Saturday, 28 November 2015 14:08

“የተበደርኩህ ሀያ ብር ይኸውልህ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(15 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሁለት ጓደኛሞች አብረው ሲሄዱ አንደኛው… “አንተ ሀያ ብሬን መልስልኝ…” ይለዋል፡፡ ጓደኝዬውም… “አሁን ስለሌለኝ ነው፣ ሰሞኑን እሰጥሀለሁ…” ሲል ይመልስለታል፡፡ ትንሽ እንደተጓዙም የሆነ ዘራፊ ይገጥማቸዋል፡፡
“ሁለትሽም ያለሽን ገንዘብ አንዲት ሳንቲም ሳትቀር ቁጭ አድርጊ!” ይላቸዋል፡፡
ሁለቱም የገንዘብ ቦርሳቸውን ያወጣሉ፡፡ ታዲያላችሁ…ያ የተበደረው ሰው ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው… ከቦርሳው ሀያ ብር ይመዝና ለጓደኛው እየሰጠው እየተቻኮለ… “የተበደርኩህ ሀያ ብር ይኸውልህ…” ብሎት ቁጭ አለ፡፡
እናማ… አይደለም አሥራ አንደኛው ሰዓት ቀርቦ፣ ገና ከማለዳው “የተበደርኩህ ሀያ ብር ይኸውልህ…” እያልን ‘አሳልፈን የምንሰጥ’ በዝተናል…ያውም በጥድፊያ!
የምር ግን…ጥድፊያ አልበዛባችሁም! በቃ…የሆነ ሰው ወይም ነገር ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ጥቂት ሴኮንዶች ቢያስፈልጉ ነው፡፡ ምን መሰላችሁ…አብዛኛውን ጊዜ ፍርዳችን…አለ አይደል…የሆነ ሰው ሽክ ብሎ ካየነው… “እባክህ ይሄኔ ብራይቡን እየጨረገደ ይሆናል…” ይባላል፡፡
እሷዬዋ ተጫዋችና ከሁሉም ጋር የምትግባባ ከሆነች… “ይሄኔ እኮ አንድ ቢራና አንድ ክትፎ ብትገዛላት የሦስት ወር ቅምጥ ልታደርጋት ትችላለህ፣” ልትባል ይችላል፡፡
እናላችሁ… “የተበደርኩህ ሀያ ብር ይኸውልህ…” አይነት ጥድፊያ በዝቷል፡፡
እግረ መንገዴን…የችኮላን ነገር ካነሳን… ከሩዋንዳ ጋር በነበረን ግጥሚያ ላይ በቀጥታ ሲተላለፉ የነበሩትን ፕሮግራሞች ስከታተል አንድ ሁለት ነገሮች ግራ ገቡኝ። በተደጋጋሚ “ኳሷን ተቆጣጥሯል…” አይነት ነገሮች ነበሩ፡፡ ክፋት ባይኖራቸውም ትንሽ ከኳስ ጋር እንዲህ አይነት ቃላት በተደጋጋሚ ሲነገሩ የሆነ የማይመች ነገር አለው፡፡ አንድ ቦታ ላይ ደግሞ ከጨዋታው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ… “በቁጥጥር ስር ውሏል…” የሚልም ነገር ሰምተናል፡፡ ደግሞላችሁ… የሩዋንዳን ደጋፊዎች መጀመሪያ ላይ… “የሩዋንዳ ኤምባሲ ደጋፊዎች…” የሚል አይነት ነገር አምልጣ ነበር፡፡
ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ለሁሉ ነገር እንጣደፋለን፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የፕሬሚየር ሊግ የኳስ ቀጥታ ስርጭቶች ላይ ‘ኮሜንታሮቻች’ን የሆነ የመጣደፍ ነገር አለባቸው፡፡ እናማ…ለውሳኔ የመቸኮል ነገር አለ፡፡ የእኛ ተጫዋች በወደቀ ቁጥር “ጥፋት ተሠርቷል…” የ‘እነሱ ተጫዋች’ በወደቀ ቁጥር “ሰዓት እያባከኑ ነው…” አይነት የጥድፊያ ውሳኔ አሪፍ አይደለም፡፡
የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር…ከዚህ በፊት እንዳነሳናት ‘የመልስ ውርወራ…’ ምን እንደሆነ እስከዛሬ የሚያስረዳን ሰው አላገኘንም፡፡ “የመስመር ውርወራ…” “የእጅ ውርወራ…” ምናምን የተባሉት ሀረጎች በ‘መተካካት’ ተገፍተው ‘ተጣሉ’ እንዴ!
