Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 February 2012 10:33

ፓርላማው የኑሮ ውድነት immunity አለው እንዴ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“አኬልዳማ” የውግዘት ጋጋታ የወለደው ነው ተባለ …

የሊዝ አዋጁ ችግር የለውም፤ ካድሬዎች ማስረዳት

ስላልቻሉ ነው (በአቅም ማነስ)

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአልበምና የኮሜዲ ድርቅ ክፉኛ አጥቅቶናል፡፡ በሌላ አነጋገር ደስታ ርቆናል፡፡ አንዳንዶች አልበሙም ኮሜዲውም ደስታውም የራቀን በኑሮ ውድነቱና በዋጋ ግሽበቱ የተነሳ ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በሊዝ አዋጁ፣ በፀረ ሽብርተኝነት ህጉ፣ በፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ያሳብባሉ (ጠ/ሚኒስትሩ ማጭበርበርያ ናት ብለዋል!) በነገራችን ላይ ከአልበሙ በቀር ሌላው ሁሉ በፓርላማ በሽበሽ ነው፡፡ በተለይ ኮሜዲውና ሳቁ!! ባለፈው ማክሰኞ የም/ቤት አባላት በሳቅ ሲፈርሱ አላያችሁም? ፓርላማ ሳቅና ደስታ ካለ እኮ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት የለም ማለት ነው፡፡ (ፓርላማው የኑሮ ውድነት immunity አለው እንዴ?)

እኔ የምለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሚለው የኢትዮጵያ ፓርላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ሊተካ አይችልም እንዴ? (የኑሮ ውድነት immunity እናገኝ ይሆናል ብዬ እኮ ነው!) እውነቴን ነዋ! ሁለት በደልማ አንችልም … ሳቅም አጥተን ኑሮም ተወዶብን … በምን ሃጢያታችን ነው! አንድ ጥያቄ አለችኝ፡፡ የፓርላማ አባላት የሚስቁት ለራሳቸው ነው ወይስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ? ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ? ሲስቁ ነገሩ አስቋቸው ነው ወይስ ጠ/ሚኒስትሩ ደስ እንዲላቸው? ማለቴ ነው፡፡ በእርግጥ ጠ/ሚኒስትሩ እንኳንስ የኢህአዴግን አባላት ተቃዋሚዎችንም ፍርፍር አድርጐ የማሳቅ ችሎታ እንዳላቸው እንኳን እኔ ተቃዋሚዎችም አይክዱትም (እኔ ከሁለቱም ጐራ ስለሌለሁበት ነው) ለነገሩ ፖለቲካን እንደ ኤሌክትሪክ በሩቁ የሚሉ አንዳንድ “ገለልተኛ ዜጐችም” የጠ/ሚኒስትሩን የፓርላማ ንግግር እንደ ኮሜዲ ፊልም በጉጉት እንደሚጠብቁት በጥናት ላይ ያልተመሰረተ ምልከታዬ (Observation ለማለት ነው) ይጠቁማል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ማታ ኢቴቪ ጠ/ሚኒስትሩ፤ በነጋታው ረቡዕ የ6 ወር ሪፖርታቸውን እንደሚያቀርቡ ሲያስተዋውቅ የቅርብ ወዳጄ ምን አለ መሰላችሁ? “ነገ ትንሽ እንስቃለና … ሳቅ ናፍቆኝ ነበር” ሲያሾፍ እንዳይመስላችሁ … ወዳጄን በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አድናቂ ነው፡፡ የሚገርማችሁ ደግም ፖለቲካ ሲጠላ ለጉድ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩን አድንቆ ፖለቲካን መጥላት እርስ በርስ የሚቃረኑ ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ ወዳጄ ግን መልስ አለው “እኔ የምወደው የጠ/ሚኒስትሩን ፖለቲካ አይደለም፤ የኮሜዲ ጥበባቸውን ነው … ለኮሜዲ እኮ ነው የተፈጠሩት!” እያለ የአድናቆት መዓቱን ያዥጐደጉዳል፡፡ ኧረ ሰውየው ፖለቲከኛ ናቸው ብላችሁ ብትከራከሩም… ወዳጄ ግን ክርክራችሁን መስሚያ ጆሮ የለውም፡፡ ለሱ ጠ/ሚኒስትሩ ፖለቲከኛ ሳይሆኑ የኪነጥበብ ሰው ናቸው (ኮሜዲያን!) ፔሬድ!!

