና ይህም የእናቲቱንም ሆነ የህፃኑን ህይወት ከሞት ሊታደግ እንደሚችል ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ሁኔታ በተለየና በእናቲቱም ሆነ በፅንሱ ላይ አንዳችም የጤና ችግር ሳይፈጠር አምጦ መውለድን በመፍራትና በወሊድ ወቅት የሚያጋጥምን ህመምና ስቃይ ለመሸሽ ይኸው በቀዶ ህክምና ልጅን የማገላገሉ ዘዴ ተግባራዊ እንደሚደረግ የሚገልፁት ዶክተሩ፤ሁኔታው በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በተለይም በከተሞች አካባቢ በስፋት እየታየ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ምንም አይነት የጤና ችግር ሳይኖርባቸው ልጃቸውን በቀዶ ህክምና ለመውለድ የሚፈልጉ ሴቶች፤ የኢኮኖሚ አቅማቸው ከፍ ያለና የህክምና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ እናቶች በፈፀሙት የቀዶ ህክምና ወሊድ ሳቢያ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡  
የአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በቀዶ ህክምና ልጅን የማገላገል ዘዴ (ሴሴሪያን ሴክሸን) እናቶችንም ሆነ የተወለዱትን ህፃናት ለከፋ የጤና ችግር እንዲጋለጡ ያደርጋል፡፡ ኢንፌክሽኖች፣ ከፍተኛ የደም መፍሰስ፣ ከማደንዘዣ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ በሌሎች የሰውነት አካላት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች፣ የስነልቦና ቀውስና የእናቶች ሞት በተፈጥሮአዊ መንገድ ከሚከወነው ወሊድ ይልቅ በቀዶ ህክምና በሚደረጉ ወሊዶች ላይ በስፋት ያጋጥማል፡፡ “አንዲት በቀዶ ህክምና ልጇን የተገላገለች ሴት፣ በመደበኛው መንገድ ልጇን ከወለደች ሴት እኩል የስነልቦና እርካታና ደስታ ታገኛለች ማለቱ ከባድ ነው” ያሉት ዶክተሩ፤ እናቲቱ በምጥ ወቅት በምታሳልፈው ህመምና ስቃይ የምታገኘው አዕምሯዊና ሥነልቦናዊ እርካታ በምንም ሁኔታ ሊገለጽና ሊተካ የሚችል አይደለም ብለዋል፡፡ ተፈጥሮ እናትና ልጅን ከምታስተሳስርባቸው አንዱና ዋንኛው መንገድ፣ ምጥና ወሊድ መሆኑንም እኚሁ ዶክተር ገልፀዋል፡፡
በአሜሪካ በሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች የተደረገውን ጥናት ዋቢ አድርጐ የአለም ጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ፤ በቀዶ ህክምና ልጃቸውን ከተገላገሉ 970ሺ ሴቶች መካከል 2500 የሆኑት ለኢንፌክሽን መጋለጣቸውን፣ 500 ያህሉ ደግሞ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉንና ህክምናው ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ወጪ መጠየቁን ያመለክታል፡፡ በአሜሪካ የተደረገውን ሌላ ጥናት መሰረት አድርጐ ዋሺንግተን ፖስት እንደዘገበው፤ በቀዶ ህክምና የተወለዱት ህፃናት በደም ህዋሳት ኢንፌክሽንና በመተንፈሻ አካላት ላይ በሚደርሱ ጉዳቶች የመጠቃታቸው እድል በተፈጥሮአዊው መንገድ ከተወለዱት ህፃናት በእጥፍ የላቀ ነው፡፡ በጥናቱ ውስጥ እንዲካተቱ ከተደረጉት 30ሺ ህፃናት መካከል 20% የሚሆኑት የደም ስኳር መመረዝና የመተንፈስ ችግር አጋጥሟቸው ተገኝተዋል፡፡ በተለመደው ተፈጥሮአዊ መንገድ በምጥ በቀጥታ ከሚወልዱ ሴቶች ጋር ሲነፃፀር፣ በቀዶ ህክምና የሚወልዱ ሴቶች የመሞት እድል በአራት እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑንም ይኸው መረጃ አመላክቷል፡፡
የአሜሪካ የህክምና ባለሙያዎች፣እናቶች ልጆቻቸውን በተፈጥሮአዊው መንገድ በምጥ እንዲገላገሉ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ በቀዶ ህክምና የሚከናወነው ወሊድ በህፃኑም ሆነ በእናቲቱ ላይ ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ጉዳቶች ሰፊ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አትቷል፡፡
በአገራችን በቀዶ ህክምና በሚፈፀም ወሊድ ሳቢያ በእናቲቱም ሆነ በሚወለዱት ህፃናት ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን አስመልክቶ የተደረገ ጥናት ባይኖርም በየህክምና ተቋማቱ ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ለሞት የሚጋለጡትና በተለያዩ ኢንፌክሽኖች የሚጠቁት በአብዛኛው በቀዶ ህክምና ልጃቸውን የተገላገሉ እናቶች መሆናቸውን ዶክተር ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡
በቀዶ ህክምና መውለድ የእናቲቱንም ሆነ የፅንሱን ህይወት ለማዳን በባለሙያዎች ታምኖበት ሲከወን ህይወት አድን የህክምና ዘዴ የመሆኑን ያህል አላስፈላጊ የሲሴሪያን ሴክሽን ክዋኔዎች ለከፋ የጤናና የሞት አደጋ ያጋልጣሉ፡፡

Read 9955 times