Saturday, 05 December 2015 09:13

ወይን

Written by  ደራሲ፡- ዶሪስ ሌሲንግ ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(7 votes)

         መንገድ ዳር ካለችው አነስተኛ ሆቴል ወጥተው ትንሽ እንደተጓዙ ግራ-ቀኝ ዛፍ የበቀለበት ሰፊ መንገድ ተቀበላቸው፡፡
ዛፎቹ ቅጠላቸው አሁንም እንደረገፈ ነው፤ ጠቁረዋል፤ አይን አይስቡም፡፡ ለፀደይ ወራት የተረገዙ ሚጢጢ ቅርንጫፎች ይታያሉ፡፡ ቀና ሲባል እነኚሁ ሚጢጢ ቅርጫፎች በቅርቡ አብረቅራቂ፣ አረንጓዴ ሸማ ለብሰን እንመጣለን፤ ጠብቁን የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ሁሉ ነገር እርግት፣ ዝም፣ ፀጥ ያለ ነው፡፡ ጥበበኛ እጅ የወለወለው የሚመስለው ሰማያዊ ሰማይም ፀጥ ብሏል።
ፍቅረኛሞቹ አብረው እያዘገሙ ነው፡፡ ከብዙ ቀናት እረፍት በኋላ የሚደረግ እንቅስቃሴ እጅጉን ያደክማል። ትንሸ እንደተጓዙ በቅርባቸው  ያገኙት መዝናኛ ቤት ዘው ብለው ገቡ፡፡ ልክ ከባድ ስራ እንዳደከማቸው ሁሉ በመጀመሪያ ያገኟቸው ሶፋዎች ላይ ዘፍ አሉ። የተቀመጡበት ቦታ ያሉት ግድግዳዎች በመስታወት የተሰሩና ወደ መንገዱ ያሞጠሞጡ ናቸው፡፡
ቤቱ ባዶ ነው፤ አንድም ደንበኛ የለም፡፡ የምሳ ሰዓት ስለሆነ ሰዎች በዚህ ሰዓት የሚያዘወትሩት ምግብ ቤቶችን ነው፡፡ ምግብ ቤት ያልሄዱት ሰዎች መንገድ ላይ ይታያሉ፡፡ በቅርቡ እንኳ ሰልፈኞች ሲያልፉ ነበር፡፡ አሁንም ከሩቁ ተበታትነው ይታያሉ፡፡  የሰልፈኞቹ የአመፃ ድምጽ፣ መፈክርና ዘፈን እንደ ጠዋቱ የፓሪስን ትራፊክ ሁካታ አልዋጠውም፡፡ ጥንዶቹንም ከእንቅልፋቸው የቀሰቀሳቸው የእነኚሁ ሰልፈኞች ድምጽ ነበር፡፡
አስተናጋጁ በሩን ተደግፎ ሰልፈኞቹን እያያቸው ነበር፡፡ እየደበረው ትእዛዝ ሊቀበል ወደ እነሱ መጣ፡፡ ቡና አዘዙ፡፡
ሰውየው አዛጋ፡፡ ሴትየዋም ተጋባባትና አዛጋች። ሳቃቸው መጣ፤ ከመጣህ አይቀር ብለው ሳቁት። ሁለቱም ‘እኔ ነኝ ጥፋተኛ’፤ ‘አይ እኔ ነኝ ጥፋተኛ’ አይነት ተያዩ፡፡  በአይኖቻቸው ይቅርታ ተጠያየቁ። ጉዳዩ በዚሁ አበቃ፡፡ አይኖቻቸው ተፋቱ፡፡ ቡናው ቀርቦላቸዋል፤ አንዳቸውም አልነኩትም እንጂ፡፡ ሁለቱም ዝም እንዳሉ ናቸው፡፡ ሴትየዋ ዳግም አዛጋች። ይሄኔ ሰውየው አይኖቹን ካሉበት መልሶ አፈጠጠባት፤ እሷም አፈጠጠችበት፡፡ ሁለቱም ፊት ላይ፡- “መተኛት እፈልጋለሁ፡፡” የሚል መልእክት ጥርት፣ ድምቅ ተደርጎ ተፅፏል፡፡ አብረው እንዲተኙ የሚገፏፏቸው ነገሮች አሁን የሉም፡፡ የቀራቸው ነገር ቢኖር ስሜታቸውን ሳይደብቁ፣ አይን ለአይን መተያየት መቻላቸው ብቻ ነው፡፡ ስሜታቸው ምንም ይሁን ምን ሳይሸሽጉት፣ በእርጋታ አይን ለአይን መተያየት ይችላሉ፡፡