እኔና ሌሎች ጓደኞቼ ተሰባስበን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ስንጨዋወት ከመካከላችን አንደኛው እንዲህ የሚል ሃሳብ ሰነዘረ “ጠ/ሚኒስትሩ የሚናገሩትን ሁሉ በኮሜዲ ዘውግ መመደብ የኮሜዲን ሀሁ ካለማወቅ የሚመጣ ችግር ነው … ባይሆን አዲስ ስያሜ ብንፈጥርለት ይሻላል …”

“እንዴት ያለ?” አልኩት፡፡

“ፖልሜዲ!” አለ - ጓደኛችን፡፡

ይሄ ጓደኛችን ከፖለቲካ “ፖል” ከኮሜዲ ደግሞ “ሜዲ” የሚሉትን ቃላት ወስዶ በማጣመር (Coinage ይሉታል) ነው “ፖልሜዲ”ን የፈጠረው፡፡ ትርጓሜውም የፖለቲካ ኮሜዲ እንደማለት ነው - ጓደኛችን እንደነገረን፡፡

አንድ የሥራ ባልደረባዬ ደግሞ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ ስናወጋ “መሌ ንግግር የሚዋጣለት ውጥረት ውስጥ ሲሆን ነው … አስተውላችሁ ከሆነ ሲወጣጠር እኮ ነው ፓርላማውን ሳቅ በሳቅ የሚያደርገው” አለኝ፡፡ የሥራ ባልደረባዬን ድምዳሜ ለመቀበል አንድም እሳቸው ራሳቸውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ አሊያም ደግም መጠነኛ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ እውነቱን ለመናገር የአሁኑ የም/ቤት አባላት (የኢህአዴግ አባላት ማለትም ይቻላል) ፈጣሪ አትደበሩ ሲላቸው አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ (የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን) ልኮላቸው ነው እንጂ ይሄ ሁሉ ሳቅና መዝናናት አይኖርም ነበር፡፡ አያችሁ ፓርላማ በሳቅ እንዲሞላና ነፍስ እንዲዘራ ሁለት ነገሮች መሟላት አለባቸው - ጠ/ሚኒስትሩና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት (አንድም ቢሆኑ) ሁለቱ ካሉ ሳቅ አለ፡፡ የተቀሩት አባላት ሚናቸው ብዙም አይደለም፡፡ ለምን ብትሉ? የእነሱ ሚና መሳቅ ብቻ ነዋ! ይሄን ደግም በኢፌክት መሙላት ይቻላል፡፡ ልብ አድርጉ! አሁን የምናወራው ስለ ፖለቲካ ሚና አይደለም፡፡ የም/ቤቱ አባላት በፓርላማ ስላላቸው የህዝብ ተወካይነት ሚናም አይደለም፡፡ ጨዋታችን ስለ “ፖልሜዲ” ነው፡፡ እናም የአውራው ፓርቲ ተወካዮች በፖለቲካ ኮሜዲው ውስጥ የተሰጣቸው ሚና ፓርላማውን በሳቅ ማጀብ ብቻ ነው እያልኳችሁ ነው፡፡ እኔን ካላመናችሁኝ በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት የተከበሩ አቶ ግርማ፣ ስለ ፓርላማው ሳቅ ተጠይቀው የመለሱትን እንደ ማስረጃ አቀርባለሁ፡- “ጠ/ሚኒስትሩ በየ6ወሩ አንዴ እየመጡ ቢያስቋቸው ምንም ክፋት የለውም፤ የተመረጡት ለመሳቅ ከሆነ … እንደምታዩኝ እኔ ቁጭ ብዬ የተመረጥኩበትን ዓላማ ሰርቼ ነው የምወጣው” (ይሄ ፓልሜዲ ሳይሆን ፖለቲካዊ ስላቅ ነው!)

በነገራችን ላይ “የፓርላማው ኮሜዲ” የሚል ምርጥ ኮሜዲ ፊልም በቅርቡ ለመስራት አቅጃለሁና ይሄን የፈጠራ ሃሳብ መኮረጅ (ቃል በቃል መቅዳት) በኮፒራይት ህግ እንደሚያስቀጣ ከወዲሁ ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ እንደተናገሩት የፀረሽብር ህጉ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ቃል በቃል የተቀዳ ነው - ኮማ ሳይቀር!! ይሄ ግን በፊልም ስራ ስለማያዋጣ እንዳትሳሳቱ ለማለት ያህል ነው፡፡ ይሄን የኩረጃ ነገር ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን አንድነት ፓርቲም እንደሚደግፈው ሰሞኑን የተከበሩ አቶ ግርማ መናገራቸውን ሰምቻለሁ፡፡ “እኛ መኮረጅ አንፈራም፤ አሪፍ ከሆነ ከኢህአዴግም እንኮርጃለን” ያሉት አቶ ግርማ፤ ኩረጃ መጥፎ የሚሆነው ት/ቤት ነው ብለዋል፡፡

