Saturday, 28 November 2015 14:30

ካፒታል ሆቴልና ስፓ “ግራንድ ሌግዠሪ” ለመሆን እየተጋ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

    በአዲስ አበባ ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ከተቀዳጁት ሆቴሎች አንዱ ካፒታል ሆቴልና ስፓ ሲሆን  ሆቴሉ ይሄን ስኬቱን ለማስተዋወቅና ለግራንድ ሌግዠሪነት ያሳጨውን በጅምር ላይ የነበረ ዘመናዊ ስፓ አጠናቆ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ካፒታል ሆቴል እንዴት ለባለ 5 ኮከብ ደረጃ እንደበቃ፣ የሠራተኞች አያያዝና ሥልጠና እንዲሁም በቅርቡ ለማካሄድ ባቀደው ዝግጅት ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከሆቴሉ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ከአቶ አሰፋ ገበየ ጋር አጭር ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡

    እስቲ ጨዋታችንን ከሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ እንጀምር----  
በካፒታል ሆቴልና ስፓ ስራ የጀመርኩት ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ በሆቴል ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ አለኝ፡፡ በተጨማሪም ስራዬን ሊደግፉ የሚችሉ አጫጭር ኮርሶችንና የአመራር ስልጠናዎችን ወስጃለሁ፡፡ ከዚህ ሌላ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት የማስተርስ ተማሪ ነኝ፡፡
ካፒታል ሆቴልና ስፓ ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ይሰጣል?
ሥራ የጀመረው በፈረንጆቹ 2013 ግንቦት ወር ላይ ነው፡፡ ሆቴሉ 114 የመኝታ ክፍሎችና 128 አልጋዎች አሉት፡፡ ሁለት ዋና ዋና ሬስቶራንቶች፣ ሁለት ባሮችና አንድ ኮፊሾፕ አለው፤ የካፍቴሪያ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ ዘጠኝ ያህል ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ያሉት ሲሆን ትንሹ 20 ሰው፣ ትልቁ 650 ሰው የመያዝ አቅም አላቸው፡፡ ካፒታል ሆቴልና ስፓ፤ የስፓ አገልግሎት ከመስጠቱም በላይ በሀገሪቱ ትልቁን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዕከል  ይዟል፡፡ ሆቴሉ ውሃ ዋና፣ በጣም ትልቅ የዘመኑን የጂም መሳሪያዎች የያዘ ጂም ሀውስ ያለው ሲሆን አንድ የወንድ፣ አንድ የሴት የውበት ሳሎኖችን ያካተተ ነው፡፡ 200 መኪኖችን በአንዴ የሚያስተናግድ፣ ከሆቴሉ ራቅ ብሎ የተሰራ የመኪና ማቆሚያ ቦታ አለው። በተጨማሪም የባንክ፣ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትና የስጦታ እቃ መሸጫ  ሱቆችም አሉት፡፡ አንድ እንግዳ በዚህ ሆቴል ውስጥ ምንም ፈልጎ የሚያጣው ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡
በቅርቡ የተሰጠውን የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት?
