Saturday, 05 December 2015 08:58

“ለበጎ ነው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(16 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው በታክሲ እየተጓዘ ነበር፡ ለሾፌሩ የሆነ ነገር ሊነግረው ይፈልግና ትከሻውን ነካ ያደርገዋል፡ ሾፌሩም ይደነግጥና መኪናውን መቆጣጠር አቅቶት ሄዶ ከግንብ ጋር ይጋጫል፡፡ ለትንሽ ጊዜ ዝምታ ይሆናል፡፡ ከዚያም ሾፌር ዘወር ብሎ…
“ለምንድነው ትከሻዬን የምትነካኝ! አስደነገጥከኝ እኮ!” ብሎ ይቆጣል፡፡
ሰውዬውም፣ “የሆነ ጥያቄ ልጠይቅህ ፈልጌ ነው፡፡ እኔ በትንሹ ነካ ማድረግ እንዲህ ያስነግጥሀል ብዬ አላሰብኩም…” ይለዋል፡፡
ከዛም ሾፌሩ ተረጋጋና ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ይቅርታ፣ የአንተ ጥፋት አይደለም፡፡ አየህ ታክሲ ስነዳ ገና የመጀመሪያ ቀኔ ነው፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት የሬሳ መኪና ስነዳ ነበር፣” ብሎት አረፈ፡፡
ሳታስቡት ከኋላ ትከሻችሁን ነክቶ ከሚያስደነግጥ ይሰውራችሁማ፡፡ ለምሳሌ የበቀደሙ የባቡር ‘በደረሰበት ቦታ ቀጥ የማለት’ ነገር ሳይታሰብ ከኋላ ትከሻን እንደመንካት የሚቆጠር ነው፡፡ ልክ ነዋ…ወላ የኃይል መቋረጥ፣ ወላ ምናምን ነገር አያስተጓጉለውም ተብሎ አልነበር እንዴ! ወይንም ‘ድንገት አገልግሎት ሊቋረጥ የሚችልባቸው ሁኔታዎች’ ምናምን ተብሎ ሊነገረን ይገባ ነበር፡፡
እኔ የምለው…እዚህ አገር ጥንቅቅ ብሎ የሚያልቅ ነገር ሊጠፋ ነው ያሰኛል፡፡ እኛ እኮ በተነገረን ነገር…አለ አይደል… “ዶንት ወሪ፣ ቢ ሀፒ” እያልን መውረግረግ ልንጀምር ነበር፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እንዲህ ችግር ሲበዛ፣ ቀኝ ያሉት ነገር ግራ ሲሆን፣ ያመኑት ሲከዳ፣ መሶቡ ሲሳሳ…አንድ የምንላት ነገር አለች፣ “ይሄ ሁሉ ለደግ ነው…” እንላለን፡፡
እናማ…ክፉ ነገር ሁሉ ‘ለደግ’ የሚሆነው እንዴት ነው! ነገርዬው… አለ አይደል… ራስን ለማረጋጋት ምናምን አሪፍ ነው፡፡ ግንላችሁ…“ለደግ ነው…”  ብሎ እጅን አጣምሮ መቀመጥ ወንዝ አያሻግርም፡ ቂ..ቂ…ቂ… (ስሙኝማ…እንደ ኤለኒኖ አኳኋን ከሆነ “መሻገሩ ቀርቶብን መጀመሪያ ወንዙ በተገኘ…” የምንልበት ደረጃ እንዳንደርስ!“
እናማ… ኑሮም ሲከፋ “ለደግ ነው…” ያመንነው ሰው ሲከዳን “ለደግ ነው…”  ያስቀመጥነው ነገር ማን እንደወሰደው ሳናውቅ ደብዛው ሲጠፋ “ለደግ ነው…” ሦስት ሱሪዎቻችን አይጥ የካምቦሎጆ መረብ ሲያስመስላቸው…“ለደግ ነው…” የሆነ ክፉ ሰው የላባችንን ሲያስቀርብን “ለደግ ነው…” እንላለን፡፡
እናላችሁ…ልክ እኮ… “አንድዬ ለእኛ ‘ደግ ነገር’ ማድረግ ሲፈለግ ምልክት የሚሰጠን ‘በክፉ ነገር’ ነው…” እንደማለት ነው፡፡ የምር ግን…እስቲ ለደግ ነው ካልናቸው ነገሮች ለደግ ሆነው ያለቁትን በድምር ቅንስ እናውጣማ!