ስትታገለው የከረመችው ሀዘን በርትቶ መጣባት፡፡ አልቻለችውም፡፡ እሱን ደግሞ ጭካኔ ጎበኘው፡፡
“አፍንጫሽ ፓውደር ያስፈልገዋል፡፡ አላት፡፡
“ማሙሽ፣ አንተ ደግሞ ግርፊያ ያስፈልግሃል፡፡”
እሱ ሀዘኑን ተቋቁሟል፡፡ ማዘን አይፈልግም፡፡ ‘እንግዲህ ይሁና!’ በሚል አይነት ትከሻዋን ሰበቀችና ወደ ውጭ ማየት ያዘች፡፡ እሱም እንዲሁ አደረገ፡፡ ከርቀት ሰልፈኞቹ ልክ እንደተተነኮስ የጉንዳን መንጋ ሲራወጡ በደብዛዛው ይታያል፡፡ ሰውየው እንዲህ ሲል አጉረመረመ፡- “አዎ፤ እንዲሁ ይቀጥላል…”
እሷም በማላገጥ እንዲህ አለች፡- “አንዳችም ነገር አይለወጥም፤ ሁሉም ነገር ሁሌም ተመሳሳይ እንደሆነ ይቀጥላል…….”
ፊቱ ቀላ፡፡ ሰውነቱ ውስጥ ያለው ደም በሙሉ ወደ ፊቱ የገነፈለ ነው የሚመስለው፡፡ “አስታውሳለሁ፡፡” ብሎ ጀመረ፡፡ የድምጹ ቃና ተቀይሯል፡፡ የጀመረውን ወሬ አቋረጠ፡፡ እሷም እንዲቀጥል አልገፋፋችውም። እሩቅ ያሉትን ሰልፈኞች እያየ ነበር፡፡ መሪር የሆነ ትውስታ እንደቀሰቀሱበት ያስታውቃል፡፡
መንገዱ ላይ ፍቅረኛሞች፣ ባለትዳሮች፣ ተማሪዎች፣ አዛውንቶች ሲሄዱ ይታያሉ፡፡ ወዲያ የተራቆቱ ዛፎች አሉ፤ ወዲያ፣ ወዲያ ደግሞ ፀጥ ያለው ሰማያዊው ሰማይ ይታያል፡፡ … በአንድ ወር ውስጥ፡- ዛፎቹ ደማቅ አረንጓዴ ይሆናሉ፤ ፀሀይቷ ሙቀቷን ታፈሰዋለች፤ ሰዎች ጠይምና ሳቂታ ይሆናሉ፤ ቁምጣ መልበስ ያዘወትራሉ። ‘አይሆንም፡፡ አይሆንም፡፡’ አለች ለራሷ፡፡ በምናብ የታያትን በእንቅስቃሴ የተሞላ፣ ቀልጣፋ የህይወት ምስል አልወደደችውም፡፡ የለመደችው፣ እርግት ያለ፣ በሀዘን የታጠረ ህይወቷ ይሻላታል፡፡ በአንዴ ከየት መጣ ሳይባል ሀዘን አፈናት፡፡ ሀዘኑን ሸሽታ፣ አስራ አምስት አመት ወደ ኋላ፣ ወደ ሌላ ሀገር ሄደች። ፍንትው ያለች ጨረቃ ስር፣ እጆቿን ለሚያምረው መልክዐ-ምድር ዘርግታ ቆማለች። ከፀጥታ በቀር መልስ አላገኘችም። ከመልክዐ-ምድሩ መልስ ስታጣ ቁልቁል ሮጠች፡፡ ትንንሽዬ የሚያብረቀርቁ ጠጠሮች እግሯ ስር እየታዩዋት፤ ትንፋሽ አጥሯት የሚያብረቀርቅ የሳር ጫካ ውስጥ ወድቃ እስክትቀበር ድረስ ሮጠች፡፡ አስራ አምስት አመታት፡፡
ልክ ይህን እያሰበች ባለችበት ቅፅበት ሰውየው አስተናጋጁን ጠራው፡፡ ወይን አዘዘ፡፡
“ምን” አለች በቀልድ፡- “ገና ካሁኑ?”