እናላችሁ…በስፖርት ብቻ ሳይሆን ሚዲያ ላይ በብዙ ነገር… “የተበደርኩህ ሀያ ብር ይኸውልህ…” አይነት ጥድፊያ በዝቷል፡፡
እናማ…ስፖርት ጋዜጠኞቻችን በቀጥታ ስርጭት ስሜታዊነቱን ‘በቁጥጥር ስር’ አውሉትማ!
እሷዬዋ ጥቃት የማትቀበልና “ለምን?” “እንዴት?” ምናምን ማለት የምትወድ ከሆነች… ይሄኔ እኮ እሷ ብቅ ስትል የሰፈሩ ሰው ሁሉ በሩን ይቀረቅር ይሆናል… ይባልላታል፡፡
እሱዬው ከሆነ ‘ቦስ’ ጋር ሞቅ ያለ ሰላምታ ሲለዋወጥ ከታየ… “እኔ ይሄ ሰውዬ የባለስልጣኖች ጆሮ ጠቢ ይመስለኛል…” ይባላል፡፡
የሆነች እንትናዬ ወጥታ ወርዳም ሬስቱራንት ቢጤ ከከፈተች… “ይሄኔ የቦምብ ተራ ነጋዴ ጠብ አድርጋ ይሆናል…” ይባልለታል፡፡ በእርግጥ ‘የቦምብ ተራ ነጋዴ ጠብ አድርጋ’ ሊሆን ቢችልም (ቂ…ቂ…ቂ…) ቸኩሎ ውሳኔ ማስተላለፍ አሪፍ አይደለም፡፡   
እሱዬው በ‘ፋውንዴሽን’ም በምንም ‘ሀንድሰም’ ነገር ይሆናል እንበል፡፡ (አሀ…ልክ ነዋ…በፋውንዴሽን ምናምን ነገር የጾታ ልዩነት ቀርቷላ!) እናላችሁ… ይሄኔ ምን ይባላል… “ወጣት ሆኖ አይተኸው ነው። የእኔ ጌታ… ዕድሜውን በእንትኑ ጠቅጥቆ ነው…” ይባላል፡፡
እግረ መንገዴን…እሷዬዋ እሱን በሆነ ነገር አበሳጭተዋለች፡፡ እናላችሁ… እሱዬው “ሞልተው ለተረፉ እንትናዬዎች…” ምናምን ብሎ እንደ ‘መተበት’  ያደርገዋል፡፡
እሷዬዋም… “እግርህ እስኪነቃ ብትሄድ የእኔ አይነት ቆንጆ አታገኝም…” ትለዋለች፡፡ (ዕድሜ ለፋውንዴሽን! ቂ…ቂ…ቂ…)
ምን ብሎ ቢመልስላት ጥሩ ነው… “አስቀያሚ ከመሆንሽ የተነሳ ቢንቢ እንኳን ስትነድፍሽ ዓይኖቿን ጨፍና ነው፣” ብሏት አረፈ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የዕድሜ ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ…እኛ ዘንድ እንጃ እንጂ እነኚህ የሰማይ ስባሪ የሚያካክሉት ሀገሮች ጠበቆች ሂሳብ የሚጠይቁት በሰዓት ነው። ሠራን የሚሉበትን ሰዓት ይደምሩና ሂሳባቸውን ይናገራሉ፡፡ እናላችሁ… አንዱ ጠበቃ እንዲሁ ሲሠራ ቆይቶ ዓለምን ተሰናብቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይሄዳል፡፡ እዛም ሲደርስ… “ስህተት ተሠርቶ መሆን አለበት፡፡ “እንዴት ነው ስህተት የሚፈጠረው?” ተብሎ ይጠየቃል፡፡
“እኔ እኮ ለመሞት ገና ወጣት ነኝ፡፡ ሀምሳ አምስት ዓመቴ ብቻ ነው፣” ብሎ አቤቱታ ያቀርባል።
“ሀምሳ አምስት ዓመት አይደለህም፡፡ እኛ እንዳሰላነው ሰማንያ ሁለት ዓመት ሞልቶሀል…” ይሉታል፡፡
“እንዴት ብትደምሩት ነው ሰማንያ ሁለት የሚመጣው?” ብሎ ሲጠይቅ ምን መልስ ቢያገኝ ጥሩ ነው…
“ለደንበኞችህ ሠራሁባቸው ያልካቸውን ሰዓታት ብቻ እንኳን ስንደምር ሰማንያ ሁለት ዓመት ይመጣል…” ተባለላችሁና አረፈው፡፡