ሰሞኑን ከኩረጃ ጋር በተገናኘ በኢቴቪ አንድ ግለሰብ (ሃላፊ መሆን አለባቸው) ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ በት/ቤት ውስጥ ኩረጃን እንደ ሙስና በመቁጠር ተማሪዎች እንዳይኮራረጁ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ት/ቤቶችን ከኩረጃ ነፃ የማድረግ ዘመቻ ነው ብለዋል - ግለሰቡ፡፡ ለነገሩ አማራጭ ጠፍቶ ነው እንጂ የፀረ ሽብር አዋጁንም ሆነ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡን የዳበረ የዲሞክራሲ ልምድ ካላቸው አገራት ከምንኮርጅ የራሳችንን ኦሪጂናል አዋጅና ደንብ ብናወጣ ይሻል ነበር፡፡ (ጠ/ሚኒስትሩ የፀረ ሽብር አዋጁ አቀራረፁም አፈፃፀሙም ምርጥ ነው - Best Practice ማለታቸውን አልዘነጋሁትም!) ግን ደግም አስተውላችሁት ከሆነ ከትላልቆቹ አገራት ተኮርጀዋል የተባሉት አዋጆችና ደንቦች በሙሉ ውግዘት እየወረደባቸው ነው (ችግር አለ ማለት ነው!) ጠ/ሚኒስትሩ የፀረ ሽብር ህጉን ለምን ከእነ አሜሪካ እንደኮረጁ (እንደቀዱ) ሲያስረዱ ከሰማችሁ ግን ችግራቸውን ትረዱላችኋላችሁ (እንደ እኔ)፡፡ እሳቸው እንዳሉት ገና አዲስ አዋጅ ሲወጣ ምዕራባውያኑ ዲሞክራሲን የሚገድብ፣ ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ፣ መብትና ነፃነትና የሚያፍን … ወዘተ እያሉ ያብጠለጥሉታል፡፡ ስለዚህ የራሳቸውን አዋጅ ቃል በቃል ኮማ ሳይቀር ቀድተን አመጣን፡፡ (አፋቸውን ለማዘጋት ማለት ነው)

ክፋቱ ግን ምዕራባውያኑ የራሳቸው ህግ ተቀድቶ መምጣቱን አላወቁም መለሰኝ … የፀረ ሽብር ህጉ የወጣ ሰሞን የተቃዋሚ ፖለቲከኞችንና የጋዜጠኞችን መብትና ነፃነት የሚገድብ ነው… ሲሉ የተፈራውን ውግዘት አዝንበውበታል፡፡ የውጭዎቹስ እሺ … የሚገርመው የአገራችን ተቃዋሚዎች ትችት ነው፡፡ ህጉ ከአሜሪካ እንደተቀዳ (እንደተኮረጀ) እያወቁ መቃወማቸው ምን ይባላል? (በዚያ ላይ ኩረጃ አንፈራም እያሉ እኮ ነው!) ባለፈው ሳምንት ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ይበልጥ ትኩረቴን የሳቡት ሁለት አጃንዳዎች ናቸው፡፡ አቶ መለስ፤ “ከፍተኛ ጫጫታ” አስነስቷል ያሉት የሊዝ አዋጁና የኢቴቪ “አኬልዳማ” ዶክመንታሪ ፊልም  ናቸው፡፡ በተለይ የሊዝ አዋጁን በተመለከተ በእኔ በኩል የነበረው “ብዥታ” ጠርቶልኛል - ከእሳቸው ማብራሪያ በኋላ፡፡ ለካስ ብዥታዬን ያባባሰብኝ የኢህአዴግ ካድሬዎች ማብራሪያ የመስጠት አቅም አናሳ መሆኑ ነበር፡፡ አሁን የሊዝ አዋጁ የሚጐዳው ተራ ተርታውን ህዝብ (ድሃውን) ሳይሆን ሁለት ዓይነት ሌቦችን ብቻ እንደሆነ ገብቶኛል - የመንግስትና የግል ሌቦችን ማለት ነው፡፡ እስከ ዛሬ የኢህአዴግ ካድሬዎችና ከፍተኛ ሃላፊዎች በቲቪ በሊዝ ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ ሰምቻለሁ፡፡ ከአንዳቸውም ግን እንደ ጠ/ሚኒስትሩ ዓይነት አጥጋቢ ማብራሪያ አላገኘሁም (የአቅም ማነስ ጣጣ ብየዋለሁ!) የሊዝ አዋጁ የመንግስትና የግል ሌቦችንም ቢሆን ለመጉዳት ታስቦ እንዳልወጣ የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ዓላማው በሊዝ ከሚገኘው ገቢ ለነዋሪው የቁጠባ ቤቶችን መስራት እንደሆነ አስረድተዋል (ድሃ-ተኮር ቤቶችን ማለታቸው ነው)

