Saturday, 21 November 2015 13:55

የአዲሱ ሚኒስትር ንግግር፤ “እሱንም አታክረው” ያሰኛል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(28 votes)

የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች “ልደታቸውን” አብረው ቢያከብሩስ?
    የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ባለፈው ሰኞ ለመጀመሪያ ጊዜ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ብዙዎችን ያስደነገጠ ነገር ተናግረዋል፡፡ ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የመንግስት ባለሥልጣናት ያደረጉትን ውይይት አስመልክቶ “አቅጣጫ ማስቀየስ እንዳይሆን?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤“አቅጣጫ የምናስቀይሰው ከምንድን ነው? አገልግሎት ከመስጠትና መልካም አስተዳደር ከማስፈን አንጻር ከፍተኛ ችግር አለብን ብሎ ምህረት የለሽ ግምገማ የተደረገበትን ዋና ጉዳይ አንስቶ ከምን ለማምለጥ ነው የሚፈለገው?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡
“አሁንም በመጥፎ ሥራው መጠየቅ ያለበት ኃላፊ ይጠየቅ፡፡ መሰቀል ያለበትም እሱ ከሆነ የሚገባው ይሰቀል፡፡ ሥርዓቱን ለማስተካከል ስንንቀሳቀስ፣ይህንን ለማደናቀፍ ግልጽ ሚና ያላቸው ወገኖችና ተቋማትም ካሉ መፍረስ ያለበት ይፍረስ፤መመታት ያለበት ይመታ፡፡; ሲሉ መንግስት የተግባር እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ አቋም መያዙን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ( አገላለጹ መረር ገረር ብሏል!) ቋንቋው ደግሞ አብዮታዊ ቅላጼ የያዘ ነበር፡፡ “መሰቀል ያለበት ይሰቀል፣መፍረስ ያለበት ይፍረስ፣መመታት ያለበት ይመታ---- (በአንዴ ጉድ ፈላ እኮ!)
በነገራችሁ ላይ ---- የአዲሱን ሚኒስትር ንግግር ስሰማ አንድ አባባል ትዝ አለኝ - “እሱንም አታክረው” የሚል፡፡ ሰውየው በደርግ ዘመን በእስር ብዙ ተንገላቷል፡፡ ስለዚህ ደርግን ሲጠላው ልክ የለውም፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ የደርግ ጥላቻውን በልክየለሽ ፍቅር ተተካ፡፡  ኢህአዴግን ወደደው፤መውደድ  ብቻ ሳይሆን አመነው፡፡ ኢትዮጵያ ገና አሁን መንግስት ወጣላት---ብሎ ተናገረ፡፡ ይሄን ያስተዋለ ወዳጁ ምን ቢለው ጥሩ ነው? “እሱንም አታክረው!” (ሁሉም በልኩ ሲሆን ጥሩ ነው ማለቱ ነው!) እናም ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ መቁረጡ መቶ ፐርሰንት የሚደገፍ ነው፡፡ (ሁሉም በጉጉት የሚጠብቀው ነው!)
አሁን በቀጥታ ወደ ብአዴን 35ኛ ዓመት የልደት በዓል አከባበር እንለፍ፡-
በዛሬው ዕለት በባህርዳር ከተማ የምስረታ የልደት በዓሉን በደመቀ ሁኔታ የሚያከብረው ብአዴን፤ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ “ነቄ” ብሎ የ30 ሚሊዮን ብር እርዳታ ለድርቁ  መለገሱ  በጅቶታል፡፡ (ፖለቲካሊ ማለቴ ነው!) እንዴ ----- የነገረኞችን አፍ ለመዝጋት እኮ ሌላ መንገድ የለም፡፡ (ከባድ ነው በዚህ ወቅት ልደት ማክበር!) በነገራችሁ ላይ እኔ የብአዴን አማካሪ ብሆን ኖሮ --- በዓሉ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አሳምን ነበር፡፡ (የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን አማካሪ የላቸውም!)
 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች በልደት በዓል ግምኛ ተጨናነቁ ልበል፡፡ ህወሓት፣ኦህዴድ፣--- አሁን ደግሞ ብአዴን በተራው እያከበረ ነው፡፡ እኔ የምለው ግን -- ሌላው ቢቀር የድርጅቶቹን የልደት በዓላት አጠጋግቶ በአንድ ላይ ማክበር አይቻልም ነበር፡፡ (#ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” አሉ!)
