Saturday, 28 November 2015 14:04

“የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች ቃለምልልስ የመስጠት ግዴታ የለባቸውም” - ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

- የምስጢራዊነት ባህል መረጃ አሰጣጥ ላይ ትልቅ ችግር ሆኗል
- ጋዜጠኛው መረጃ ለማግኘት ልመና ውስጥ እየገባ ነው

   በመረጃ ነፃነትና የፕሬስ አዋጅ አፈፃፀም ላይ ሰሞኑን በተደረገ ውይይት፤ የመንግሥት አስፈፃሚዎች የግንዛቤ ችግር እንዳለባቸው ጥናቶች የጠቆሙ ሲሆን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ በአዋጁ መሰረት የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ቃለ ምልልስ የመስጠት ግዴታ የለባቸውም ብለዋል፡፡
ጋዜጠኞች መረጃ እንዳያወጡ ማስፈራራት፣ ጋዜጠኞች መረጃ ቢያወጡም ባያወጡም ምንም ተፅዕኖ እንደማይፈጥሩ አድርጎ መቁጠር፣ የመንግሥት ጋዜጠኞች የኛ ልጆች ናቸው ማለትና ሌላውን የመንግሥት ጠላት አድርጎ መቁጠር በጥናት ከተለዩ ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡
የመንግሥት መረጃ ሰጪ አካላት ስር የሰደደ ሚስጥራዊነት አላቸው፤ በህጉ የተቀመጡ አንዳንድ ክልከላዎችን ያለ አግባብ እየተጠቀሙባቸው ነው ተብሏል - በጥናቱ፡፡
ከመንግሥት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ስለዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ምንም ግንዛቤ የሌላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ 80 በመቶዎቹም ቢሆን ያላቸው ግንዛቤ መጠነኛ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁሩ ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ ገልፀዋል፡፡
በጥናቱ መሰረት የዜጎች መረጃ የማግኘት መብትን በተመለከተ ጋዜጠኞች ሙሉ ለሙሉ ግንዛቤ ያላቸው ሲሆን ከመንግሥት ኃላፊዎች ደግሞ ሙሉ ግንዛቤ ያለው አንድም የመንግሥት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የለም ተብሏል፡፡ አስተያየት ሰጪዎችም፤ የመንግሥት ኃላፊዎች ሙሉ ለሙሉ ብቁ ሳይሆኑ አዋጁን እንዴት ለማስፈፀም ይታሰባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አዋጁ ከወጣ 3 ዓመት ቢሆነውም አንድም የመንግሥት ኃላፊ ሙሉ እውቀት የለውም መባሉ ይሄን ያህል ጊዜ ምን ሲሰራ ተከረመ የሚል ጥያቄም አስነስቷል፡፡
መረጃን ለማግኘት እንቅፋት ናቸው ተብለው በጥናቱ ከተጠቆሙት መካከልም የቀጠሮ መብዛትና መጉላላት፣ የዝምድና አሰራሮች፣ የተደራጀ መረጃ የሚሰጥ አካል አለመኖር፣ ደንበኞችን በአግባቡ ያለማስተናገድ፣ ያለአግባብ የሚጠየቁ ስጦታዎች (ጥቅሞች) እና መረጃን ለማግኘት የሚጠየቅ ክፍያ ከፍተኛ መሆን የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ባቀረቡት ጥናትም ከዶ/ር ደረጃ ጥናት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ውጤቶች እንደተገኙ ተጠቁሟል፡፡
የመንግስት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች “እኔ እያለሁ እንዴት ወደ በላይ ኃላፊ ጋዜጠኛ ይሄዳል” በሚል ስሜት ጋዜጠኞች ከሚመለከተው ኃላፊ ተገቢውን መረጃ እንዳያገኙ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆመው ጥናቱ፤ ለራስ ዝናና እውቅና መሮጥ እንዲሁም የህዝብ ግንኙነት ስራን በትክክል አለመረዳትና የፕሮፓጋንዳ ስራ አድርጎ መቁጠር ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ ተገቢ ልምድና እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች በቦታው አለማስቀመጥም ሌላው ዋነኛ ችግር ነው ተብሏል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ የመረጃ ነፃነት አዋጁ በተፈለገው አግባብ አለመተግበር፣ መንግስት ሊያሳካቸው የሚፈልጋቸውን አላማዎች አደጋ ላይ የጣለ ነው ብለዋል። በመረጃ አሰጣጥ ላይ የሚታየው ዋና ችግር የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቁርጠኛ አለመሆን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የሚስጥራዊነት ባህልና የተቋምን ገጽታ ብቻ ለመጠበቅ መንቀሳቀስም ትልቁ ችግር ነው ብለዋል። “ጋዜጠኛው መረጃ ለማግኘት ልመና ውስጥ እየገባ ነው፤ መረጃ ማግኘት የችሮታ ጉዳይ ሣይሆን ሰብአዊና ህገመንግስታዊ መብት ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪዎች፤ በጋዜጠኛው ላይ መረጃን በማግኘት በኩል የተጣለበት ማንኛውም አይነት ስውር እቀባ ሊነሳ ይገባዋል ብለዋል፡፡ በመንግሥት የህዝብ ግንኙነት ቦታ የሚመደቡ ኃላፊዎችም ለሙያው ተስማሚ የሆነ የትምሀርት ዝግጅት ያላቸው አለመሆኑ ችግር መፈጠሩም ከተሳታፊዎች ተጠቁሟል፡፡
የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በውይይቱ የተዛቡ ግንዛቤዎች ያሏቸውን ጠቅሰዋል። የመረጃ ነፃነት ሲባል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ወይም ሚኒስትሮች ኢንተርቪው ከማድረግ መብት ጋር ተያይዞ መታየት የለበትም በማለትም የስራ ሃላፊዎች (ሚኒስትሮች) ኢንተርቪው የመደረግ ግዴታም እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ አንድን የስራ ሃላፊ በአዋጁ ላይ ተመስርቶ ኢንተርቪው አልሠጠኝም ብሎ መውቀስና መክሰስ አይችልም፤ የመንግስት ተቋማት ያለባቸው ግዴታ በመንግስት እጅ ያለ የተሰናዳ መረጃን መስጠት ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ከመንግስት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ሙያዊ ብቃት ጋር በተያያዘ ለተሰነዘሩ አስተያየቶች ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ “ሁሉም ሙያዊ ብቃት አላቸው ብሎ መደምደም ባይቻልም የኮሙኒኬሽን ባለሙያው የግዴታ በጋዜጠኝነት ወይም በቋንቋና ስነጽሑፍ የተመረቀ መሆን አለበት የሚለው ተቀባይነት የለውም፤ ዋናው የመንግስትን አላማ ማሳካቱ ነው” ብለዋል፡፡

Read 5471 times