Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 February 2012 10:11

የትጋት እመቤት!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ትውልዷና እድገቷ በሰሜናዊው የአገሪቱ ክልል መቀሌ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ተወልዳ ካደገችበትና እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርቷን ከተከታተለችበት የመቀሌ ከተማ በ1979 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በመግባትም በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽንና በማርኬቲንግ ሙያዎች ትምህርቷን ተከታትላ በዲፕሎማ ተመረቀች፡፡ የሥራውን ዓለም የተቀላቀለችው ግን በጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ ላይ ለሚሰራና “አማረኤፍሞይ” ለተባለ እስራኤላዊ ድርጅት ፀሐፊ በመሆን ነበር፡፡ ይህ ድርጅት የጠብታ መስኖን (Dip irrigation) ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ለማስተዋወቅ የመጣ ቢሆንም በወቅቱ ቴክኖሎጂው በህብረተሰቡ ዘንድ እምብዛም ባለመለመዱ የድርጅቱ ሠራተኞች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ያለስራ ነበር፡፡

ሆኖም ግን ወርሃዊ ደመወዛቸውን በወቅቱ ከመቀበል የሚያግዳቸው ነገር አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ ለሥራ ወዳዷ አስቴር ፈጽሞ ሊዋጥላት አልቻለም፡፡ ከወር እስከ ወር ያለ ሥራ ተቀምጦ የሚወሰድ ወርሃዊ ደመወዝን ህሊናዋ አልተቀበለውምና ከራሷ ጋር መክራ ወሰነች፡፡ ሥራዋን በፈቃዷ ለመልቀቅ መወሰኗን የነገረቻቸው የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች ግን ሃሳቧን ፈጽሞ ሊቀበሏት አልፈለጉም፡፡ ለሥራ መልቀቋ ምክንያት የሆናትን ነገር መለወጥ እንደምትችል አሳምነው፣ ደንበኛ እንድታመጣና ከሚገኘው ገቢ ተካፋይ እንድትሆን አደረጓት፡፡ አሁን ሁኔታው ለአስቴር በጣም ተመቻት፣ ደንበኞች ፍለጋ በምታደርገው ሩጫ ስለ ጠብታ መስኖ የበለጠ እውቀት እያዳበረችና ሙያውን እየወደደችው ሄደች፡፡ ግን ወቅቱ ስለጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ በቂ ግንዛቤ ያልነበረበት ጊዜ ስለነበር ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅ በምታደርገው ጥረት ሰዎች ይሳለቁባት ነበር፡፡ ምን ማለት ነው? በዓመት ሁለቴ ዝናብ ላላት አገር ለዚያውም ተንጠባጥባ በምትገኝ ውሃ ምን አይነት ሰብል ሊመረት ይችላል?... በሚል፡፡

ግን ተስፋ አልቆረጠችም፡፡ ዕለት ከዕለት የምታየው ለውጥና እንቅስቀሴም ተስፋዋን አለመለመው፡፡ እ.ኤ.አ እስከ 2000 ዓ.ም በዚህ ሁኔታ ቀጠለች፡፡ የእስራኤላውዊ ድርጅት ኃላፊዎች ወደአገራቸው ሲመለሱ ወ/ሮ አስቴርን በኢትዮጵያ የድርጅቱ ወኪል አደረጓት፡፡ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂው ቀስ በቀስ እየታወቀና እየተለመደ በመምጣቱም ሥራዎች ይመጣሉቸው ጀመር፡፡ የተለያዩ የአበባ እርሻዎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማሳዎች ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ሁኔታው ለሥራ ወዳዷ እንስት ትልቅ ደስታ ነበር፡፡ ደከመኝ፣ ሥራ በዛብኝ፣ እረፍት እፈልጋለሁ ሳትል የደንበኞቿን ጥያቄ ለመመለስና በአግባቡ ለማስተናገድ ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዘችው፡፡ መናገሻ ፍላወርስ፣ ድሬ ሃይላንድ፣ አርሲ አበባ የወ/ሮ አስቴር ተስፋሚካኤልን ዝናባማ እጆች ያገኙና የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ውጤት ካስገኙ የእርሻ ማሳዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ለአምስት አመታት የድርጅቱ ወኪል ሆና ከቀጠለች በኋላ ራሷን ችላ ለመቆምና ባለሙያዎችን ይዛ በግሏ ለመስራት ወስና “አስቱኔት ቢዝነስ ኢንተርፕራይዝ” የተባለ ድርጅት አቋቋመች፡፡ ድርጅቱ እስራኤል አገር ከሚገኝ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ መሥሪያ ዕቃዎችን ከሚያመርት ድርጅት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥር በማድረግ ሥራዋን ቀጠለች፡፡ በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በመያዝ የተጀመረው እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እድገት ማሳየት ጀመረ፡፡ የደንበኞቹ ቁጥር ዕለት ከዕለት እያደገ፣ ትላልቅ እርሻዎችንና የልማት ሥራዎችን እንዲሠራ ትዕዛዝ መቀበል ያዘ፡፡ በዚህ ድርጅት ከተሰሩና በስፋታቸው ከሚጠቀሱ የእርሻ ማሳዎች መካከል የካስትል ዋይነሪ (የካስትል የወይን እርሻ) ዋንኛው ነው፡፡ በ125 ሄክታር ላይ ያረፈውን የዚህን እርሻ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ የሠራው የዚህችው ትጉ ሴት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ሥራውን በማስፋፋት በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና በገጠራማ አካባቢዎች ላይ ለመሥራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው፡፡ የወ/ሮ አስቴር የቴክኖሎጂ ሥራ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ማሳያ ቀርቧል፡፡

