Saturday, 05 December 2015 08:53

በአዋሣ ሪፈራል ሆስፒታል መብራት በመቋረጡ 3 ህሙማን ህይወታቸው አለፈ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(12 votes)

       በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ መብራት ለሀያ ሰዓታት ያህል በመቋረጡ ምክንያት በፅኑ ህክምና ክፍል (ICU) ውስጥ የነበሩ ሦስት ህሙማን ለሞት ተዳረጉ፡፡
ህዳር 20 ምሽት ላይ ለ20 ሰዓታት መብራት ተቋርጦ በመቆየቱና የሆስፒታሉ ጀነሬተር ተበላሽቶ በመቀመጡ የተነሳ በፅኑ ህክምና ክፍል የነበሩ አንዲት ወላድ እናትና ሁለት ሌሎች ህሙማን ህይወታቸው እንዳለፈ ምንጮች ገልፀዋል፡፡
ከይርጋለም ከተማ ወደ ሆስፒታሉ ሪፈር ተደርጋ የመጣችውና ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የደም ግፊት ህመም ሳቢያ ወደ ፅኑ ህክምና ክፍል የገባችው እናትና ሁለቱ በፅኑ ህክምና ክፍል ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩት ህሙማን በራሳቸው መተንፈስ የማይችሉ በመሆኑ፣ በመሳሪያዎች እገዛ ድጋፍ እየተደረገላቸው ህክምናቸውን ሲከታተሉ ነበር፡፡ ሆኖም ድንገት መብራት ተቋርጦ በመቅረቱ ህሙማኑ ህይወታቸው አልፏል፡፡ የሆስፒታሉ ጄነሬተር ተበላሽቶ ስለነበር መተካት አልተቻለም ተብሏል፡፡ መብራት መጥፋቱን ተከትሎ የቀዶ ህክምና ሊደረግላቸው የነበሩ ህሙማን ቀጠሮአቸው ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡
በዕለቱ የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ መረጃ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የሆስፒታሉ ዋና ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ክንፈ ለማን ወክለው ሆስፒታሉን በማስተዳደር ላይ የሚገኙት ዶ/ር አብይ ሚካኤል፤ ስለሁኔታው ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
በአካባቢው በትልቅነቱ የሚታወቀው የአዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት በርካታ የአሰራር ችግሮች እንዳሉበት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የሆስፒታሉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ህዝቡን እያገለገሉ አይደለም ያሉት ምንጮች፤ በጥብቅ (ጥኑ) ህሙማን ክፍል ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በተለያዩ ከባድ የጤና ችግሮች የተያዙ ህሙማን ክትትል የሚደረግላቸው በነርሶችና በተማሪ ሀኪሞች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡  

Read 5023 times