“ምን አለበት?”
ተቃራኒውን ስሜት ለጊዜው አፍና ይዛ ሙሉ ለሙሉ ውድድ አደረገችው፤ ልክ እናት ልጇን እንደምትወደው አይነት፡፡ በጉጉት ሲቁነጠነጥ እያየችው ወይኑን ሁለት ብርጭቆዎች ላይ ቀድታ፣ እስከ አሁን ጢም እንዳሉ ካሉት የቡና ስኒዎች አጠገብ አስቀመጠቻቸው፡፡ አሁንም ግን የዛሬ አስራ አምስት አመት በጨረቃዋ ብርሀን ስትፈነድቅ የነበረችውን ኮረዳ እያስታወሰች ነበር፤ በዛፎቹ መሀል ወደር በሌለው ነፃነት ስትሮጥ ታየቻት፤ ለማንም ሊያጋሩት፤ ለማንም ሊነግሩት የማይቻል ስሜት ውስጥ ነበረች፡፡ አዎ፤ ነገርየው እንዲያ ነበር፡፡
“ምን እያሰብሽ ነው?” ብሎ ጠየቃት፡፡ ጭካኔው ሙሉ ለሙሉ አለቀቀውም፡፡
“ተወኝ እስኪ ባክህ፡፡” አለች የቀልድ እየተቆጣች፡፡
“ይህ ነው እንግዲህ ችግሩ፤ ይህ ነው እንግዲህ ችግሩ፡፡” አለ፡፡ ብርጭቆውን አነሳ፤ ሴትየዋን ገርመም አደረጋት፤ እና ሳይቀምሰው አስቀመጠው፡- “መጠጣት አልፈለግሽም እንዴ?”
“ቆይ፡፡”
ማጨስ ጀመረ፡፡
በእንዲህ አይነት ቅፅበቶች ስሜትን መግለጽ ግድ ይሆናል - እንዲያው በትንሹም ቢሆን እንኳ፤ ያልታሰበበት፣ ድንገት የተደረገ ቢሆንም ወይም ቢመስልም እንኳ ስሜትን ማሳወቅ ያስፈልጋል። ሁለቱም ሰዎች በውስጣቸው ሁለት የተለያዩ ሰዎች ይዘው ነው የሚዞሩት፡፡ አንደኛው ሰብዕና፡- ሁሌም በማይታክቱ አይኖች በስስት የሚመለከትና የሚከታተል ነው፡፡ ክትትሉ አባርቶ አያውቅም፡፡ ቢቀሰቅሱት የማይነቃ፣ ስልችት ያለው ሀዘኔታ አለበት፡፡ ከአሁን በኋላ ግድ የለኝም፣ ከአሁን በኋላ አያገባኝም አይነት ነገር ነው። ሁለተኛው፡- የአመፃ ልጅ ነው፡፡ ቁጣ፣ ቁጣ ይለዋል፡፡ በፍላጎትና በእፎይታ፣ አዲስ ነገር በመፍጠርና በስኬት መሀል ዥዋ-ዥዌ ይጫወታል፤ ይህንኛው ሰብዕና፡፡
የጭካኔ ፊቱን አሳያት፡፡ ተያዩ፡፡ አሳዛኙን ምፀት በአይኖቻቸው ተቀባበሉ፡፡ እሱ በብስጭት እጁን ወደ ጠረጴዛው ወሰድ መለስ አደረገ፡፡ አይኖቹን ከእሷ ላይ አነሳ፡፡ እሷም አይኖቿን ከእሱ ወሰደቻቸው፡፡ አሻግራ በማቆጥቆጥ ላይ ያሉትን ትንንሽዬ ቅርጫፎች በሀሴት ሲወዛወዙ፣ ለአዲስ ህይወት ሲያሸበሽቡ አየቻቸው፡፡
“አስታውሳለሁ፡፡” ብሎ አሁንም ጀመረ፡፡
“እባክህ እስኪ ተወኝ!” አለች በስጨት ብላ፡፡
እራሱን ተቆጣጠረ፡- “ውዴ” አለ ለዛ በሌለው፣ ደረቅ ድምፅ፡- “ዘመኔን ሁሉ ከአንቺ ሌላ ሴት አፍቅሬ አላውቅም፡፡” ሁለቱም ሳቁ፡፡
