Saturday, 05 December 2015 08:55

መንግሥት፣ ማስተር ፕላኑን ካልሰረዘ፣ ሰላማዊ ሰልፍ እጠራለሁ” - ኦፌኮ

Written by 
Rate this item
(47 votes)

“ማስተር ፕላኑ ልማትን ያሻሽላል፤ በረብሻ የተሳተፉ ይከሰሳሉ” - መንግሥት

     “የአዲስ አበባና የፊኒፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን” ላይ፣ ሰሞኑን በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች  በተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ከፖሊስ ጋር ግጭት ተፈጥሮ፣ ሶስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ የክልሉ ፖሊስ በበኩሉ፤ በረብሻው የተሳተፉ ሰዎች ይከሰሳሉ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እጅ አለበት ብሏል፡፡
አምና ተመሳሳይ ግጭትና ተቃውሞ ተፈጥሮ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ “ማስተር ፕላኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ በዙሪያው የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞችን እንዲጠቀለል የሚያደርግ ነው፤” የሚለው ተቃውሞ ከሰሞኑ እንደገና ተሰንዝሯል፡፡ “የከተሞቹ የአስተዳደር መዋቅር በማስተር ፕላኑ አይቀየርም” የሚለው መንግስት በበኩሉ፤ መሰረተ ልማትን በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል ነው ሲል ቆይቷል፡፡
“የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ በዙሪያው ወዳሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች እየሰፋ መጥቷል” በማለት የሚከራከረው ኦፌኮ፤ “ማስተር ፕላኑን አንቀበልም፤ መሬታችን አጥንታችን ነው፤ አንነቀልም” በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች (ግንጪ፣ ደንቢዶሎ፣ ዲላላ፣ ወሊሶ፣ መደወላቡ፣ ሀረማያ፣ አይራ ጉይሶና በሌሎችም) ለተነሳው የተማሪዎች  ተቃውሞ፤ መንግስት ሰላማዊ ምላሽ መስጠት አለበት የሚለው ኦፌኮ፤ እየደረሰ ላለው ጉዳት መንግስት ኃላፊነቱን ይወስዳል ብሏል፡፡
እስር፣ ድብደባና ግድያ እየተፈጸመ፣ መሆኑን በማውገዝ፤ መንግሥት ይህን ድርጊት በአስቸኳይ ማቆም አለበት ብሏል- ኦፌኮ፡፡ “የአዲስ አበባ ወሰን፤ ከ1987 ዓ.ም በፊት  ወደነበረበት መመለስ አለበት፤ ከወሰን አልፈው የተከናወኑ ግንባታዎች በሙሉ በኦሮሚያ ክልል ስር መተዳደር አለባቸው” ሲልም ፓርቲው ጠይቋል፡፡ የከተሞች ፕላን የፌደራል መንግስት ጉዳይ አይደለም ያለው ኦፌኮ፤ ማስተር ፕላኑ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ይጻረራል ብሏል፡፡  
ለልማት ተብሎ ከመሬታቸው የሚነሱ ገበሬዎች የህንፃዎች ጠባቂ እየሆኑ ነው ያሉት የኦፌኮ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ገበሬዎቹ የባለሀብትነት ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡  
ዓለም ባንክ ማስተር ፕላኑን መደገፍ የለበትም ያለው ኦፌኮ፤ ባንኩ እጁን ያንሳ ሲል ጠይቋል፡፡ የፈረንሳይዋ ሊዮን ከተማ አስተዳደር ለማስተር ፕላኑ ድጋፍ በመስጠትም አሁን ለተፈጠረው ችግር አስተዋጽኦ ስላደረገ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል ብሏል - ኦፌኮ፡፡  
የመንግስት በደልና ግፍ ካልቆመ፣ የአገሪቱን ሰላምና አንድነት ስጋት ላይ ይጥላል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ መንግስት ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንደሚገደድ ተናግረዋል፡
“በአዲስ አበባ ዙሪያ፣  በኦሮሚያ ላይ ሰፊ የመሬት እና የባህል ወረራ ተካሂዷል  ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ከ25 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ አካባቢ የነበሩ 28  የገበሬ ማህበራት ዛሬ የሉም ብለዋል፡፡ መንግስት በርካሽ የካሳ ክፍያ ከገበሬዎች መሬት እየወሰደ  በሚሊዮን ብሮች በጨረታ ይሸጣል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ሱሉልታ አካባቢ ገበሬዎች በ50 ሺህ ብር ካሳ ይፈናቀላል ብለዋል፡፡
ሰኞ እለት በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ከፖሊስ ጋር በተነሳ ግጭት በርካታ ተማሪዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ትምህርት ተስተጓጉሎ ሰንብቷል፡፡  ዩኒቨርስቲው በበኩሉ፣  በተቃውሞ ምክንያት ትምህርት ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቋረጠና የግቢው ሁኔታ እንደተረጋጋ ገልጿል፡፡
ተቃውሞው በበርካታ ከተሞች በሚገኙ ዩንቨርስቲዎችና ት/ቤቶች የተስፋፋ ሲሆን ፣ በአንዳንዶቹ  አካባቢዎችም  ነዋሪዎች እንደተሣተፉበት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር በበኩሉ፤ በረብሻው የሰው ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን በመግለፅ ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ማስተር ፕላኑ የፌደራል ስርአቱን አይጥስም ያለው መስተዳድሩ፤ የኦሮሚያ መሬትንም ቆርሶ ለሌላ አካል አይሰጥም ብሏል፡፡  ሁከት የሚሹ ሃይሎች፤ ለማስተር ፕላኑ የተሣሳተ ትርጉም ሰጥተውታል፣ በዚህም ለጠፋው ህይወትና ለወደመው ንብረት ተጠያቂ ናቸው ብሏል መስተዳድሩ ፡፡
ባለፈው አመት በዩንቨርስቲዎችና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ማስተር ፕላኑን ተመሳሳይ ተቃውሞ ተቀስቅሶ፤ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት 10 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡

Read 12762 times