እናላችሁ…ምንም ነገር ላይ ለውሳኔ መቸኮል… አለ አይደል…ባህሪያችን ነገር እየሆነ ነው፡፡ አንድ ሀሳብ ስንሰጥ… “እስቲ ሀሳቡን እንመርምረው…” ከማለት ይልቅ…ደቂቃ እንኳን ሳይሞላ… “እንዲህ አይነት አስተያየት ከጀርባው ያዘለው ነገር አለ…” አይነት ‘የቀጥታ ቀይ ካርድ’ ይመዘዛል፡፡
እናማ…ነገሩ ሁሉ “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል” አይነት እየሆነ ተቸግረናል፡፡
ስሙኝማ…የሆነ የታወቀ ኮሜዲያን ነው አሉ። እናላችሁ… አንድ ቀን በማታ ሲሄድ ማጅራት መቺ ይገጥመውና ሽጉጥ ያወጣበታል፡፡ ታዲያላችሁ…
“ወይ ከገንዘብህ ወይ ከህይወትህ ምረጥ…” ይለዋል። ኮሜዲያኑም ለረጅም ጊዜ ምንም ሳይተነፍስ ቆየ፡፡ ማጅራት መቺው…
“ወይ ከገንዘብህ፣ ወይ ከህይወትህ…” ሲል እንደገና ይጮህበታል፡፡
ኮሜዲያኑ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አትቸኩል…እያሰብኩበት ነው፡፡” እንዲህ አይነትም… “እያሰብኩበት ነው…” አለ!
እናማ…“የተበደርኩህ ሀያ ብር ይኸውልህ…” አይነት ጥድፊያ አሪፍ አይደለም፡፡
የምር ግን…በችኮላ አስተያየት መስጠት ብዙዎቻችን… አለ አይደል…ልብ ለልብ ተገናኝተን እንዳናወራ እያደረገን ነው፡፡ አሀ…የምንጠቀምባቸውን ቃላትና ሀረጎች መምረጡ ራሱን የቻለ መከራ ነዋ! እንደ አካሄድ ካልን በዚህ ወገን እንሆናለን…“ድንቄም ሁለት ዲጂት…” ካልን በዛ ወገን እንሆናለን፡፡ እናላችሁ…የቃላት አጠቃቀማችን ታይቶ የሚተላለፍብን ውሳኔ ፈጣን ነው፡፡
እናማ…“የተበደርኩህ ሀያ ብር ይኸውልህ…” አይነት ጥድፊያ አሪፍ አይደለም፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ትምህርት ቤት ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… ልጁ ለልጅቷ ምን ይላታል…
“ዳይሬክተራችን ነገር የማይገባው ደደብ ሰው ነው፣” ይላታል፡፡
እሷም “እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቃለህ?” ትለዋለች፡፡
እሱም፣ “አላውቅም…” ይላታል፡፡
እሷም፣ “እኔ የዳይሬክተሩ ልጅ ነኝ…” ትለዋለች።
እሱዬውም፣ “እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቂያለሽ?” ይላታል፡፡
እሷም “አላውቅም…” ትለዋለች፡፡ ይሄኔ ልጁ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው…
“ደህና ሁኚ…” ብሎ ሄደ፡፡
“የተበደርኩህ ሀያ ብር ይኸውልህ…” አይነት ጥድፊያን ወደዚያ አሽቀንጥሮ ‘ውሳኔ’ ከመስጠታችን በፊት ለደቂቃዎች እንኳን ቢያቅተን… አለ አይደል… ለሴኮንዶች እንድናስብ የሚያስችለንን ሶፍትዌር አንድዬ ይጫልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6153 times