Saturday, 21 November 2015 13:46

ህገወጥ ስደት በከፍተኛ ደረጃ ተባብሷል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ (ከሐማሬሳ)
Rate this item
(21 votes)

ከትግራይ የሚሰደዱ በርካታ ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ
· በአንድ ፍተሻ ጣቢያ ብቻ በቀን ከ100 በላይ ስደተኞች ይያዛሉ
· በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ብድር የወሰዱ ወጣቶች ገንዘቡን ይዘው ይሰደዳሉ

   በተሽከርካሪና በእግር የሀገሪቱን ድንበር አቋርጠው በህገወጥ መንገድ ወደ አረብ አገራት የሚሰደዱ ወጣቶች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን በተለይ ከትግራይ ክልል በርካታ ወጣቶች እየተሰደዱ እንደሆነ ፖሊስ ገለፀ፡፡
ሰሞኑን የአዲስ አድማስ ሪፖርተር በሀረር ክልል ሃማሬሳ አካባቢ ተገኝታ እንደታዘበችው፤ በርካታ ወጣቶች በጅጅጋ አድርገው፣ የኢትዮጵያን ድንበር በማቋረጥ ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞችም በታዳጊነትና በአፍላ የወጣትነት እድሜ ላይ እንደሚገኙ ከአካባቢው ፖሊስ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በሐማሬሳ የፍተሻ ጣቢያ ብቻ በየቀኑ ከ100 የማያንሱ ወጣቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚውሉ የገለፀው ፖሊስ፤ ስደተኞቹ የሚለዩት በአዳዲስ ፎርጅድ መታወቂያቸው ነው ብሏል፡፡
የፍተሻ ጣቢያው ፖሊሶች እንደሚሉት፤ ስደተኞቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ወደ መጡበት እንዲመለሱ በመኪና ከተሳፈሩ በኋላ፣ ከመኪና ሹፌሮች ጋር በመመሳጠር በድጋሚ ወርደው በእግር ለማለፍ የሞት ሽረት ትግል ያደርጋሉ፡፡
የሃረሪ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ጣሰው ሻረው በበኩላቸው፤ የስደቱ መባባስ ፖሊስ መደበኛ ስራውን ትቶ ስደተኞቹን በመያዝ ላይ ብቻ እንዲያተኩር አድርጎታል ብለዋል፡፡ ከትግራይ ክልል የሚመጡ ወጣቶች ቁጥር ላቅ ያለ እንደሆነ ኮማንደሩ  ጠቁመው፤ በአንፃሩ ከደቡብ ክልል የሚመጡ ወጣቶች በእጅጉ መቀነሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአማራ ክልል የሚመጡ ስደተኞች በአሁኑ ወቅት ቀላል የማይባል እንደሆነ ኮማንደሩ ገልፀዋል፡፡ባለፈው ዓመት ብቻ በዚህ መስመር ድንበር ለማቋረጥ ሲሞክሩ ከ8ሺህ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች የተያዙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንድ ሺህ ያህሉ ሴቶች እንደነበሩ የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል፡፡
መንግሥት ከየመንና ከሳውዲ አረቢያ ተመላሾችን ለማቋቋም በማሰብ ስራ እንዲፈጥሩ የሰጣቸውን የገንዘብ ብድር በመያዝ ዳግም ሊሰደዱ ሲሉ የተያዙ በርካታ ወጣቶች እንዳሉም ታውቋል፡፡ በየኬላው የተያዙትን ስደተኞች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ሲሞከር፣ ከተሳፈሩበት መኪና ወርደው በማምለጥ ለመሰደድ እንደሚሞክር ኮማንደር ጣሰው ገልፀዋል፡፡ ስደተኞቹ ለገንዘብ ዘረፋ፣ ለአስገድዶ መድፈርና ለተለያዩ ጥቃቶች በስፋት ተጋላጭ እንደሆኑ የጠቆሙት ኮማንደሩ፤ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞች የተለያዩ ፎርጅድ መታወቂያዎች የያዙ ሲሆን መታወቂያዎቹ በደላሎች የሚዘጋጁ መሆኑንና ስደተኞቹ የደላሎቹን ማንነት ላለመግለፅ ቃል ስለሚገቡ እንደማይናገሩም  ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 7437 times