የተቦደሱት ሱሪዎቻችን እንኳን ሊተኩ ያሉትም እየነተቡ ነው… የላባችንን ያስቀረብን ሰው እንኳን ሊመልስልን ገና ሌላውም እንደገና ጉድ አድርጎናል… አስቀምጠነው የጠፋው ነገር እንኳን ሊገኝ “በተአምር ካልሆነ አይጠፋም” ያልነው ነገር እምጥ ይግባ ስምጥ ከተሰወረ ሰባተኛ ሳምንቱን ይዟል…ያመንነው ሰው እንኳን ‘ድንጋይ ተሸክሞ’ ይቅርታ ሊጠይቅ “ከሌላው ሰው ትንሽ ይሻላል…” ያልነው ሰው የሉሲፈር ታናሽ ወንድም ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ ይሄን ጊዜ አቤቱታችንን ይዘን ወደ አንድዬ ማንጋጠጥ ነው፡፡
 ምስኪን ሀበሻ፡− አንድዬ!…አንድዬ!…ምነው ጉሮሮዬ እስኪሰነጠቅ ብጮህ ዝም አልከኝ?
አንድዬ፡− አንተ በቀን አሥራ ሦስት ጊዜ ትጠራኛለህና በአሥራ ሦስት ዓመት አንዴ እንኳን የማይጠሩኝን ችላ ልበላቸው!
ምስኪን ሀበሻ፡− እንደ እሱ ማለቴ ሳይሆን…
አንድዬ፡− አሁን እሱን ተወውና ደግሞ ምን ሆንኩ ልትል መጣህ…
ምስኪን ሀበሻ፡− አንድዬ ስንትና ስንት ችግርና መከራ ሲደርስብኝ ‘ለበጎ ነው፣ እሱ ያስተካክለዋል…’ እያልኩ ምነው እንዲህ ከእነመኖሬም ረሳኸኝ!
አንድዬ፡− ደግሞ ምንድነው የማስተካክልልህ…
ምስኪን ሀበሻ፡− አንድዬ ምኑን ልበልህ! ስንቱን ቆጥሬ እጨርሰዋለሁ…
አንድዬ፡− ትሰማኛለህ…የምትለው ካለ በለኝ፣ ጊዜዬን አታባክን፡፡ የእኔን እገዛ የሚፈልጉ ብዙ ነገሮች ልመናና አቤቱታ በማያበዙ ፍጡራኔ ላይ እየተፈጠሩ ስለሆነ ከአንተ ጋር ስለፋለፍ ልውል አልችልም፡፡ አሁንማ ገና ድምጽህን ስሰማ…ከዚሀ ሰው የምገላገለው መቼ ነው እላለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡− አንድዬ አንተም ትማረራለህ!
አንድዬ፡− እንደውም መማረር ምን እንደሆነ ያወቅሁት በአንተና በመሰሎችህ ነው፣ አሁን ነገር አታብዛ፣ ወደ ጉዳይህ…
ምስኪን ሀበሻ፡− በዛ ሰሞን ሚስቴ ጥላኝ ስትሄድ ‘ለደግ ነው፣ ልብ ገዝታ ትመለሳለች’ ስል ይኸው ከሄደች ዘጠነኛ ወሯ፡፡ ከእኔ ጋር ብትሆን እኮ የመጀመሪያ ልጃችንን እንወልድ ነበር…
አንድዬ፡− ወይ ጉድ እና…ጥላህ የሄደችው እሷ፣ እኔ ምን ላድርግህ?
ምስኪን ሀበሻ፡− አይደለማ አንድዬ…የዛን ጊዜ እኮ ‘ለደግ ነው፣ እሱ እንደወሰዳት እሱ ይመልሳታል’ ስል እንኳን አልሰማኸኝም?
አንድዬ፡− አልሰማሁህም፣ ለነገሩ ‘እሱ ነው የወሰደኝ፣ እሱ ይመልሰኛል ብላህ ነበር እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡− እንደ እሱ እንኳን አላለችኝም….
