Saturday, 28 November 2015 09:18

“ቢያንስ ጉቦ አትስጡ፤ ሰጪ ከሌለ ተቀባይ የለም”

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(3 votes)

ጠ/ሚኒስትሩና የባህርዳር ነዋሪዎች በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ተወያዩ

   ባለፈው ሳምንት የብአዴን 35ኛ አመት የምስረታ በአል በተከበረባት የባህርዳር ከተማ ከነዋሪዎች ጋር በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ችግሩ በመንግሥት ብቻ የሚፈታ ሳይሆን የነዋሪዎችን ርብርብ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጠንከር ብለው እንደሚታዩ የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትም በብዛት እንደሚስተዋል ገልፀዋል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫው ብዙ ቢሆንም ህብረተሰቡ ቢያንስ ጉቦ ባለመስጠት የራሱን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል  ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ በበኩላቸው፤ “ሰጪ ከሌለ ተቀባይ የለም” ብለዋል።
በከተማዋ ኢንዱስትሪ በሚፈለገው ደረጃ እየተስፋፋ አይደለም በሚል ላነሱት ቅሬታ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ፤ የግል ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ እንዳይገቡ ከሚያደርጓቸው ችግሮች አንዱ የመልካም አስተዳደር ጉድለት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህንን በጋራ ጥረት መፍታቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢንዱስትሪ ልፋት የሚጠይቅ ዘርፍ በመሆኑ ባለሀብቱ በአቋራጭ ወደሚከብርባቸው ሌሎች ዘርፎች እያዘነበለ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ይህንንም ለመፍታት ከባለሀብቱ ጋር እጅና ጓንት ሆነን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ባህርዳር ለቱሪዝም የተመቸች ከተማ ብትሆንም በቱሪዝሙ በኩል በቂ ስራዎች እየተሰሩ እንዳልሆነ የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ለአብነትም ጢስ አባይን ጠቅሰዋል፡፡ “የቱሪስት መስህብ የሆኑ ቦታዎች መሰረተ ልማት የተሟሉላቸው አይደሉም፤ ዘርፉ ካለው አገራዊ ጠቀሜታ አንፃር መንግስት በቀጣይ ምን ሊሰራ አስቧል” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አገሪቷ በ2015 ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ተብላ መሸለሟን ያስታወሱት አቶ ኃይለማርያም፤ እንደ አገር የቱሪዝም እድገቱን ለማስቀጠል የሚሰሩ በርካታ ስራዎች እንዳሉ  የግል ባለሀብቱና የከተማው ነዋሪ የየድርሻውን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል - ከአባይ ማዶና በመሃል ከተማ ካለው ድልድይ በተጨማሪ ሌላ ድልድይ የመገንባቱ ስራ የሚታሰብበት እንደሆነም በመጠቆም፡
መንግስት የጀመራቸውን የልማት ስራዎች አጠናክሮ በመቀጠል በተለይ በሃይል አቅርቦት ዙሪያ የሃይል ምንጮችን የማስፋትና ወደ ስራ የማስገባት ስራዎችን እያከናወነ በመሆኑ፣ የሃይል አቅርቦት ችግር ከተማዋን እንደማያሰጋት ጠ/ሚኒስትሩ ለነዋሪዎቹ አስረድተዋል፡፡   

Read 1987 times