ሙያዋን የበለጠ ለማሳደግ ዘወትር የምትጥረው ወ/ሮ አስቴር፤ ወደ እስራኤል አገር ሄዳ ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታም አስመልክታ ስትናገር፤ “በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በአመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡ ውሃን ለመቆጠብና በርካታ ሥፍራዎችንም ለማዳረስ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል” ትላለች፡፡

የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ በከተማ ውስጥም የቤተሰብ መስኖንና የግቢ ማስዋብ ሥራን ለመሥራት እንደሚያገለግልና Landscape የተባለው ግቢን ለማስዋብ የምንጠቀምበት የዚህ ቴክኖሎጂ ሥራ ግቢው ሁሌም አረንጓዴ እንደሆነ በማቆየት፣ ተክሎችን በየዕለቱ ውሃ ለማጠጣትና ለመንከባከብ የሚውለውን የሰው ጉልበትና ጊዜ በመቆጠብ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን ትናገራለች፡፡ ለጠብታ መስኖው ቴክኖሎጂ መሥሪያ የሚሆኑ ዕቃዎችን ከእስራኤል አገር እንደምታስገባ የምትናገረው ወ/ሮ አስቴር፤ ዓላማችን እነዚህን ዕቃዎች እዚሁ አገር ውስጥ በማምረት ለዕቃዎቹ መግዣ የምናውለውን የውጪ ምንዛሪ ከማስቀረቱ ጐን ለጐን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ነው በማለት አስረድታለች፡፡ ሕይወቷና ሥራዋ ከእርሻ ጋር የተያያዘው ወ/ሮ አስቴር፤ ምርቶች ከእርሻ ማሣ ላይ ተቀጥፈው ወደሚፈለጉበት ቦታ ከመጓጓዛቸው በፊት በሙቀትና በፀሐይ እንዳይበላሹ በማድረግ ለማቆየት የሚያስችል Cold Store (ቀዝቃዛ መጋዘን) የሚሰራ “ጌርሎፍ” የሚባል የደች ኩባንያ ሥራ አስኪያጅም በመሆን እየሰራች ትገኛለች፡፡ ኩባንያው በመቀሌ አየር መንገድ ውስጥ የሰራው ትልቅ መጋዘን ሥራው በመጠናቀቁ በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ መጋዘኑ የሚቀመጡት ፍራፍሬዎችና ተክሎችም ሆኑ አበቦች በሚያስፈልጋቸው የአየር ሙቀት መጠን እንዲጠበቁና ወደሚፈለጉበት ሥፍራ እስከሚጓዙ ድረስ በጤና እንዲቆዩ ለማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ወ/ሮ አስቴር ታስረዳለች፡፡ በኤሌክትሪክና በጄኔሬተር ኃይል የሚሰራውን ይህንን መጋዘን በሶላር ሲስተም እንዲሠራ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ቴክኖሎጂውን ወደ ሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ወ/ሮ አስቴር ገልፃልናለች፡፡ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂውም ሆነ የቀዝቃዛ መጋዘን ሥራው በአገራችን ብዙም ያልተለመዱ እንደሆኑ የምትናገረው ወ/ሮ አስቴር፤ መንግስት ቴክኖሎጂዎቹ ያላቸውን ጠቀሜታና አገልግሎት ተገንዝቦ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በመቀጠል የጐደለውን ቀዳዳ እያየ ሊደፍንልን ይገባል ትላለች፡፡ ቴክኖሎጂውን ሁሉም አውቆትና በስፋት ተሰርቶበት አገሪቱ አረንጓዴ ሆና የማየት ጽኑ ምኞትም እንዳላት ትናገራለች፡፡

“አስቱኔት ኢንተርፕራይዝ” የተባለው ድርጅት በአሁኑ ወቅት ለሁለት ኢሪጌሽን ኢንጅነሮች፣

ለአስራ አራት ቋሚ ሠራተኞችና ለ12 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል ከፍቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

 

 

Read 3755 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:15