በነገራችን ላይ በሊዝ አዋጁ ዙሪያ ብዥታ አለብን ለሚሉ ግለሰቦች፣ ተቃዋሚዎች፣ ልማታዊና ኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች … ወዘተ የማብራሪያ አገልግሎት መስጠት እንደጀመርኩ ስገልፅ በደስታ ነው፡፡ (ለግማሽ ሰዓት ማብራሪያ 500 ብር ብቻ!) የኢህአዴግ አባላትም ቢሆኑ ችግር የለብኝም፡፡ መክፈል እስከቻሉ ድረስ ከማብራራት ወደ ኋላ አልልም፡፡ ኢህአዴግ ከህብረተሰቡ አድናቆት አትርፌበታለሁ ያለውን (ተቃዋሚዎች ህገ መንግስት የሚጥስ ያሉትን) በኢቴቪ የተዘጋጀ ዶክመንታሪ ፊልም (አኬልዳማ ማለቴ ነው) በተመለከተ ጠ/ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያም አርክቶኛል፡፡ “አኬልዳማ” የውግዘት ጋጋታ የወለደው ነው - ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ እንደገለፁት፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በተያዙ ማግስት መንግስት ከፍ/ቤት ውጭ ወንጀለኛ ተብሎ ተወገዘ ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ፊልሙ ራስን ለመከላከል ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው ብለዋል፡፡ (ብሶት የወለደው እንደማለት!)

በነገራችን ላይ ስለ “አኬልዳማ”ም የማብራሪያ አገልግሎት በቅርቡ እንደምጀምር እገልፃለሁ (በነፃ ግን አይደለም!)

ትዝ ይላችኋል በቅርቡ በሽብርተኝነት ዙሪያ ያቀረብኩት መጣጥፍ? “ሽብርተኛ እየተባባላችሁ ስትፈራረጁ ድምፃችሁን ዝቅ አድርጉ!” የሚል ነበር - ዓለም ሁሉ ሰምቶ ኢትዮጵያን ከዳር እስከዳር በሽብርተኝነት እንዳይፈርጅና የፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ እንዳይከፍትብን በመፍራት የፃፍኩት ነው፡፡ የፈራሁት አልቀረም፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ ወደ ኡጋንዳ ለመሄድ ቪዛ ጠይቆ ኤምባሲው በስልክ ይጠራውና “ጋዜጠኞች ሽብርተኞች ናችሁ ይባላል?” የሚል ጥያቄ ቀረበለት፡፡ (ባለቤቱ ያላከበረውን አሞሌ ጐረቤት ድንጋይ ነው ይለዋል … የሚለው ተረት ትዝ አለኝ)

በመጨረሻ ጠ/ሚኒስትሩ በየ6 ወሩ በፓርላማው የሚያቀርቡት ሪፖርት “Melese Show” ቢባል የሚል ሃሳብ ለፓርላማው ሳይሆን ለህዝብ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ህዝብ ሃሳቤን ከደገፈው ፓርላማው ፈቀደም አልፈቀደም ስያሜው የፀና ይሆናል፡፡ (ፓርላማው የእኛ እኮ ነው - የህዝብ!)

ከሰሞኑ የፓርላማ ሾው ያስደሰቱኝን፣ ያስገረሙኝንና ያሳዘኑኝን ጥቂት ነጥቦች ጠቅሼ የ”ፖለቲካ በፈገግታ ሾው”ን አጠናቅቃለሁ፡፡

ከአሸባሪው ይልቅ ጠላታችን ሙሰኛው ነው (ያስደመመኝ!)

ሽብርተኞች ይሄን ነገር ትተነዋል፤ ተሳክተናል ካሉ ነፃ ናቸው (ያልጠበቅኩት!)

እኛ እኮ በቀል አይደለም አጀንዳችን፤ ዓላማው መማማር ነው (ያስገረመኝ!)

የመንግስትና የግል ሌቦች የዘመቱበት የሊዝ አዋጅ (የጠበቅኩት!)

የመድረክ አመራር ውስጥ መቶ በመቶ ሽብርተኞች መሆናቸውን የምናውቃቸው ግለሰቦች አሉ… (ያስደነገጠኝ)

ውድ አንባቢያን:- ለጊዜው ያስደሰተኝን ነጥብ ስለዘነጋሁት ለሚቀጥለው ሳምንት ለማስታወስ እሞክራለሁ፡

 

 

Read 3403 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:39