በጥናት ወይም በመረጃ ባይረጋገጥም በድርጅቶቹ መካከል የፉክክር ስሜት ተፈጥሯል ሲባልም ይሰማል፡፡ ፉክክሩ በልማት ወይም በኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይመስላችሁ፡፡ በልደት በዓል አከባበር ነው፡፡ (የማን ደምቋል----የማን ሞቋል ዓይነት ነገር!?) አስተውላችሁ ከሆነ----  ከመሃል አገር አርቲስቶችን ወስዶ ትግል የተጀመረበትን ታሪካዊ ሥፍራ ማስጎብኘት፣ስለትግሉ ገለጻ መስጠት፣የጥያቄና መልስ ውድድር በአርቲስቶች መካከል ማካሄድና ብዙ ሺ ብሮች በሽልማት ሰበብ ማሻር----ወዘተ የልደት በዓላቱ መለያ ሆነዋል፡፡ (የአባላት መመልመያ አጋጣሚም ሳይሆን አልቀረም!)
 በነገራችን ላይ እነ ህወሓትና እነ ብአዴን ትግል የጀመሩበትን ስፍራ ሲያስጎበኙና ስለ ትግሉ ታሪክ ሲያብራሩ፣ያሁኑ ትውልድ የእነሱን አርአያ ተከትሎ ጫካ እንዲገባ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ (አንዳንዱ አርቲስት “ኢንስፓየር” ሆኛለሁ ብሎ ቢያመርስ!) የጸረ ሽብር ህጉን የማያውቅ ቀለጠ! እናላችሁ---እንደሚመስለኝ ይሄኛው ትውልድ፤“ተራራን ካንቀጠቀጠው ትውልድ# ቁርጠኝነትና ጽናትን ተምሮ የዘመኑን ባላጋራ ድህነትን እንዲፋለም ነው የተፈለገው፡፡ (በ21ኛው ክፍለ ዘመን የትጥቅ ትግልማ እንደ አርአያ ሊወሰድ አይችልም!!)
እኔ የምለው ግን እነ ህወሓት ---- ብአዴንና ሌሎቹም ድርጅቶች የልደት በዓላቸውን ሞቅ ደመቅ አድርገው የሚያከብሩት ለየትኛው ስኬት ነው? በትጥቅ ትግል ለተገኘው ወይስ ከዚያ በኋላ ለተመዘገበው ልማታዊ ድል? ሁለቱም ከጥያቄ የሚያመልጡ አይደሉም፡፡ ለትጥቅ ትግሉ ከተባለ፣ትኩስ ስኬት አይሆንም፡፡ ሁላችንንም በጋራ የሚያጓጓን ደግሞ በህይወት መስዋዕትነት የተገኘውን ድል ተጠቅመን ምን ፈጠርን? የሚለው ነው:: በተለይ መሠረቴ አርሶአደር ነው ለሚለው ኢህአዴግ፣ይሄ ዋና ጉዳዩ መሆን አለበት፡፡
እናም---- ለምሳሌ ብአዴን ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ለአማራ አርሶአደር ህዝብ ምን የሚታይ፣የሚጨበጥ፣የሚዳሰስ ነገር ፈየደለት? ብአዴን ብዙ የሰራቸው ልማቶች እንዳሉ እስኪሰለቸን ድረስ ሊዘረዝርልን ይችላል፡፡ ከሰራቸው የማይተናነሱ ያልሰራቸው ሥራዎችስ የሉም? ባለፉት 25 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ፣ በልማት፣የአርሶአደሩን ኑሮ በመለወጥ፣ከኋላቀርነት በማውጣት፣በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ወዘተ---ያስመዘገባቸው ስኬቶች  ደረት አስነፍቶ 35ኛ የልደት በዓልን በታላቅ ፌሽታ ለማክበር የሚያጣድፍ ነው? ጥያቄው፤የልደት በዓላቸውን ቀደም ብለው ያከበሩትን ህወሓትና ኦህዴድንም ይመለከታል፡፡
በቅርቡ ብአዴን የ35ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ምክንያት በማድረግ ታዋቂ የአርቲስቶችና ጋዜጠኞች ቡድን ከመሃል ከተማ ጋብዞ፣ ድርጅቱ ትግል የጀመረበትን ታሪካዊ ስፍራ ባስጐበኘበት ወቅት የአንድ ወረዳ ነዋሪዎች ከፍተኛ የውሃ… የመሠረተ ልማት--- የትምህርት ቤት፣የጤና ተቋማት--ወዘተ ችግሮች እንዳሉባቸው በምሬት ተናግረዋል፡፡ በነገራችሁ ላይ ከ10 ዓመት በፊት የተናገሩትን ምሬት ነው የደገሙት፡፡ (ብአዴን 10 ዓመት ሙሉ የት ነበር?)
