Saturday, 28 November 2015 09:19

አቤቱታ በማቅረባችን የበቀል እርምጃ እየተወሰደብን ነው” - ተፈናቃዮች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

የሚሰማን የመንግሥት አካል አጥተናል ብለዋል

    የብሄር ማፈናቀልና ሰብአዊ በደል አድርሰዋል በሚል የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ይፋ ባደረጋቸው የኦሮሚያና አፋር ወረዳ የመንግስት ኃላፊዎች ላይ እርምጃ ባለመወሰዱ ነዋሪዎች ለበቀል ጥቃት እንደተጋለጡና 71 አባወራዎች ከቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ ከትናንት በስቲያ የአካባቢው ተጎጂዎች ለጋዜጠኞችና ለዲፕሎማቶች አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ፣ አሎ ቀበሌ፣ በአንድ የኦሮሞ ተወላጅ ግድያ ምክንያት በአንድ አማራ ተወላጅ ላይ ግድያ፣ በ10 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል አካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም 99 የሳርና 22 የቆርቆሮ ቤቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ተከትሎ፣ ሰመጉ በነሐሴ 2007 ዓ.ም “ብሄር ተኮር ማፈናቀልና እንግልት በአስቸኳይ ይቁም!” የሚል መግለጫ በማውጣቱ፤ “ለምን መረጃ ሰጣችሁ” በሚል በተጎጂዎች ላይ ይበልጥ ጥቃት መፈፀሙን የጉባኤው አመራሮች ጠቁመዋል፡፡
በደላቸውን ለማስረዳት ሰሞኑን ከወረዳው ወደ አዲስ አበባ ከመጡት ተጎጂዎች መካከል የሚሊሻ ኮማንደር የነበረው አለሙ አሰፋ፤ የወረዳ ፖሊስ ኃላፊዎችና አመራሮች፤ “እኛን የትም ሂዳችሁ ብትከሱ ምንም አታመጡም” እያሉ ነጋ ጠባ ድብደባ፣ ወከባና እንግልት ሲበዛባቸው አዋሳኝ ወደሆነው የደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ጥገኝነት ለመጠየቅ መገደዳቸውን አስረድቷል፡፡
“እኛ ክልል ገብታችሁ ማረስ አትችሉም” ተብለናል ያሉት  ተፈናቃዮቹ፤ አብዛኞቹም ሞዴል ገበሬዎች የነበሩና ራሳቸውን በአጭር ጊዜ ቀይረው  ብዙ ንብረት ያፈሩ እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
አቤቱታችንን ይዘን ያልረገጥነው የመንግስት ተቋም የለም፤ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ድረስ ሄደናል የሚሉት አቤት ባዮቹ፤ “መንግሥት ችግራችንን የማያዳምጠን ከሆነ፣ ወዴት ሄደን ለማን አቤት እንበል?” ሲሉ አማረዋል፡፡
በሌላ በኩል በአፋር ክልል በአሳይታ ወረዳ፣ በዋሙሌ ቀበሌ የተከሰተን የቴምር ዛፍ ጭፍጨፋ አስመልክቶ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲጣራላቸው ለሰመጉ አቤት ማለታቸውን ተከትሎ፣ ሰመጉ ባለሙያ ልኮ ካጣራ በኋላ “በልማት ስም በዜጎች ላይ የሚፈፀም ማፈናቀልና የንብረት ማውደም በአስቸኳይ ይቁም” በሚል ነሐሴ 26 ቀን 2007 መግለጫ አውጥቶ፣ ለመንግሥት አካላት ቢያደርስም ነዋሪዎቹ እስካሁን መፍትሄ አላገኙም ተብሏል፡፡
ከወረዳው የመጡ አቤቱታ አቅራቢዎችም፤ ለረጅም ዘመናት በአካባቢው ሲኖሩ ለቤት መስሪያነት፣ ለምግብነትና የገንዘብ ምንጭ በመሆን ልጆቻቸውን ያሳደጉበት የቴምር ዛፎቻቸው ተጨፍጭፈው፣ ሀብት ንብረታቸው ወድሞ፣ በአካባቢው መኖር የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡
የሰመጉ አመራሮች በበኩላቸው፤ በየጊዜው በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሪፖርቶች እንደሚያወጡ ጠቁመው፤ ከመንግስት ወገን ሪፖርቶቹን ተመልክቶ እርምጃ የመውሰዱ ጉዳይ አናሳ መሆኑን ገልፀዋል፡፡  

Read 3414 times