Saturday, 21 November 2015 13:48

ጅግራ ያዝ፤ ሩጫ ከፈለግክ ልቀቃት፣ ሥጋ ከፈለግክ እረዳት

Written by 
Rate this item
(23 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን ውሻና አውራ ዶሮ ውድ ጓደኛሞች ሆኑ፡፡ ከዚያም ረዥም መንገድ ለመሄድ ተስማሙና ጉዞ ጀመሩ፡፡ ማታ ላይ አውራዶሮ አንድ ትልቅ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ወጣና መኝታውን እዚያ ላይ አደረገ፡፡
ውሻው ደግሞ የዛፉ ግንድ ከሥር በኩል ተፈልፍሎ ስለነበር እዚያ ውስጥ ገብቶ ጥቅልል ብሎ ተኛ፡፡
አውራ ዶሮ ሊነጋ ሲል እንደተለመደው መጮህ ነበረበትና ኩኩሉ… አለ፡፡
በአቅራቢያው የነበረ አንድ ቀበሮ ድምፁን ሰማና፤
“ኦ ዛሬ ምርጥ ቁርስ አገኘሁ ማለት ነው!” እያለ ድምፁን ወደሰማበት አቅጣጫ ገሰገሰ፡፡ ከትልቁ ዛፍ ዘንድ ሲደርስ ከቅርንጫፉ ሥር ቆመና፤
“እባክህ ውረድና አጫውተኝ፡፡ ይህን የሚያምር ዜማህንም አሰማኝ” እያለ ሊያማልለውና ሊያታልለው ይሞክር ጀመር፡፡
አውራ ዶሮም፤
“ዕውነትም እኔም ወርጄ ባጫወትኩህ በጣም ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ግን አሁን ገና በጣም ጠዋት ነው፡፡”
ቀበሮ፤
“ነግቷል‘ኮ፡፡ ይልቅ ውረድና ቁርስም ልጋብዝህ” አለው፡፡
አውራ ዶሮም፤
“የለም ገና ነው፡፡ እኔ እኮ ነኝ የጊዜ አዋቂ፡፡ ረሳህ እንዴ? ይልቅ አንተ ዛፉ ላይ ወጥተህ ለምን ትንሽ አረፍ አትልም?”
“እኔ ዛፍ መውጣት‘ኮ አልችልም”
“ምንም ችግር የለም ዘበኛዬ ታች ተኝቷል፡፡ ቀስቅሰውና በሩን ይከፍትልሃል”
ቀበሮ እንደተባለው ግንዱን እየጫረ አንኳኳ፡፡
ይሄኔ ውሻ ነቃና ዘሎ አንገቱን አንቆ ብጭቅጭቁን አወጣው፡፡
***
ብልሃት ከሁሉ የተሻለ መሣሪያ ነው፡፡ ብልሃት ጊዜን ማወቅ ነው፡፡ ብልሃት የኃይል አጠቃቀምን ማወቅ ነው፡፡ ብልሃት ቅልጥፍናንና የችግር አፈታት ዘዴን እንዴት እንደምናቀናጅ ማወቅ ነው፡፡ ብልሃት ድንገተኛ ችግር ሲያጋጥም ረጋ ብሎና ጥሞና ገዝቶ ሳይደናገጡ ችግሮችን መፍታት ነው፡፡ የሀገራችን ችግሮች የተወሳሰቡና አንዱ ካንዱ ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ሁሉንም ባንዴ ለመፍታት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ቅደም ተከተል ማበጀት ግድ ነው፡፡ አደገኞቹንና አጣዳፊዎቹን ከፊት ለፊት፣ ሌሎቹን ከኋላ አድርጐ መሰደር ያስፈልጋል፡፡ ከፊት ያሰለፍናቸውን ጊዜ አለመስጠትና ሳያወላዱ መምታት ከብዙ ጣጣ ይገላግለናል፡፡ ይህ ማለት ግን ያለጥንቃቄ መጋለብና መዝመት ማለት አይደለም፡፡ በዕውቅ እና በጥንቃቄ (Cautiously and consciously እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ፡፡ አያሌ የተጠላለፉ የሙስና ተግባራት አሉ፡፡ እንደ ዳንቴል አንዷ ክር ስትሳብ መዓት ክር ይተረተራል፡፡ ሙሰኛ ኢ-ፍትሐዊም ነው፡፡ ሙሰኛ ኢ ዲሞክራሲያዊም ነው፡፡ ሙሰኛ ኢ-መልካም አስተዳደር ነው፡፡ ሙሰኛ በስልጣን ባላጊ ነው፡፡ ሙሰኛ ዘማዊ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ሁሉም ተጠራቅመው የተሰጡት አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ብቻ እንደ ካንሰር የሆኑበት አለ፡፡ ካንዱ ወደአንዱ የሚዘምትም አለ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የፖለቲካ ምሁራን የሚሉንን መስማት ደግ ነው፡፡ “አልፎ አልፎ ስህተት ይፈጠራል፡፡ ዓለም ይህ ይሆናል ብለን ለመተንበይ በጣም አዳጋች ናት፡፡ ያም ሆኖ ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ጉድ እሚሆኑት ስህተት በመፈፀማቸው ሳይሆን ስህተቶቹን ለማስተካከል በሚጠቀሙበት ዘዴ ምክንያት ነው፡፡ እንደቀዶ ጥገና ሐኪም የተበላሸውን ክፍል ቆርጠው መጣል አለባቸው፡፡ ይቅርታ መጠየቅና ሰበብ አስባብ መፍጠር ደነዝ ቢላዎች ናቸው፡፡ ሰበባ ሰበቦች ማንንም አያረኩም፡፡ ይቅርታ ሲበዛም ብቃት ማነስን ነው የሚጠቁመው፤” ይለናል ሮበርት ግሪን የተባለው ፀሐፊ፡፡
ቆራጥ እንሁን፡፡ አጋርን ለማዳን ጋንግሪን መቁረጥና የመርዝን ሰንኮፍ መንቀል ዛሬ ግዴታ ነው፡፡ ማንኛውም ዓይነት ሙሰኛ የዕድገት ጠላት ነው፡፡ ፖለቲከኛ ስለሆነ ሙሰኛ ሊሆን አይችልም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ነጋዴም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡ አለቃም ሆነ ምንዝር ከሞሰነ ሙሰኛ ነው፡፡ በመሬት፣ በቤት፣ በቢሮ አሻጥር ሙስና ሙስና ነው፡፡ አገር በድርቅ ይጠቃል እየተባለ አያሌ ድጋፍ በሚያስፈልግበት ሰዓት እየመዘበረ በዋንጫ ጋጋታ በሠፊ ገበታ፣ አሸሸ ገዳሜ ሲል ይፋ የሚታየው ሙሰኛ፣ አልታየን ካለ ከተጠያቂነት አናመልጥም፡፡ ጠባቂውን ማን ይጠብቀው (Who guards the guard) የሚለውን ሳንዘነጋ ነው ታዲያ! የያዝ ለቀቅ አሠራር አገራችንን እጅግ አድርጐ ጐድቷታል፡፡ ያለው አማራጭ “ጅግራ ያዝ፤ ሩጫ ከፈለግክ ልቀቃት፣ ሥጋ ከፈለግክ እረዳት” የሚለውን ተረት በቅጡ መረዳት ነው፡፡

Read 7304 times