Saturday, 21 November 2015 13:51

‘የማያልቅ ‘ጥበቃ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

“ምክንያት ከሌላቸው ጥበቃዎች ይሰውረንማ!”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…የምንጠብቃቸው ነገሮች በዙሳ! አለ አይደል…ማለቅ ባለባቸው ጊዜ የሚያልቁ ነገሮች እያነሱ ነው፡፡
በተሰጠን ቀጠሮ ሀኪም ቤት ዘንድ እንሄድና ሀኪሙ እስኪመጣ እንጠብቃለን፡፡ አንዳንዱ ሀኪም በተባለው ሰዓት አይመጣማ! እናማ…ለማን አቤት ይባላል! ‘ማስጠበቅ’ ተለምዷላ! ዘንድሮ ልጄ አቤት ማለት ጦሱ ሊበዛ ይችላላ!
የሲኒማና የትያትር ቤት በር እስኪከፈት ተሰልፈን እንጠብቃለን፡፡ የሲኒማና የትያትር ቤቱ በር ደግሞ ይከፈታል በተባለው ሰዓት አይከፈትም፡፡ እናማ…ለማን አቤት ይባላል! አቤት ብንል…አለ አይደል… “ሰዉ ለአንድ ድስት የምትሆን ሽንኩርት መግዛት አቅቶታል አጅሬ የሲኒማና የትያትር ቤት በር አልተከፈተልኝም ብለህ ታማርራለህ!” ልንባል እንችላለና!
‘ይህን ፊልም እናሳያለን፣ ያንን ፊልም እናቀርባለን…’ እየተባለ ፉክክር በበዛበት ዘመን በሮችን በጊዜ አለመክፈት ቀሺም ነው፡፡
እግረ መንገዴን…የፉክክር ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ…ቢራዎች ቀልባችንን ለመሳብ ፉክክሩ ተጧጡፏል አይደል፡፡ ይቺን ስሙኝማ…ለንደን ውስጥ ትልቅ የቢራ ፌስቲቫል ይካሄዳል፡፡ ፌስቲቫሉ ካለቀ በኋላ የቢራ ፋብሪካዎች ፕሬዝዳንቶች አንድ ሁለት እንባባል ምናምን ተባብለው ተያይዝው ወደ አንድ ሆቴል ይሄዳሉ፡፡
ኮሮና የተባለው ቢራ ፕሬዝዳንት ለባሬስታው… “የዓለም ምርጡን ቢራ ኮሮናን ስጠኝ…” ይለዋል፡፡ ባሬስታውም የቀዘቀዘ ኮሮና ቢራ አምጥቶ ይከፍታል፡፡
የበድዋይዘር ቢራ ፕሬዝደንት ደግሞ… “የቢራዎች ንጉሥ የሆነውን በድዋይዘርን ስጠኝ…” ይላል፡፡ ባሬስታውም ቀዝቃዛ በድዋይዘር ቢራ ይከፍትለታል፡፡
ኮርስ የተባለው ቢራ ፕሬዝዳንት በበኩሉ… “በዓለም ምርጥ የሆነውንና ከሮኪ ተራራ ንጹህ የምንጭ ውሀ የሚጠመቀውን ብቸኛውን ኮርስ ቢራ ስጠኝ…” ይላል፡፡ ባሬስታውም ቀዝቃዛ ኮርስ ቢራ ይከፍትለታል፡፡
አብሯቸው የነበረው የጊነስ ቢራ ሰውዬ ቁጭ ይልና… “ለእኔ ለስላሳ ክፈትልኝ…” ይለዋል፡፡ ሌሎቹ ፕሬዝዳንቶች… “ለምን ጊነስ አትጠጣም?” ይሉታል፡፡ የጊነሱ ሰውዬ ምን ቢል ጥሩ ነው… “እናንተ ለስላሳ እየጠጣችሁ ስለሆነ እኔ ብቻዬን ለምን ቢራ እጠጣለሁ…” ብሏቸው አረፈ፡፡
አሪፍ ‘ማስታወቂያ’ አይደለች!
