Saturday, 28 November 2015 09:16

ሕብረት ባንክ ከ358 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

    ሕብረት ባንክ አ.ማ ባለፈው ሳምንት የባንኩን የባለአክሲዮኖች 17ኛ መደበኛ ጠቅላላና 9ኛ ድንገተኛ ጉባኤ በሂልተን ሆቴል ያካሄደ ሲሆን ከታክስ በፊት ከ358 ሚ. ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ባለፈው ሰኔ 30 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ ከሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎት ዘርፎች አጠቃላይ ገቢው 1.3 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ከታክስ በፊትና ከፕሮቪድ በኋላ 358.2 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን፣ ሙሉ በሙሉ በተከፈለ አክሲዮን ላይ የ25 በመቶ የትርፍ ክፍያ እንዲደረግ የዲሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡን የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ፋሲል አስናቀ ገልጸዋል፡፡  የበጀት ዓመቱ በርካታ ሥራዎች የሰሩበትና አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡበት እንደሆነ የጠቀሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በተቀማጭ ገንዘብና በብድር በሴክተሩ ያላቸውን የገበያ ድርሻ ማሳደጋቸውን፣ በርካታ አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈታቸውን፣ የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግን እጅግ በማዘመን ማቅረባቸውንና በአገሪቷ ለመጀመሪያ ጊዜ የወኪል ባንክ አገልግሎት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕብር ኦንላይን በሚል ብራድ ስምና ሕብረ ሞባይል በሚል ስያሜ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዘንድሮ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ፣ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ጋር ሲነፃፀር የ28.1 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ 43.4 በመቶ ጨምሮ ወጪው 975.7 ሚሊዮን ብር መድረሱንና ጭማሪው አሳሳቢ መሆኑን፣ የባንኩ ተቀማጭ 11.8 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ከአምናው ጋር ሲወዳደር የ27 በመቶ ብልጫ በማሳየት 2.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመልክተዋል፡፡
ባንኩ፣ በበጀት ዓመቱ በአዲስ አበባና ከመዲናዋ ውጪ ባሉ ከተሞች 30 አዳዲስ ቅርንጫፎችና 3 ንዑስ ቅርንጫፎ የከፈተ ሲሆን፣ 18ቱ ከአዲስ አበባ ውጪ የተከፈቱ ናቸው፡፡ የባንኩ የሰው ኃይልም 2,921 መድረሱ ታውቋል፡፡  


Read 1639 times