ይህንን የደረጃ ምደባ ሆቴላችን በጣም በጉጉት ሲጠብቀው የነበረው ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ሂደት የምናየው በሶስት መንገድ ነው፡፡ አንደኛ እንደ ድርጅት ባለቤት፣ ሁለተኛ እንደ አገርና ሶስተኛ እንደ ደንበኛ ማለቴ ነው። በነዚህ ምክንያቶች የደረጃ ምደባው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እናስብ ነበር፡፡ እንደ ደንበኛ ስናየው፣ ከዚህ በፊት የሆቴል ምደባ ደረጃ ባለመኖሩ ማንኛውም ሆቴል የሚገነባ ሰው፣ ደረጃዎቹን በአግባቡ ያሟላም አያሟላም በራሱ ፈቃድ የኮከብ ደረጃ  ይሰጡ ነበር፡፡ ይህም ለደንበኞች የትኛው ነው ጥሩ አገልግሎት የሚሰጠው የሚለውን ለመለየት አስቸጋሪ ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ ይህ የደረጃ ምደባ የደንበኞችን ጥያቄ በትክክል መልሷል። እንደ አገር ስናየው ደግሞ አገራችን አንፃራዊ ሰላም ያላት፣ በርካታ ዲፕሎማቶች የሚኖሩባት ናት፤በተለይ መዲናዋ የተባበሩት መንግስታት መ/ቤቶች በብዛት የሚገኙባት ናት፡፡
በዚህ የተነሳ በኮንፍረንስ ቱሪዝም በደንብ መስራትና መጠቀም ስንችል፣ የሆቴሎች ደረጃ በአግባቡ ባለመመደቡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትልልቅ ስብሰባዎችን በሀገራችን ለማካሄድ ሙሉ እምነት እንዳይኖራቸው ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ያንን ብዥታ የደረጃ ምደባው አጥርቷል ባይ ነኝ፡፡ እንደ ድርጅት ባለቤት፣ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አፍስሰን፣ አምስት ኮከብና ከዚያ በላይ ይሆናል ብለን አቅደን የገነባነው በመሆኑ፣ከማርኬቲንግ አንፃር ከገበያው ጋር ለመጣጣም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላደረገልን ምደባውን ወደነዋል፡፡ በውጤቱም ደስተኞች ነን… በዚህ መልኩ ነው የምገልፀው፡፡ በደረጃ አሰጣጡም ላይ አንዳንድ ጥያቄዎች እንዳይነሱ በማያሻማ ሁኔታ  የተባበሩት መንግስታት አለም አቀፍ የቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) የራሱን ከፍተኛ ባለሙያዎች ልኮ ምዘናው የተሰራ በመሆኑ፣ ውጤቱም ተገቢና ለጥርጥር ያልተጋለጠ ስለሆነ ደስተኞች ነን፡፡
ከላይ እስከ ታች ባልተለመደ መልኩ ሆቴሉ በኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች መደራጀቱ ይነገራል፡፡  በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ብቻ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት መስጠት አይከብድም? እስኪ ስለ ሰራተኞች ቅጥር፣ ስልጠና አሰጣጥ፣እድገትና የሰራተኞች አያያዝ ሥርዓታችሁ ይንገሩኝ?
  እኛ ከሌሎች ምናልባትም አለም አቀፍ ብራንድ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ ሆቴሎች ጋር ተወዳድረን የላቀ ውጤት ማምጣታችንን ለየት የሚያደርገው፣አንደኛ ሆቴሉ የተገነባው በኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከፅንሰ ሀሳብ ጀምሮ ግንባታውንና የማማከር ስራውንም ያካሄዱት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ግንባታው ከተጠናቀቀም በኋላ እስካሁኑ ሰዓት ድረስ ከተራ የስራ መደብ እስከ ከፍተኛ የማኔጅመንት ቦታ የተያዘው በኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ይህ ትልቁ የምንኮራበትና ለሌሎችም ምሳሌ የምንሆንበት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መጀመሪያ የሆቴል አገልግሎት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ኢትዮጵያዊያን አይችሉም እየተባለ እስካሁን የውጭ አገር ዜጎች ናቸው ሆቴል የሚመሩትና የውጭ ምግቦች የሚያበስሉት። በሌላው የስራ ዘርፍ ትልልቅ ባለሙያዎችና አዋቂዎች ያላት አገራችን፣ እንዴት በሆቴል ዘርፍ ብቃት የላቸውም ተብሎ እንደሚታሰብ አይገባኝም፡፡ እኛ ያንን አስተሳሰብ በመስበር ብቃት እንዳለን አሳይተናል፡፡ “እኛም እንችላለን” የሚል አቋም ያላቸው የሆቴሉ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የማነ ገ/ሥላሴ፤ ይህንን እውን አድርገውታል፡፡ በኢትዮጵያኖች ብቃት ላይ ምንም ጥርጥር ሳይኖራቸው፣ ያለንን የአመራር ብቃት እንድናሳይ አግዘውናል፤ ከልብ እናመሰግናቸዋለን፡፡
የሰራተኛ ቅጥር፣ የእድገትና የስልጠና አሰጣጥ አሰራራችሁ ምን ይመስላል?
