Print this page
Saturday, 21 November 2015 13:55

ሕዳር ሲታጠንና ዓለምን ያጠቃው የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ

Written by  ሀብታሙ ግርማ፣የዩኒቨርሲቲ መምህር)
Rate this item
(4 votes)

     የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሁለት አስርት ዓመታት ለመላው የዓለም ህዝብ የሰቆቃ ዓመታት ነበሩ፤ ምክንያቱ ደግሞ የወቅቱ ሃያላን መንግስታት በሁለት ጎራ ሆነው ጦርነት ውስጥ ገብተው ስለነበር ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1914 ዓ.ም እስከ 1918 ድረስ የዘለቀውና የ15 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ይህ ጦርነት፣ በታሪክ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡  የጦርነቱ ማብቃት ሊታወጅ ጥቂት ሲቀረውና ዕልቂቱ ቆመ ሲባል ግን የዓለም ህዝብ ሌላ ፍዳ ማስተናገድ ግድ ሆነበት፤ በሰው ሰራሽ ችግሮች (በዋነኝነት በጦርነት) ተወጥሮ የቆየው መላው የአለም ህዝብ አሁን ደግሞ በእንፍሉዌንዛ በሽታ ከዳር እስከ ዳር  ተጠቃ፡፡:
በተለምዶ የስፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ፣ መነሻው ከወደ አሜሪካ እንደሆነ ይታመናል፡፡ እ.ኤ.አ በጥር ወር 1918 ዓ.ም በአንደኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ ዋዜማ፣ በጦርነቱ ለመካፈል የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር ይያያዛል፡፡ በካንሳስ በሚገኘው ፉንስተን የወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የተቀሰቀሰው ወረርሽኙ፣ በሶስት ቀናት ብቻ 45 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አጠቃ፤ወታደሮቹ አትላንቲክን አቋርጠው አውሮፓን እንደረገጡ በሽታውም አውሮፓ ደረሰ፡፡ የእንፍሉዌንዛ በሽታው በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በፈረንሳይ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ይሆናል በሚል ወረርሽኙ ለህዝብ ሳይገለጽ ተደብቆ ቆይቷል፡፡ በሽታው ይፋ የሆነው  እ.ኤ.አ በህዳር ወር 1918 ዓ.ም  በስፔን  ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታው መታየቱን ተከትሎ ነበር፡፡
ስፔን በጦርነቱ ተካፋይ አልነበረችምና በአገሪቱ የጦርነት ጊዜ ሳንሱር አልነበረም፤ በመሆኑም የበሽታው መስፋፋት ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን በማግኘቱ ወረርኙ እስፓኒሽ እንፍሉዌንዛ (ስፓኒሽ ፍሉ) የሚለውን ስያሜ አገኘ፡፡
የበሽታው ምልክቶች ሳል፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ነስር፣ የጆሮና የአንጀት መድማት፣ ተቅማጥ፣ የአይን ማስለቀስና ውጋት ሲሆኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስም የአእምሮ ህመም ያስከትላል፡፡
  በሽታው ከኮሌራ ወይም ከፈንጣጣ በሽታዎች ጋር ተቀራራቢ ምልክቶችን ስለሚያሳይ ብዙ ያምታታ ነበር፡፡ የበሽታው አስገራሚ ባህሪ፣ አንድ ሰው በበሽታው በተጠቃ በአምስት ቀን ውስጥ ወይ ይሞታል አልያም ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ይፈወሳል፡፡ ይህም እንደ ግለሰቡ የበሽታ መከላከል አቅም ይወሰናል፤ ቫይረሱ የተፈጥሮ የበሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክም ሲሆን ጠንካራ የመከላከል አቅም ያለው ሰው ከአምስት ቀናት በላይ  መቋቋም ስለሚያስችለው  በስድስተኛው ቀን ፈውስ ያገኛል፡፡
የበሽታው አማጪ ቫይረስ ባለመታወቁ መድሃኒትም ሆነ ማስታገሻ አልተገኘለትም፡፡ (እ.ኤ.አ በ1933 ዓ.ም በእንግሊዛዊያን ሳይንቲስቶች እንደተረጋገጠው የበሽታው አማጪ ቫይረስ በሳይንሳዊው አጠራር H1N1 ተብሎ ይታወቃል፡፡) በዚህም የተነሳ የበሽታውን ስርጭት ለማቆም አልተቻለም፡፡ በጥቂት ጊዜም ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከኤሽያ እስከ አፍሪካ፣ከአርክቲክ እስከ ፓስፊክ ደሴቶች ድረስ በከፍተኛ ፍጥነት ተዛመተ፡፡ በሽታው እንዲዛመት የአለም የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ይህም ወታደሮች ከአንዱ የአለም ክፍል ወደ ሌላው ለዘመቻ መንቀሳቀሳቸው ነበር፡፡ አንድ ሶስተኛው የአለም ህዝብ በዚህ በሽታ እንደተያዘም ይነገራል፤ በበሽታው ከተያዙት ውስጥ ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ሲኖ ባይሎጂካ የተሰኘ የህክምና ጥናት ማዕከል ባደረገው ጥናት መሰረት፤ በአሜሪካ እስከ 28 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በበሽታው ተጠቅቶ ነበር፤ 675 ሺህ ገደማ የሚሆነው ህዝብ ደግሞ በበሽታው ሞቷል፡፡ ወረርሽኙ  በህንድ የከፋ ነበር፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ 17 ሚሊዮን ህንዳዊያን በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በጃፓን 23 ሚሊዮን ህዝቦችን ያጠቃ ሲሆን 400 ሺህ ገደማ የሚሆኑትንም ገድሏል፡፡ እንግሊዝ  ሩብ ሚሊዮን፣ ፈረንሳይ ደግሞ 400 ሺህ ዜጎቻቸውን በበሽታው አጥተዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከጥር ወር 1918 ዓ.