Saturday, 28 November 2015 14:30

አለማችን ዘንድሮ በታሪክ ከፍተኛውን ሙቀት አስተናግዳለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   እስካለፈው ጥቅምት በነበሩት አስራ ሁለት ወራት የተመዘገበው አለማቀፍ አማካይ የሙቀት መጠን በታሪክ ከፍተኛው እንደሆነና ሊጠናቀቅ አንድ ወር ብቻ የቀረው የፈረንጆች አመት 2015 በአለማችን እጅግ ሞቃቱ አመት ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአለም የሜቲሪዮሎጂ ድርጅት ማስታወቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ከ2011 እስከ 2015 የነበረው የአምስት አመታት ጊዜ፣ በአለማችን ታሪክ እጅግ ከፍተኛው ሙቀት የተመዘገበበት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ የድርጅቱ ተመራማሪዎች የዘንድሮው የአለማችን አማካይ የሙቀት መጠን ከፍተኛ ሊሆን የቻለው የሰው ልጅ የሚፈጥረው የአለም የሙቀት መጠን በመጨመሩና የኤል ኒኖ ክስተት ባደረሱት የከፋ ተጽዕኖ ሳቢያ ነው ማለታቸውን ጠቁሟል። በተገባደደው የፈረንጆች ዓመት በአለማችን የበካይ ጋዞች ልቀት መጠን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ያለው የአለም የሜቲሪዮሎጂ ድርጅት፣ የውቅያኖሶች የሙቀት መጠንም እስካሁን ከተመዘገቡት መጠኖች ከፍተኛው ደረጃ ላይ እንደደረሰ አስታውቋል፡፡
በዘንድሮው አመት በርካታ የአለማችን አገራት በታሪካቸው ከፍተኛውን የሙቀት መጠን አስተናግደዋል ያለው ዘገባው፣ ቻይና ባለፉት 12 ወራት አይታው የማታውቀውን ሙቀት እንዳሳተናገደች ጠቁሞ፣ አፍሪካም በአመቱ ከፍተኛውን ሙቀት እንዳስመዘገበች አውስቷል፡፡

Read 2927 times