“ይህ መንገድ ሳይሆን አይቀርም ትዝታዬን የቀሰቀሰው፡፡ አሊያም ይህ አሁን ያለንበት መዝናኛ ቤት ይሆን ይሆናል፡፡ ሁሉ ነገር ተቀያይሮአል ግን። ትናንትና እዚህ በነበርሁበት ወቅት አዘወትረው ወደ ነበረው ቤት ሄድኩ፡፡ ኬክ ቤት አድርገውታል፡፡ ሴትየዋም ልታስታውሰኝ አልቻለችም፤ ረስታኛለች፡፡ አንድ እለት ነው፤ ብዙ ሆነን መጣን፤ ብዙ ጊዜ ብዙ ሆነን ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ አንዲት ልጅ እዚህ ቤት አየሁኝ፤ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው እዚህ ሳያት፡፡ ያኔ ለመቀጣጠሪያ የሚሆኑ የተወሰኑ፣ ታዋቂ ቤቶች ነበሩ፡፡ ቤቱ እንደዚያ አይነት ነው፡፡ ሰዎች ከቪየናም ይምጡ ከፕራግ፣ ከየትም ቦታ ይምጡ ብቻ እኒያን ቤቶች ያውቋቸዋል፡፡ እዚያ ነው መገናኛቸው፡፡ ተጠራጠርኩ እኮ፤ መቼስ ይሄ ቤት አይሆንም ብዬ፡፡ በጣም አሳምረውታል፤ እኛ ይህን ሁሉ ማስዋቢያ ሊያስገዛቸው የሚችል ብር አናወጣም ነበራ።”
“እሺ፤ ቀጥል፡፡”
“ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንጃ ብቻ ሰሞኑን ትዝ እያለችኝ ነው ልጅቷ፡፡ ለረዥም አመታት አስታውሼያት አላውቅም ነበር፡፡ ስገምት አስራ ስድስት ቢሆናት ነው። ቁንጅት ያለች ነገር ናት-አይደለም፣ አይደለም፤ በጣም ተሳስተሻል፡፡ መፅህፎቿን ይዛ እኔ ክፍል ትመጣና አብረን እናጠናለን፡፡ ወደድኳት፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ ፍቅረኛ ነበረችኝ፡፡ ከፍቅረኛዬ ጋር አብረን አናጠናም፤ እሷ የምትማረው ሌላ ነገር ነበር፤ ምን እንደሆነ ረሳሁት ግን፡፡” አሁንም ንግግሩን አቆመ፤ አሁንም ፊቱ በትዝታ ሰብስብ፤ ጭምድድ አለ፡፡ ሴትየዋ ሳይታወቃት ዞር ብላ ወደ መንገዱ አየች፡፡ ሰልፈኞቹ አይታዩም፤ ዘፈናቸውንም፣ ጩኸታቸውንም ይዘው ሄደዋል፤ ምንም አይሰማም፡፡
“ለምን መሰለሽ ያስታወስኳት …” በተመስጦ ሲያስብ ከቆየ በኋላ፡- “ሁል ጊዜም አፍቅረው ድንግላናቸውን በፈቃዳቸው ይኸው የሚሉ ልጃገረዶች ‘አልፈልግሽም’ መባል እጣ-ፈንታቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡”
“ምን!” ደንግጣ ጮኸች፡፡ ንዴት ውስጧ ተላወሰ፡፡ ንዴቷን ለጉማ በረዥሙ ተነፈሰች፡፡
“ቀጥል፡፡”