የሰራተኛ ቅጥር ሁኔታችን እጅግ ስርዓት ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርፆለት የሚካሄድ ሲሆን ከመረጣው ጀምሮ የስልጠናው ሁኔታ፣ ሰራተኛውን የማነቃቃት ሂደት፣ የደሞዝ ፓኬጁ፣ ለሰራተኛው የሚሰጠው ጥቅማጥቅም ሁሉ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ የሚካሄድ ነው፡፡ በሆቴላችን ሰራተኛ ከአንዱ መደብ ወደ ሌላው መደብ በፍጥነት ያድጋል፡፡ አንድ ሰራተኛ በተመደበበት የስራ ቦታ ላይ ጥሩ የስራ አፈፃፀም ካለው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያድጋል፡፡ ይህ ሰራተኛውን የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ያደረገው ሲሆን አቅም ግንባታን በተመለከተ ሆቴላችን የራሱ የሆነ የስልጠናና ዴቨሎፕመንት ዲፓርትመንት ራሱን ችሎ ተቋቁሞለታል፤ የራሱም ማናጀር አለው፡፡ በዋናነት ለስራው የሚመጥን አስተሳሰብ ካለው፣ እውቀትና ክህሎቱን በስልጠናና ልማት ክፍሉ በኩል ሰጥተነው ይቀጠራል፡፡
ሥልጠናውን የሚሰጡት ባለሙያዎችስ ኢትዮጵያዊያን ናቸው?
አሰልጣኞቻችንም ሰልጣኞቻችንም ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ በእርግጥ ሁለት አይነት የአሰለጣጠን ሂደት አለ። በድርጅቱ ውስጥ ባሉ አሰልጣኞች የምናሰለጥናቸው አሉ። እንደየስልጠናው ባህሪ ለሌሎች ድርጅቶች ኮንትራት እየሰጠንም የምናሰለጥናቸው ሰራተኞች ይኖሩናል፡፡ ለምሳሌ ለዋና ማናጀሮችና ለቴሌ ኤክስፐርት የሚሰጡ ስልጠናዎችን በሌሎች ድርጅቶች እናሰለጥናለን።  ለምሳሌ ከሊደርሺፕ ኢንስቲትዩቶች ጋር ኮንትራት እንይዝና ያሰለጥኑልናል፡፡
ሆቴላችሁን ለባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ያበቁት መስፈርቶች ምንድን ናቸው?
በጣም ጥሩ፡፡ በUNWTO 12 ያህል የመመዘኛ ዋና ዋና ነጥቦች ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህ መሰረታዊ ነጥቦች በሆቴል ዘርፍ ለተሰማራ በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ነጥቦች ናቸው፡፡ እኛ እነዚህን 12 ነጥቦች በከፍተኛ ውጤት ነው ያለፍነው። እዚህ ወረቀት ላይ እንደምትመለከቺው (የነጥቦቹን አይነትና ያመጡትን ውጤት የያዘ ፋይል ነው) ይሄ በመዛኞቹ የተቀመጠ ነጥብ ነው፡፡ በመመዘኛው ከፍተኛ ውጤት አምጥተናል፡፡ ሴፍቲና ሴኩሪቲ በሚለው ነጥብ መቶ በመቶ ነው ያመጣነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ ካለው የደህንነት ስጋት አንፃር ስትመለከቺ፣የደህንነት ስጋትን የሚያስወግዱ ፋሲሊቲዎች በቤቱ ውስጥ አሉ ብለው ኤክስፐርቶቹ መቶ ፐርሰንት ነጥብ ሰጥተውናል። ይሄን ውጤት ያገኘነው ድርጅታችን ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ እነዚህን የደህንነት ፋሲሊቲዎች በማሟላቱ ነው። የህንፃውን ግንባታ ብትመለከቺ፣በሶስቱም አቅጣጫ የአደጋ ጊዜ መውጫ አለው፡፡ ይሄም ብቸኛ ያደርገናል። በመቀጠልም ኤክስፐርቶቹ “Staff facilities and training” በሚለው ነጥብ፣ከ140 የሰጡን 134 ነጥብ ነው፡፡ አጠቃላይ ውጤታችን ደግሞ 85.68 ሲሆን እስካሁን አንደኛ መሆናችንን ነው የምናውቀው፡፡
ጥናቱን የሰሩት ኤክስፐርቶች በማጠቃለያቸው፣ ስለ ሆቴላችን ቀጣዩን ሪፖርት አስቀምጠዋል፡- “The property is an indigenous hotel operated by highly qualified management and staff. It is an excellent example of 5 star Hotel with the potential to becoming a 5 star Grand Luxury”  በቀጣይ “Luxury” ለመሆን ማሟላት ያሉብንን ነገሮች ጠቁመውናል፤ይሄ አስተያየት እነሱን በትጋት እንድንሰራ ያነቃቃናል፡፡ ትልቅ ነጥብ ካስመዘገብንባቸው ውጤቶች አንዱ፣ በአገራችን ሰዎች መገንባቱና መመራቱ ነው፡፡ ያው ለ“ Grand Luxury” እጩ ነን ማለት እንችላለን፡፡
አንድ ሆቴል የግራንድ ሌግዠሪ ደረጃ የሚሰጠው ምን ምን ሲያሟላ ነው?  
በዝርዝር በተቀመጡት 12 ነጥቦች፣ 90 ከመቶና ከዚያ በላይ ያመጣ ነው ግራንድ ሌግዠሪ የሚባለው፤እኛም ወደዚያ ነጥብ ለመቅረብ ትንሽ ነው የቀረን፡፡ ከ80-90 ከመቶ ያለው አምስት ኮከብ ደረጃ ተሰጥቶታል። በነገራችን ላይ የደረጃ ምደባው ሲካሄድ፣ የነገርኩሽ ትልቁ ስፓችን ስራ አልጀመረም፡፡ ገና በመሟላት ላይ ነበር፡፡ እሱ ቢሟላ ኖሮ ግራንድ ሌግዠሪ ደረጃ እናገኝ ነበር፡፡ መዛኞቹ በመጨረሻው ሪፖርታቸው፣ “ስፓው ስራ ሲጀምር ግራንድ ሌግዠሪ ይሆናል፤ በሚቀጥለው ጉብኝታችን እናየዋለን” የሚል አስተያየት አስፍረዋል፡፡
አምስት ኮከብ ደረጃ ማግኘታችሁን አስመልክቶ፣ስኬቱን ለማብሰር አንድ ዝግጅት ማሰባችሁን ሰምቻለሁ፡፡ ስለሱ ሊነግሩኝ ይችላሉ?
በመሰረቱ የዚህን ስኬት ደስታ ማክበር የጀመርነው ከመስከረም አንስቶ ነው፤ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ማግኘታችንን በጭምጭምታ ከሰማን በኋላ ማለት ነው፡፡ ለሰራተኞች የምስጋናና የማነቃቂያ ስራ ስንሰራ ቆይተናል። አሁን በይፋ ውጤቱን ካወቅን በኋላ በመሰራት ላይ የነበረውንና ለግራንድ ሌግዠሪነት ያሳጨንን ስፓ በይፋ አስመርቀን ለመክፈትም ጭምር ነው እየተዘጋጀን ያለነው፡፡ ዝግጅቱ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይካሄዳል። በተጨማሪም ቀጣይ እቅዳችንን በይፋ ለማስተዋወቅ የተለያዩ ትልልቅ ዝግጅቶችን እያደረግን ነው፡፡ አምስት ኮከብ ካገኘን በኋላ ግራንድ ሌግዠሪ ለመሆን ቀን ከሌት እየሰራን እንገኛለን፡፡ 

Read 3019 times