ም እስከ ታህሰስ 1920 ዓ.ም በመላው ዓለም ተንሰራፍቶ የቆየው የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ፣አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ፈጅቷል፤ የሟቾቹ ቁጥር እስከ 200 ሚሊዮን ይደርሳል የሚሉ መረጃዎችም አሉ፡፡ የወረርሽኙን ጉዳት የከፋ ያደረገው አምራች ዜጎችን በከፍተኛ ሁኔታ በማጥቃቱ ነበር፡፡ በበሽታው ከሞቱት መካከል ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 34 ዓመት የሆኑ ወጣቶች አብዛኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፤ በመሆኑም በሽታው ካደረሰው ሰብዓዊ ውድመት ባለፈ ጥሎት ያለፈው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠባሳ የከፋ ነበር፡፡
ወረርሽኙ በአፍሪካ በሁለት ዙር ነበር የተከሰተው፤ የመጀመሪያው  በፈረንጆቹ በ1918 ዓ.ም የጸደይና የበጋ ወራት ሲሆን ሁለተኛውና የከፋ ጉዳት ያደረሰው ደግሞ  በበልግ ወራት የታየው ነበር፡፡ በሽታው ለመጀመረያ ጊዜ በአፍሪካ የታየው በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችው በሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታዎን ሲሆን በአጭር ጊዜ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ተስፋፋ፡፡ ሚስተር መሪ (Murray) የተባሉ አጥኚ Global Pandemic በተሰኘ ጥናታቸው እንዳሰፈሩት፤ የበሽታው ስርጭት ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት ላይ ሰፊ ነበር፤ በክፍለ አህጉሩ የተከሰተው የሞት መጠን በመላው ዓለም በበሽታው ከተከሰተው ሞት ውስጥ የ29 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በተለይም በምዕራብና ደቡባዊ አፍሪካ ጥፋቱ የከፋ ነበር፤ በጋና እስከ መቶ ሺህ ዜጎች እንዳለቁ ይገመታል፤ በምስራቅ አፍሪካም ቀላል የማባል ቁጥር ያላቸው ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በእንግሊዝ ሶማሊ ሰባት በመቶ የሚሆኑ ህዝቦች በበሽታው ሲሞቱ፣ በኢትዮጵያም ከአርባ ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ከሰብዓዊ ውድመቱ ባለፈ ወረርሽኙ በአፍሪካ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ በጊዜው አጠራር ደቡብ ሮዴሺያ (የዛሬዋ ዚምባብዌ) አምራች የሰው ሀይል በበሽታው በመያዙ የወርቅ ማውጫ ስፍራዎች እንዲዘጉ ሆኖ ነበር፤ በዚህም በማዕድን ዘርፍ ላይ የተንጠለጠለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ ተጎዳ፡፡  ወረርሽኙ በማላዊና በዛምቢያም ያደረሰው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከፍ ያለ ነበር፡፡ በናይጀሪያም፣በተለይ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በሽታው የከፋ ጥፋት በማድረሱና ምርት በማሽቆልቆሉ፣ ቀድሞ ለምግብነት የማይውለው ካሳቫ ለምግብነት መዋል ጀመረ፡፡ በአነስተኛ ጉልበትና ያለ ብዙ ልፋት የሚመረተው ካሳቫ ተመራጭ ምግብ ሆነ፡፡
የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ በአፍሪካ ያስከተለው ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አልነበረም፡፡ በሽታው ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ የኢኮኖሚ ደረጃን ሳይለይ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ቢሆንም ቅኝ ገዢዎች በሽታው ከጥቁር ህዝቦች የመጣ እንደሆነ በማናፈስ የዘር መድልዖ ለማድረግ ተጠቅመውበታል፡፡ ይህ ችግር በተለይም በደቡብ አፍሪካ የጎላ ነበር፤ በዚህም ነጮችና ጥቁሮች ማንኛውንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ላይ እንዳያደርጉ የሚደነግግ አዋጅ እንዲጸድቅ ተደረገ፡፡ በቦትስዋናም በሽታው በርካታ ህጻናትን ወላጅ አልባ አድርጓል፡፡ በጋና የሆነው ደግሞ ትንሽ ለየት ያለ ነበር፤ በሽታው ተንሰራፍቶ በርካታ ሴቶች በመጠቃታቸው፣ ከነባራዊው የጋናዊያን ባህልና ወግ ባፈነገጠ መልኩ ባሎች የሴቶች ድርሻ ተደርጎ ይወሰድ የነበረውን የቤት ውስጥ ስራዎች መስራት ግድ ሆነባቸው፡፡  ወንዶች ማዕድ ቤት ገብተው በቆሎ መፍጨት፣ ምግብ ማብሰል የመሳሰሉትን ስራዎች ይከውኑ ጀመር፡፡