“አልተኛኋትም፡፡ በጋውን ሙሉ አብረን አጠናን። በአንዱ የሳምንት መጨረሻ ተሰባስበን፤ ብዙ ሆነን ወጣን፡፡ ማናችንም ገንዘብ አልነበረንም፤ ግልፅ ነው። ሊፍት እየጠየቅን፣ በየመንደሩ እየተጠባበቅን ነው እንሄድ የነበረው፡፡ ፍቅረኛዬ አብራኝ ነበረች፡፡ ለመኝታችንም ዘዴ አላጣንም፡፡ ገበሬዎቹን ፍራፍሬ በመልቀም እናግዛቸዋለን፤እነሱ ደግሞ በልዋጩ የእህል ማከማቺያቸው ቤት ውስጥ እንድናድር ይፈቅዱልናል። አንድ ቀን ነው፤ ምሽት ነበር፡፡ ሁላችንም እየዘፈንን፣ እየቀበጥን ነበር፡፡ ፍቅር በፍቅር ሆነናል፡፡ ሁላችንም። ሳምኳት፡፡ ከመሳሳም ውጪ ምንም አላደረግንም፡፡ ለሊት ወደ አለሁበት መጣች፡፡ ከአንድ ልጅ ጋር ቆጥ ላይ ተኝተን ነበር፡፡ ልጁ እንቅልፍ ወስዶታል፡፡ ሴቶቹ የገለባው ክምር ጋ ነበር የሚያድሩት፤ ወደ እዚያ እንድትመለስ አደረግሁ። ገና ልጅ ነሽ እሺ አልኳት፡፡ በእድሜ ከፍቅረኛዬ አታንስም ነበር ግን--” ንግግሩን ቆም አደረገ፡፡ ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላም ጥልቅ ሀዘንና ግራ መጋባት ይታይበታል፡- “አላውቅም፡፡” አለ፡- “ለምን እንድትመለስ እንደአደረግሁ አላውቅም፡፡” ሳቀ፡-“ ብዙ አሳስቦኝ አይደለም እሺ፡፡”
“ባለጌ ነገር” አለች ሴትየዋ፡- “ስመሀታል አይደል?”
ትከሻውን ሰበቀ፡- “ሁላችንም እየተጃጃልን ነበር እኮ። ያ ምሽት መቼም አይረሳኝም፡፡ ገበሬዎቹ ‘ስራውን ትታችሁ፤ ፍቅሩን አበዛችሁ’ ብለው ይጮሁብናል። ማን ይሰማቸው ታዲያ፡፡  ፖም እየለቀምንላቸው ነበር የዚያን እለት፡፡ ወይናችንን እየጠጣን መዝፈን ነው፡፡ ስሪያውንም አጧጡፈነዋል፡፡ ጊዜው አግዞናል፤ የወጣቶች አመፅ የተቀሰቀሰበት ወቅት ነበር፡፡ ታማኝነትና ቅናት የቡርዣው ስነ-ምግባር ቅሪቶች ተደርገው ነበር የሚወሰዱት፡፡” ሳቀ። ሳቁ ውስጥ ስቃይ አለ፡- “ሳምኳት፡፡ ፍቅረኛዬ አብራኝ እንደመጣች ታውቃለች፡፡”  
“እና ሳምካት?” አለችው፣ በወቀሳ፡፡
ከወይኑ ብርጭቆ አገዳ ጋር እየተጫወተ፣ ጥርሶቹን ነክሶ፡- “አዎ የኔ ውድ” ሲል አንሾካሾከ፣ “ሳምኳት፡፡”
ንዴቷ ብልጭ አለ፡- “አፍቅራህ ፍቅርህን የፈለገች ልጅ ነበረች፡፡ ይህን እያወቅህ ሳምካት፡፡ ግን በደንብ ታውቅ ነበር …”
“ምንድነው በደንብ የማውቀው?”
“እንዲያ ማድረግ ጭካኔ መሆኑን ታውቅ ነበር፡፡”
“ልጅ ነበርኩ ያኔ፡፡”
“ለውጥ አያመጣም፤ ልጅ መሆንህ፡፡” አለች በመረበሽ፤ ልታለቅስ ምንም አልቀራት፡፡ “አብራችሁ ስታጠኑ ነበር፡፡ በጋውን በሙሉ፣ ከአስራ ስድስት አመት ልጅ ጋር ስታጠኑ ነበር!”