እናላችሁ…የደሞዝ እድገት እስኪሰጠን እንጠብቃለን፡፡ የደሞዝ እድገቱ ደግሞ ይሰጣል ከተባለ ይኸው አንድ የዓለም ዋንጫ አልፎ ሁለተኛው ሊመጣ ነው፡፡ እናማ…ለማን አቤት ይባላል! ‘ማስጠበቅ’ ተለምዷላ! ልጄ አይደለም እድገቱ እርከኑ እንኳን ሊቀር ይችላላ!
እናማ… የማስጠበቅ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ባልና ሚስቱ ብዙ ጊዜ ይጨቃጨቃሉ፡፡ የሚጨቃጨቁትም በተለይ ገበያ በሚሄዱ ቁጥር ነው፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን አብረው ሱፐርማርኬት ይሄዳሉ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሚስት እንደተለመደው ከአጠገቡ ትጠፋበታለች፡፡ ቢጠብቅ፣ ቢጠብቅ ሊያገኛት አልቻለም፡፡ ታዲያ ወደ አንዲት ቆንጆ ሴት ይጠጋና… “የእኔ እመቤት ለጥቂት ደቂቃ አብረሽኝ እያወራሽ መቆም ትችያለሽ?” ይላታል፡፡ ሴትዮዋም ግራ ገብቷት…“ለምን?” ትለዋለች፡፡
እሱም “ሚስቴ ጠፍታ ነው…” ይላታል፡፡
“ታዲያ ሚስትህ ብትጠፋ ከእኔ ጋር እያወራህ መቆሙ ምን ያደርግልሀል?” ትለዋለች፡፡ ምን ቢላት ጥሩ ነው… “ከቆንጆ ሴት ጋር ሳወራ ካየች ከየትም ይሁን ከየትም ብቅ ትላለች፡፡” እውነትም በቅጡ እንኳን ሳያወራ ሚስት ሆዬ ከች አለቻ! እንትናዬዎቻችሁ ሱፐርማርኬት ውስጥ እየጠፉ ያስቸገሯችሁ እንትናዎች ይኸው ማግኛ ዘዴውን ጠቁመናል፡፡
እግረ መንገድ ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ሚስቱ ጨቅጫቃ ነገር ትሆንበታለች፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን ምን ይላታል…
“ኃይማኖተኛ እንድሆን አደረገሽኝ…” ይላታል፡፡
እሷም… “እውነት! እንዴት አድርጌ ነው ኃይማኖተኛ ያደረግሁህ?” ትለዋለች፡፡ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“በገሀነም አላምንም ነበር፡፡ አሁን አንቺን ካገባሁ በኋላ ግን ገሀነም ምን ሊሆን እንደሚችል አውቄያለሁ፡፡”
እናላችሁ…የሚያስጠብቁን ነገሮች በዝተዋል፡፡ ያስገባነው ማመልከቻ ተፈርሞ ሊሰጠን “ሰኞ ሦስት ሰዓት መጥተህ ውሰድ…” እንባልና በተባለው ጊዜ ሄደን ፈራሚው አለቃ እስኪመጣ እንጠብቃለን፡፡ እናማ…ለማን አቤት ይባላል! ‘ማስጠበቅ’ ተለምዷላ!  ማመልከቻው ለሌላ ወር ‘ተጎልቶ’ ሊከርም ይችላል፡፡
ወደ እንትን ሰፈር የሚሄደው አውቶብስ እስኪመጣ አንጠብቃለን፡፡ አውቶብሱ ደግሞ ይደርሳል በተባለበት ሰዓት አይደርስም፡፡ እናማ…ለማን አቤት ይባላል! ‘ማስጠበቅ’ ተለምዷላ! አቤት ብንል… አለ አይደል… “ስንቱ ሰው በእግሩ መአት ኪሎሜትር በሚሄድበት አገር አንተ አውቶብስ በሰዓት አልመጣም ብለህ ታማርራለህ!” ልንባል እንችላለና!