በኢትዮጵያ በሽታው የታየው የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየ ከአስር ወራት በኋላ በህዳር ወር 1911 ዓ.ም ነው፡፡ ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በሽታው መግባቱ አይቀርም በሚል የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መስራት እምብዛም የተለመደ አልነበረም፡፡ በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችለው በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቆንሰላ ያደረገው ነገር ነበር፡፡ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻረድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም ባሳተሙት An Introduction to the Medical History of Ethiopia በሚለው የምርምር ስራቸው ላይ እንደጻፉት፤ በሽታው በውል ያልታወቀ ነበርና ምናልባትም የፈንጣጣ በሽታ ይሆናል በሚል በወቅቱ በኢጣሊያ ቆንስላ ትብብር በሀምሌ ወር 1910 ዓ.ም አስር ሺህ ዶዝ የፈንጣጣ ክትባት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ተደርጎ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ከዘመናዊ ህክምና ጋር ለማይተዋወቀው የኢትዮጵያ ህዝብም ወረርሽኙ ታላቅ መቅሰፍት ነበር፡፡ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ በመላው አገሪቱ ከባድ ዕልቂት ማስከተል ጀመረ፡፡ በተለይም ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን  በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ መረበሽን ፈጥሯል፡፡  
በበሽታው ከተጠቁ ታላላቅ የዘመኑ ሹመኞችና የቤተ መንግስት ሰዎች መካከል ራስ ተፈሪ መኮንን (ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ) እና ባለቤታቸው ወ/ሮ አቴጌ መነን አስፋው ይገኙበታል፡፡ እንዲያውም የራስ ተፈሪና ቤተሰቦቻቸው  ሀኪም የሆኑት ሊባኖሳዊው ዶክተር አሳድ ቼይባን ራሳቸው የበሽታው ተጠቂ ነበሩና የራስ ተፈሪን ቤተሰብ የሚያክም ጠፍቶ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ከህዳር 7 እስከ ህዳር 20 ቀን 1911 ዓ.ም  ለአስራ አራት ቀናት ገደማ የቆየው በሽታው በህዳር ወር የተከሰተ በመሆኑም ህዝቡ የህዳር በሽታ እያለ ይጠራው ጀመር፡፡ ብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በተሰኘው መጽሀፋቸው እንዳሰፈሩት፤ ወረርሽኙ እስከ አርባ ሺህ ኢትዮጵያዊንን ለሞት ዳርጓል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ዘጠኝ ሺህ ዜጎች በበሽታው ሞተዋል፡፡ በተለይም ህዳር 12 ቀን 1911 ዓ.ም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሞቱበት በመሆኑ በቀኑ የጽዳት ዘመቻ እንዲደረግ በአዋጅ ተነግሮ ስለነበር፣ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ይህ ነገር እንደባህል ተወስዶ በየዓመቱ ህዳር 12 ቀን  የጽዳት ዘመቻ ይደረግ ጀመር፤ ይህም በተለምዶ ህዳር ሲታጠን የምንለው ነው፡፡ዶ/ር እናውጋው መሃሪ፣ዶ/ር ክንፈ ገበየሁ እና ዶ/ር ዘርጋባቸው አስፋው የተባሉ የህክምና ባለሙያዎች በጋራ ያሰናዱትና በ2013 እ.ኤ.አ የታተመው The Manual of Ethiopian Medical History ላይ እንደሰፈረው፤ የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በአሜሪካን የቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ (Vanderbilt University) ምሁራን ሲሆን ወቅቱም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት በየጊዜው የተሻሻሉ ክትባቶች በምርምር ተገኝተዋል፡፡ በ1918 ዓ.ም እንደተከሰተው እንፍሉዌንዛ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ባያውቅም ዛሬም ድረስ ግን የሰው ልጆች የጤና ፈተና መሆኑን አላቆመም፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ብቻ በመላው ዓለም አምስት መቶ ሺህ ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ የእንፍሉዌንዛ ክትባቶች የዋጋ ውድነት መፍትሄ ካላገኘ፣ ህዝቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ካላገኘ፣ መንግስታት በሽታውን ለመከላከል ከፍ ያለ ትኩረት ካልሰጡ ---- በእንፍሉዌንዛ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት መቀነስ አዳጋች ነው፡፡  
(የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ፤በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ት/ክፍል መምህር ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 6772 times