“ግን ስናጠና የነበረውም በቁም ነገር ነበር፡፡ ዶክተር ነው የሆነችው፣ በሙያዋ ቪየና ውስጥ ትሰራ ነበር። ናዚዎች ከተማዋን ሲወሩ ተሳክቶላት ጥላ ወጣች፣ ግን…”
ትእግስት አጣች፡- “ስመሀታል፣ ለዚያውም የዚያን ቀን ምሽት፡፡ አስባት እስኪ ሁሉም ሰው እስኪተኛ ስትጠብቅ፣ አብሮህ የተኛውን ልጅ ላለመቀስቀስ እየተጠነቀቀች የቆጡን መሰላል ስትወጣ፣ ቆማ አንተ ያለምንም ሀሳብ እንቅልፍህን ስትለጥጥ እያየችህ፣ ቀስ ብላ ልብሶቿን ስታወልቅ እና …”
“እንቅልፍ አልወሰደኝም ባክሽ፡፡ አውቄ እንቅልፍ የወሰደኝ መሰልኩ እንጂ፡፡ ካኒቴራና ቁምጣ ነበር የለበሰችው፡፡ ሴቶቻችን ቀሚስ አይለብሱም፤ ሊፕሲቲክም አይቀቡም፤ እነዚህም እንደ ቡርዣው ቅሪቶች ነበር የሚታዩት፡፡ ቆጣችን በጨረቃዋ ብርሃን ደምቋል፡፡ የለበሰችውን አውልቃ እጆቿን አፌ ላይ አድርጋ፣ ጎኔ ተኛች፡፡” አሁንም ፊቱ ላይ አግራሞት ይታያል፡- “የዚያን እለት ምን እንደሆንኩ እግዚሄር ነው የሚያውቀው፡፡ እኔ ምኑንም አላውቀውም፡፡ እጅጉን የምታምር ፍጥረት ናት እኮ፡፡ ለምን እንደ አስታወስኳት አላውቅም፡፡ ሰሞኑን ደግሞ፣ ደጋግማ እንዲሁ ትዝ ስትለኝ ነበር፡፡” ዝም አለ፣ የወይኑን ብርጭቆ ሲያሽከረክር ቆይቶ፡- “ብዙ ነገር ላይ ቀሺም ነኝ፣ ግን .” በፍጥነት እጇን ለቀም አድርጎ ሳመና ከልቡ እንዲህ አለ፡- “ለምን እንደ አስታወስኳት አላውቅም፤ ለዚያውም በዚህ ጊዜ …” ሁለቱም ተያዩና በረዥሙ ተነፈሱ፡፡
እጆቹን እጁ ላይ አድርጋ ልስልስ ባለ ድምፅ፡- “እና ወደ መጣችበት እንድትመለስ አደረክ፡፡” ሳቀ፡፡
“በነጋታው አኮረፈቺኝ፡፡ የዚያ ቀን ምሽት አብሮኝ ተኝቶ ከነበረው ልጅ ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀመረች። እንዲያ ማድረጓ አይገርምም፡፡ ግልፅ ነው፡፡ ወኔዬን፣ እሷን ለመግፋት የነበረኝን ወኔ ለጉድ ነው የጠላችው። አይፈረድባትም፡፡”  
“እስኪ አስባት፡፡ በዚያን ቀን፣ በዚያን ምሽት፣ በዚያች ቅፅበት ምን ሊሰማት እንደሚችል አስብ፡፡ ልብሶቿን ሰብስባ ወደ አንተ ለማየት ድፍረት አጥታ…” አቋረጣት፡፡
“የሚገርምሽ እብድ ነው የሆነችው፡፡ የምታውቃቸውን ስድቦች ሁሉ አወረደችብኝ፡፡ ዝም እንድትል፣ ኸረ የተኙትን ሁሉ ትቀሰቅሽያለሽ ብዬ ደጋግሜ መንገር ነበረብኝ፡፡”