ስሙኝማ…የፈለገውን ሰዓት ብንጠብቅ ‘ማድ’ የማንሆንበት ምን መሰላችሁ….የእንትናዬ ቀጠሮ! እሷ ትምጣ እንጂ… አብዛኞቻችን ቆሞ ለማደርም ወደኋላ አንልም፡፡ እንትናዬአችሁ እስክትመጣ…አለ አይደል… አይደለም ሁለት ሰዓት አራት ሰዓትም ትጠብቃላችሁ፡፡ ዋናው ነገር የእሷ መምጣት ነው፡፡
ለነገሩማ…አለ አይደል… እኛዬዎቹ የልብ ልብ እንዳይሰማን… “ተዪው እባክሽ፡ ትንሽ ይምታው…” ብለው ዘና ይላሉ፡፡ እናማ… የስልክ እንጨት ተደግፎ የስምንት ሰዓቷ ተቀጣሪ እስክትመጣ እስከ አሥራ አንድ ሰዓት ሲጠብቅ የኖረውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…አንድ ወታደር ለግዳጅ ከአገር ርቆ ተመድቦ ይቆያል፡፡ እና ተመልሶ ሲመጣ እጮኛው… “ከአንተ ጋር መሆን አልፈልግም፣ በቃኝ…” ብላ ‘አውላላ ሜዳ ላይ አስጥታው’ ትሄዳለች፡፡ በዚህም ይናደዳል፡፡
 ትንሽ ቆይታ ስልክ ትደውልና… “የሰጠሁህን ፎቶግራፌን መልስልኝ…” ትለዋለች፡፡ ይሄኔ ወታደር ሆዬ ከየጓደኞቹ ላይ የመአት ሴቶች ፎቶዎች ይሰበስባል፡፡ ከዛም በፖስታ አሽጎ ይልክላታል፡፡ ከፎቶዎቹ ጋር አብሮ የላከው መልእክት ምን የሚል መሰላችሁ…
“ይቅርታ፣ የትኛዋ እንደሆንሽ ማስታወስ አልቻልኩም፡፡ የአንቺን መርጠሽ ውሰጂና ሌሎቹን መልሽልኝ፡፡”
በገዛ እጇ! እኛ ስንትና ስንት ነገር እየጠበቅን እያለ ብትጠብቅው ኖሮ ምን አለበት!
እግረ መንገዴን… ሰውየው በትዳሩ ይበሳጫል፡፡ እናላችሁ… “ምን ሲሆን ነው ያገባሁት…” ምናምን እያለ ይማረራል፡፡
አንድ ቀን ለጓደኛው ምን ቢለው ጥሩ ነው…  “የሠርግ ቪደዮአችንን የማየው ከመጀመሪያ ጀምሮ ሳይሆን ከመጨረሻው ጀምሮ ወደ ኋላ ነው…”  ይለዋል፡፡ግራ የተጋባ ጓደኛም “ለምን?” ይለዋል፡፡ ባል ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ወደ ኋላ ሳየው ቀለበት የምደራረግበት ጋ ሲደርስ የሚታየው ቀለበት ስታጠልቅልኝ ሳይሆን ስታወጣው ስለሆነ ያኔ ደስ ይለኛል፡፡”
የተበሳጫችሁ አባወራዎች ቪደዮአችሁን ወደ ኋላ አይታችሁ የሚሰማችሁን በፈለጋችሁት የኤስ.ኤም.ኤስ. ቁጥር ላኩልንማ! (ማን ከማን ያንሳል!) እናላችሁ… የምንጠብቅባቸው ሰበቦች መአት ናቸው፡፡ ደሞስ… ለማን አቤት ይባላል! ‘ማስጠበቅ’ ተለምዷላ!
እናማ…ምክንያት ከሌላቸው ጥበቃዎች ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4173 times