Saturday, 28 November 2015 14:23

መልካም አድራጊው

Written by  ደራሲ ፡- ኦስካር ዋይልድ ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(9 votes)

መሽቷል፡፡ እሱም ብቻውን ነበር፡፡
እሱም በርቀት ተመለከተ፡፡ በግንብ የታጠረች ክብ ከተማም አየ፡፡ ወደ ከተማዋም አቀና፡፡
ወደ ከተማዋ በቀረበ ጊዜም ሶስት ድምፆች ሰማ፡፡ አንደኛውም፡- በፈንጠዚያ የሚዘሉ እግሮች ድምድምታ ነበረ፡፡ ሁለተኛውም፡- ከፍተኛ የሆነ የደስታ ማሽካካት ነበረ፡፡ ሶስተኛውም፡- ድብልቅልቁ የወጣ የዋሽንት ዝማሬ ነበረ፡፡ እሱም ቅጥሩን አንኳኳ፡፡ ከፈቱለትም፡፡
እሱም በፊቱ በእምነ-በረድ የተሠራ ቤትም ተመለከተ፡፡ ከቤቱም ፊት ለፊት በእምነ-በረድ የተሰሩ የሚያማምሩ አዕማድ ነበሩ፡፡ አዕማዱም ከአበቦችና ከሚያማምሩ ቅጠሎች በተሰሩ አክሊሎች ተጊጠዋል፡፡ በቤት ውስጥም፣ ከቤት ውጪም ከጥድ የተሰሩ ችቦዎች ይበራሉ፡፡ እሱም ወደ ቤት ገባ፡፡
እሱም በአንጸባራቂና በሚያምሩ የከበሩ ድንጋዮች የተለበጡ ሁለት ፅርሆች አልፎ ወደ መመገቢያ እልፍኝ ዘለቀ፡፡ በዚያም የተንጣለለ ሀምራዊ ሶፋ ላይ የተንፈላሰሰ፣ እራሱም ላይ ከቀይ ፅጌረዳዎች የተሰራ አክሊል የደፋ፣ ከናፍሩም በሚጠጣው ቀይ ወይን የቀሉ ወጣት አየ፡፡
እሱም ወደ ወጣቱ ቀረበ፡፡ ትከሻውንም ነካ አደረገው። እንዲህም ብሎ ጠየቀው፡-
“ስለምን እንዲህ አይነት ኑሮ ትኖራለህ?”
ወጣቱም ወደ ኋላው ዞሮ ተመለከተ፡፡ ማን እንደሆነም አወቀ፡፡ እንዲህም ብሎ መለሰ፡-
“በአንድ ወቅት ቆማጣ ነበርኩ፤ አንተም ፈወስከኝ፡፡ ከዚህስ ሌላ እንዴት ልኖር ይሆንልኛል?”
እሱም ከወጣቱ ቤትም ሄደ፡፡ ወደ መንገድም ወጣ፡፡
እሱም ጥቂት እንደሄደ ፊቷንና ልብስዋን ያቀለመች ሴት አየ፡፡ ጫማዎቿ በሉል ተንቆጥቁጠዋል፡፡ ከኋላዋም ለአደን እንደወጣ ሰው እያደባ የሚከተላት ጎረምሳ ነበረ። ጎረምሳውም ባለሁለት ቀለም ካባ ደርቧል፡፡ ሴቲቱም መልከኛ ናት፡፡ ጣኦትም ትመስል ነበረ፡፡ የጎረምሳውም አይኖች በመጎምጀት ተይዘው ያበራሉ፡፡
እሱም ጎረምሳውን ተከተለው፡፡ ቀርቦም እጁን ነካው። እንዲህም ብሎ ጠየቀው፡-
“ስለምን ይህቺን ሴት በእንዲህ አይነት መቋመጥ ትመለከታታለህ?”
ጎረምሳውም ዞሮ ተመለከተ፡፡ ማን እንደሆነም አወቀ፡፡ እንዲህም ብሎ መለሰ፡-
“እውር ነበርኩ፡፡ አንተም አይኖቼን አበራሀቸው፡፡ ታዲያ ምንስ ልመለከት ይሆንልኛል?”
እሱም ፈጥኖ ወደ ሴቲቱ ሄደ፡፡ ያቀለመችውን ልብሷንም ነካ፡፡ እንዲህም ብሎ ጠየቃት፡-
“ከሀጢአት መንገድ በቀር ሌላ የሚኬድበት መንገድ አታውቂምን?”
ሴቲቱም ዞራ ተመለከተች፡፡ ማን እንደሆነም አወቀች። ሳቀችም፡፡ እንዲህም ብላ መለሰች፡-
“በሀጢአት መንገድ እመላለስ ነበረ፡፡ አንተም ሀጢአቶቼን ይቅር አልከኝ፡፡ የሀጢአት መንገድ እጅግ ደስ ይላል፡፡ ታዲያ በየት መንገድ ልሄድ ይሆንልኛል?”
እሱም በከተማዋ አለፈ፡፡
በከተማዋም እያለፈ ሳለ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ የሚያለቅስ ወጣት አየ፡፡
እሱም ወደ ወጣቱ ሄደ፡፡ ከረዣዥም የተገመዱ ጸጉሮቹም አንዱን ዘለላ ነካ፡፡ እንዲህም ብሎ ጠየቀው፡-
“ስለምን ታለቅሳለህ?”
ወጣቱም ቀና ብሎ አየው፡፡ ማን እንደሆነም አወቀ፡፡ እንዲህም ብሎ መለሰ፡-
“ሞቼ ነበር፡፡ አንተም ከሙታን አስነሳኸኝ፡፡ ታዲያ ከማልቀስ ሌላ ምን ይሆንልኛል?”
(የእንግሊዝኛው ርዕስ፡- The Doer of Good)

Read 3172 times