እኒህ የልማት ካፊያ አልደረሰንም ባይ ወገኖች፣ ከድርጅቱ ጋር ደርግን ሲዋጉ እንደነበርም አስታውሰዋል - አሁን አስታዋሽ አጣን ብለው ቢያማርሩም፡፡ እናላችሁ… #መሰረቴ ጭቁኑ የአማራ ህዝብ ነው” የሚል አብዮታዊም ልማታዊም የፖለቲካ ድርጅት፣ የእነዚህን ነዋሪዎች ችግር በከፊልም ቢሆን እየፈታ ልደቱን ቢያከብር፣ “ልማታዊ ጽድቅ” ይሆንለት ነበር፡፡ (በእርግጥ እኔ ከብአዴን አላውቅም!)
                         ***    
ከጥቂት ጊዜያት በፊት በፌስቡክ ገጽዋ ላይ ያነበብኩት የህይወት የምሻው ማለፊያ ጽሁፍ፣ (ለአጭር ልብወለድ በቀረበ የአጻጻፍ ዘይቤ የተከሸነ ነው) እስካሁን ስሞግት የነበረውን ሃሳብ የሚያጸኸይልኝ ስለመሰለኝ እንደወረደ ታነቡት ዘንድ እነሆ፡-
ዛሬ በጠዋት የመንግሥት ወዳጅ የሆነው ወዳጄ፣ ሰላም እንኳን ሳይለኝ፤ “ውሃና መብራት ጠፋ ለማለት ከፌስቡክ የማትጠፉ ፀሃፊዎች፣ሁሌም እዚህ አገር ደህና ነገር ሲደረግ ድራሻችሁ ይጠፋል አይደል?” አለኝ፡፡ለወትሮው ትሁት ስለሆነ ላረጋጋው ብዬ፤“እግዜር ይመስገን፤አንተ እንዴት አደርክ?” አልኩት፡፡ “የእውነቴን ነው በጣም ነው የማዝነው፡፡ ቢያንስ ተማርን የምትሉት ለሀገር የሚሆን ነገርን ከመንግሥት ለመለየት አለመቻላችሁ ያሳዝነኛል”
“እንዴ… ምንድን ነው? ባቡሩ እኔ ተኝቼ ሌሊት ተመረቀ እንዴ?”
“አታሹፊ ሕይወት፤ ሰሞኑን የህገ መንግሥቱ 20ኛ ዓመት ሲከበር ጭጭ አላችሁ…! ለህዝባችን ለውጥ አላመጣም? አያስማማንም? በተለይ አንቺ ፖለቲካል ሳይንስ ተምረሽ…”
“የምርህን ነው?”
“አዎ የምሬን ነው፡፡ ከህገ መንግሥቱ ጋር ያላችሁ ጥል ምንድን ነው?”
“አይ እንግዲህ ይሄ የቡድን ነገርህን እዛው ተው፡፡ እኔ ስለራሴ ብቻ ነው ማውራት የምችለው!”
“እሺ አንቺስ ከህገ መንግሥታችን ጋር ያለሽ ጥል ምንድን ነው?”
“ኧረ እኔ ህገመንግስቱን እወደዋለሁ”
“አታሹፊ…”
“አላሾፍኩም! ታውቃለህ፤ አሳምሬ ተምሬዋለሁ፡፡ አሳምሬ አስተምሬዋለሁ”
“እኔም እኮ ለዚያ ብዬ ነው፤ …ታዲያ ለምን ጭጭ አልሽ?”
“ለምን ጭጭ አልሽ?”
“አዎ… ለምን ጭጭ አልሽ…?”
“አሁን ላለንበት ሁኔታ፤የፀደቀበትን ቀን ከማክበር ራሱን ህገ መንግሥቱን ማክበር ይበልጥ አንገብጋቢ ነው ብዬ ነው”
ስልኩ ጆሮዬ ላይ ተዘጋ፡፡
*******   **************
እውነቴን ነው የምላችሁ… ከላይ ካነሳሁት ሃሳብ ጋር ግጥም ነው ያለልኝ፡፡ እናላችሁ---  “አሁን ላለንበት ሁኔታ ብአዴን የተመሰረተበትን ዓመት ከማክበር የተመሰረተበትን ዓላማ (የህዝብን የልማት ችግሮች መፍታት) ማክበር ይበልጥ አንገብጋቢ ነው” ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ (ቅድም እንዳልኳችሁ “እኔ ከብአዴን አላውቅም!”)
ለማንኛውም ግን መልካም 35ኛ ዓመት የልደት በዓል ለብአዴን!

Read 4621 times Last modified on Saturday, 21 November 2015 14:34