አንድዬ፡− እና በገዛ ፍላጎቷ የሄደችውን ሴት የምመልሰው እኔ ምን ቤት ነኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡− ቢሆንም አንድዬ…ደግሞ በዛ ሰሞን ‘በሰበብ አስባብ ከሥራ ትቀራለህ፣ ትጠጣለህ፣ ከሠራተኛ ጋር አትግባባም፣’ ብለው ከሥራ ሲያግዱኝ…‘ለደግ ነው፣ እሱ የተሻለ ደሞዝ የሚገኝበት ሥራ ሊያስገባኝ ቢፈልግ ነው…’ አልኩ፡፡ ይኸው ብጠብቅ፣ ብጠብቅ እንኳን ሌላ ሥራ ላገኝ እገዳው ቀርቶ አንደኛውን ከሥራ አባረሩኝ፡፡
አንድዬ፡− እና ከሥራ ያስቀረሁህ እኔ ነኝ! አንተ ስትጠጣ አረቄህን ስቀዳልህ የነበርኩት እኔ ነኝ! ከምትሠራቸው ሰዎች ጋር ተበጣበጥ ብዬ የላኩህ እኔ ነኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡− አንድዬ ኧረ እንደሱ አላልኩም…
አንድዬ፡− አልክ እንጂ…በሰበብ አስባቡ አንተ በቀረኸው፣ አረቄህን ስታንቃርር ሥራ በበደልከው፣ ከትንሹም ከትልቁም በተናከስከው እየተመላላስክ በሬን  የምትደበድበው ለምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡− አንድዬ በቃ ጭርሱን ትተኸኛል ማለት ነው…እኔን ምስኪን ፍጡርህን ረስተኸኛል ማለት ነው!
አንድዬ፡− በአንተ ቤት ልቤን ማራራትህ ነው…ለመሆኑ ደግሞ ሌላ ‘ለደግ ነው’ ብለህ ቀረብኝ የምትለው ነገር አለ?
ምስኪን ሀበሻ፡− አለ እንጂ አንድዬ…አለ እንጂ…በዛ ሰሞን ታናሽ እህቴ ከዓረብ አገር ተጠርዛ ስትመጣ ‘ለደግ ነው፣ እሱ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ሊልካት ፈልጎ ነው’ ብዬ ብጠብቅ፣ ብጠብቅ አይደለም አሜሪካ ልትሄድ ከተማ ውስጥ ስትዞር ለምትውለው እኔ የታክሲው ወጪ ገደለኝ፡
አንድዬ፡− ቆየኝማ…እኔ ከዓረብ አገር ወደ አሜሪካ የምወስዳት ሰው አዘዋዋሪ ነኝ! ደላላ ነኝ!...
ምስኪን ሀበሻ፡− ኧረ አንድዬ ይቅር ይበልህ…ይቅርታ ራስህን ይቅር በል! እኔ እንደሱ አልኩ!
አንድዬ፡− እኔ እኮ ከእናንተ ጋር ብዙ ማውራት የማልፈልገው አስተሳሰቤን በእናንተ አእምሮ እኩል እንዳትቀርጹት ነው፡፡ ለችግሮቻችሁ ሁሉ እኮ እኔን ጥፋተኛ እያደረጋችሁኝ ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡− ኧረ አንድዬ…በጭራሽ!
አንድዬ፡− ታዲያ እንቅፋት በመታችሁ ቁጥር ‘ለበጎ ነው፣ እሱ ያስተካክለዋል’ ከማለት አካሄዳችሁን አታስተካክሉም! የጠፋባችሁን ነገር ራሳችሁ ፈልጋችሁ አታገኙም!…የተበላችሁትን ገንዘብ ራሳችሁ አታስመልሱም! የሄደችባችሁን ሚስት ራሳችሁ አትመልሱም!
ምስኪን ሀበሻ፡− አንተ እያለህ አንድዬ…አንተ እያለህ!
አንድዬ፡− ስማኝ… ይልቁንም ነገር ባበላሻችሁ ቁጥር “ለበጎ ነው፣ እሱ ያስተካክለዋል…” እያላችሁ ጊዜያችሁን ከምታባክኑ ወገባችሁን ጠበቅ አድርጋችሁ መፍትሄ ፈልጉ፡፡ እናማ  ሌት ከቀን በረባውም፣ ባልረባውም በሬን ለሚያንኳኩት ንገራቸው… “ለበጎ ነው…” የምትሉት ነገር እኔ ዘንድ አይደርስም፡፡ ወይንም በእናንተ አነጋገር የእኔ ሶፍትዌር “ለበጎ ነው…” የሚለውን ነገር አያነበውም፡፡ (አንድዬ በትንሹ ይስቃል)  ይኸው ምን አልኩ… እንደ እናንተው ልታደርጉኝ ምንም አልቀራችሁ፡፡ በል ደህና ሰንብት፡፡

Read 6511 times