Saturday, 05 December 2015 08:57

የሌሊት ጀግና ባሌ ነው፤ ትላለች የሌባ ሚስት

Written by 
Rate this item
(28 votes)

     ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አቴናዊና አንድ ቲቤታዊ መንገድ ላይ ይገናኛሉ። ከዚያም ውይይት ማድረግ ጀመሩ፡፡ መንገደኞች ትንሽም ይሁን ትልቅ ነገር ማንሳታቸው የተለመደ ነው፡፡ የተለያዩ ጉዳዮችን ካነሱ በኋላ ስለጀግኖች ወሬ ጀመሩ፡፡ ሁለቱም የየራሳቸውን ጀግኖች ማወደስ ያዙ፡፡
አቴናዊው፤
“የእኔን አገር ከተማ ጀግኖች የሚያክል ማንም የለም” አለ፡፡
ቲቤታዊው፤
“ኧረ አፍ አውጥተህ እንዲህ ያለ ድፍረት አትናገር፤ ቲቤት ምን የመሳሰሉ ጀግኖች ያፈራች ከተማ መሆኗን አለማወቅህ ገርሞኛል” ይላል፡፡
አቴናዊው፤
“የጀግና ልክ አታቅም ማለት ነው፡፡ ቴሲየስን የሚያክል ጀግና ያለን ነን እኛ፡፡”
ቲቤታዊው፤
“ሒርኩለስን የሚያክል ጀግና በዓለም ላይ እንዳልነበረ በታሪክ የተመሰከረ ነው። በአማልክቱ ዘንድ ትልቁን ሥፍራ የተሰጠው ጀግና ነው፡፡”
አቴናዊው፤
“ቴሲየስ ይህ ነው የማይባል ሀብት ያለውና ሔርኩለስን ሳይቀር አገልጋዩ ማድረግ የቻለ ነበር፡፡”
ይህን ሲል ሙግቱ ሚዛን አነሳ፡፡ እንደ ብዙዎቹ አቴናውያን አንደበተ ርቱዕና አሳማኝ ነው፡፡
ቲቤታዊው በክርክሩ የተሸነፈ መሆኑነ አውቆ በመከፋት፤
“ይሁን፡፡ መንገድህ የራስህ ነው፡፡ እኔ ተስፋ እማደርገው ጀግናዎቻችን በእኛ የተናደዱ ለታ፤ አቴናውያን የሄርኩለስ ንዴት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ቲቤታውያን ደግሞ ቴሲየስ የተናደደ ለታ የእሱን ሥቃይ ይቀበላሉ፡፡
*        *       *
ዕጣ ፈንታችን በጀግና መሪዎች ንዴትና ትኩሳት ላይ የተጣለ ከሆነ ህዝቦች እየተመራን ሳይሆን እየተነዳን ነው ማለት ነው፡፡ መሪዎች፤ ኃላፊዎችና አመራሮች ስሜታቸውን የሚቆጣጠሩ ሆደሰፊነታቸውን ያስመሰከሩ፣ ሁኔታዎችን በጥሞና አይተው የሚፈርዱ መሆን አለባቸው፡፡ ከባለሙያዎች ጋር መክረው፣ ዘክረው የሚተገብሩት ተግባር ፍሬው አመርቂ ይሆናል፡፡ ፍርድ ሁሉ የብቻዬ ነው፤ ሁሉን ወሳኝ እኔ ነኝ ማለት ውሎ አድሮ ብሶትን፣ ምሬትንና በቀልን እንጂ ዲሞክራሲያዊ ትሩፋትን አያስገኝም፡፡ የምናጭደው የዘራነውን ነው! የዘራነውን ብቻ ነው!
ለራስህ ታማኝ ሁን፡፡ ያኔ ሌላውን ሰው አትዋሽም (To thine own self be true. Thou canst be false to any man) ይለናል ሼክስፒር፡፡ ለራሱ ታማኝ የሆነ ሰው ልበ - ሙሉ የሆነ ሰው ነው፡፡ ልበ - ንፁህም የሆነ ሰው ነው! ለራስ ታማኝ መሆን ከሥልጣን መባለግ ያድናል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን ከሙስና ራስን ለማዳን ይጠቅማል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን ሌሎችን በወገን፣ በጎሣ፣ በዘር፣ በሃይማኖት ነጥሎ ከማየትና ከመበደል ሙሉ ልቦናን ይሰጣል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን ሌሎችን ላለመጠራጠርና በራስ መተማመንን ያበለፅጋል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን መማርንና መመራመርን ስለሚያበረታታ፤ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” የሚለውን ብሂል፣ በወጉና በቅጡ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ ለራስ ታማኝ መሆን መልካም አስተዳደርን በሀቅ እንድንረዳ፣ በሀቅም እንድንተገብር ያግዘናል! ለራስ ታማኝ መሆን ለህግ የበላይነት ታማኝ እንድንሆን ያደርገናል! በመጨረሻም ለራስ ታማኝ መሆን ለሀገር ታማኝ እንድንሆን በሩን ይከፍትልናል!
አገራችን ወደፊት ትጓዝ ዘንድ በራሳቸው የሚተማመኑ ጎበዛዝት ያስፈልጓታል! እኒያ ጎበዛዝት ከአሁኑ ትውልድ የሚፈልቁ ናቸው፡፡ ይህ ትውልድ በትምህርት፣ በዕውቀት እና በጥበብ የለማና የዳበረ መሆን አለበት፡፡ በሀገር ፍቅር የበለፀገ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ትሁት ግብረገብነት ወሳኝ ነው፡፡ ግብረገብነት በተለይ ዛሬ ለሀገር ወሳኝ ነው! “የጠፋው በግ” ግብረ ገብነት ነው! ለዚህ መንግሥት፣ ህዝብ፣ ቤተሰብ፣ ት/ቤቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ሁሎችም መተባበር ወቅታዊም፣ ታሪካዊም ርብርብ ያሻሉ፡፡! የዛሬው ጥሪያችን ግብረገብነት ያለው ሀቀኛ ትውልድ መፍጠር ነው!
“የኔ ቀበሌ፣ የኔ ክፍለ ከተማ፣ የኔ ክልል፣ የኔ ከተማ፣ የኔ ብሔር - ብሔረሰብ ጀግና ነው” ማለት ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን እያደረግሁ ነው ብሎ ራስን መፈተሽ ብቻ ነው ሀገራችንን ከገባችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ የሚያወጣት፡፡ የራስን ሰፈር ብቻ የተሻለ ለማድረግ ማሰብ ለዲሞክራሲ ሩቅ ነው። ትምክህትም ሆነ ጥበት ዞሮ ዞሮ የጥፋት መፈልፈያ ነው፡፡ ይህን ማረም “የሌሊት ጀግና ባሌ ነው፣ ትላለች የሌባ ሚስት” የሚለውን ተረት ማወቅ ነው!

Read 11270 times