እሷ ቀጠለች፡- “ከቆጡ ወረደች፡፡ ጨለማው ውስጥ ሆና ልብሷን ለበሰች፡፡ ከዚያ ከነበራችሁበት የእህል ማከማቻ ወጣች፤ በደረሰባት ሀፍረት የተነሳ ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር መቀላቀል አትችልምም፤ አትፈልግምም ነበር ፤ በዚያን ሰአት፡፡ ከዚያ ወደ ፍራፍሬው እርሻ ሄደች፡፡ ጨረቃዋ አሁንም እንደ ደመቀች ናት፡፡ ጭር ብሏል፡፡ የሚያስፈራ ፀጥታ ነው፡፡ እንዴት ስትዘፍኑ፣ ስትስቁ፣ ስትቀብጡ እንደ ነበር ታወሳት፡፡ ወደ ተሳሳማችሁባት ዛፍ ጋ ሄደች፡፡ የጨረቃዋ ብርሃን፣ የፖም ዛፎቹንና ፍሬዎቹን አድምቋቸዋል፡፡ ፈጽሞ አትረሳውም ያን ምሽት … ፈፅሞ፡፡ ፈፅሞ፡፡”
በመገረም አያት፡፡ ጉንጮቿ በእንባ እርሰዋል፡፡
“ዘግናኝ ነው፡፡” አለች፡- “እጅጉን ዘግናኝ። ምንም ነገር ሊክሳት አይችልም፡፡ በህይወት እስካለች ድረስ ምንም ነገር ያን ጉዳት ሊጠግንላት አይችልም። በህይወቷ ውስጥ ሁሉ ነገር ሲሳካ፣ ሁሉ ነገር ሲሰምርላት፣ ህይወቷ ሙሉ ሲሆን ልክ በዚያች ቅፅበት ያ ምሽት ትዝ ይላታል። አጠገቧ ምንም የለም፣ በአለም ላይ ብቻዋን ሆና …… ያቺ የተረገመች፣ እሩቅ ያለች፣ የማይደረስባት ጨረቃ ብቻ፣ ድምቅ ብላ …”
በተንኮለኛ አይኖች አያት፡፡ ከዚያ በቀልድ ሁኔታ፣ ሁኔታዎችን በሚያስረሳ አኳኋን ወደ ፊት ሰገግ ብሎ ሳማትና እንዲህ አለ፡- “ውዴ የእኔ ጥፋት አይደለም፡፡ በቃ የእኔ ጥፋት አይደለም፡፡”
“አይደለም፡፡” አለች፡፡
ወይኑን አንስቶ እጇ ላይ አስቀመጠው፡፡ መጠጡን ከፍ አድርጋ የብርጭቆውን ቅርፅ ይዞ ትንሽዬ ቀይ ሉል የሚመስለውን፣ ብዙ በመቀመጡ መሞቅ የጀመረውን ፈሳሽ አየች፡፡ አጋጩ፡፡ አብረው ጠጡ፡፡
እ.ኤ.አ 1957 ዓ.ም
(የዚህ አጭር ልብ-ወለድ የእንግሊዝኛው ርእስ፡-Wine ነው፡፡)    
ስለ ደራሲዋ፡-
ዶሪስ ሌሲንግ እንግሊዛዊት የአጫጭርና የረዣዥም ልብ-ወለዶች ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ጸሀፊ ተውኔትና የህይወት ታሪክ ፀሀፊ ነበረች፡፡  እ.ኤ.አ በ2001 ዓ.ም. በእንግሊዝ ስነ-ፅሁፍ ለህይወት ዘመን ስኬት የሚበረከተውን  የDavid Cohen Prize ተሸልማለች፤ እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም. በስነ ፅሁፍ የኖቤል ሽልማት አሸንፋለች፤ እ.ኤ.አ. በ2008 ዓ.ም. ደግሞ ታይም መፅሔት እ.ኤ.አ. ከ1945 ዓ.ም. ወዲህ ከአሉ እና ከነበሩ ምርጥ 50 ደራሲያን 5ኛዋ አድርጎ መርጧታል፡፡
ዶሪስ በ88 አመቷ ኖቤል በመሸለም በጎምቱ ደራሲነት ሪከርዱን ይዛለች፡፡ ዶሪስ  እ.ኤ.አ. በ1919 ዓ.ም. ተወለደች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 ዓ.ም. ሞተች፡፡

Read 3402 times