አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ጁን 30, 2015 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከታክስ በኋላ 64.33 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን፣ ትርፉም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ10.5 በመቶ ብልጫ እንዳለውና የአንድ ዕጣ የተጣራ ትርፍ ክፍያ 272 ብር መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ አስታወቁ፡፡
ሊቀመንበሩ አቶ ቀነአ ዳባ፤ በሂልተን ሆቴል በተካሄደው 21ኛው የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ የበጀት ዓመቱን ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ኩባንያው፣ ሕይወት ነክ ባልሆኑ አጠቃላይ የኢንሹራንስ ዘርፍ 404.3 ሚሊዮን ብር አረቦን መሰብሰቡን፣ ይህም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የ13.7 በመቶ ብልጫ እንዳለው፣ በሕይወት ዘርፍ ኢንሹራንስ ደግሞ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ 10 በመቶ ብልጫ ያለው 40 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
ይህ ገቢ ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር ሲነፃፀር ለተከታታይ ሦስት ዓመት ቀዳሚ ያደርገዋል ያሉት አቶ ቀነአ፤ በአጠቃላይ ኢንሹራንስ ዘርፍ ከአምናው ጋር ሲተያይ ከአምናው 12.25 በመቶ ብልጫ ያለው 189.5 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈፀማቸውን ገልፀዋል፡፡
በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከኡራኤል ቤተክርስቲያን ወደ ቦሌ መድኃኒዓለም በሚወስደው መንገድ ላይ ሁለት ቤዝመንትና ግራውንድ ወለሉን ሳይጨምር የገዙት ባለሰባት ፎቅ ሕንፃ በመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ነው፡፡ ቃሊቲ አካባቢ የገዙት 2107 ካ.ሜ ቦታ ለመጋዘንና ጋራዥ ምቹ ሲሆን ለህንፃውና ለመሬቱ ግዢ 13 ሚሊዮን ብር ወጪ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ኩባንያው በደሴና በዓለም ገና ከተሞች ሁለት አዳዲስ ቅርንጫቾች በመክፈት ሳር ቤት የነበረውን አገናኝ ቢሮ ወደ ቅርንጫፍ በማሳደግ፣ በአጠቃላይ የ39 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና ሦስት አገናኝ ቢሮዎች ባለቤት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አንድ የህንድ ኩባንያ አዲስ የኢንሹራንስ ኢንፎርሜሽን ሲስተም እንዲቀርፅላቸው ተዋውለው ተግባር ላይ ያዋሉ ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፣ የውል፣ የካሳ፣ የጠለፋ ዋስትና የፋይናንስ፣ የገበያና የሥራ ማስፋፊያ መምሪያዎች በአዲሱ የመረጃ መረብ በመተሳሰር፣ ለደንበኞች፣ ዘመናዊ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት የሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
አዋሽ ኢንሹራንስ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድጋፍ የዘጠኝ ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛቱን የጠቀሱት አቶ ቀነአ፤ የዘንድሮውን ሳይጨምር እስካሁን ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ የ27 ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛቱን አስታውቋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል 118.13 ሚሊዮን ብር መድረሱን፣ አጠቃላይ የሰራተኞች ቁጥር 448 መሆኑን፣ በዓመቱ 49 የሽያጭ ወኪሎች አሰልጥነው ማስመረቃቸውንና የሽያጭ ወኪሎች ቁጥር ወደ 336 ከፍ ማለቱን አቶ ቀነአ ዳባ ገልፀዋል፡፡
Saturday, 28 November 2015 09:16
አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ
Written by መንግሥቱ አበበ
Published in
ዜና