Saturday, 21 November 2015 13:40

አለማቀፉ የፕሬስ ተቋም ጦማሪ ዘላለም ከአገር እንዳይወጣ መከልከሉ ያሳስበኛል አለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

- በግለሰቡ ላይ የደረሱ የመብት ጥሰቶች በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ ጠይቋል
- የዞን ዘጠኝ ጦማርያንን ሽልማት ለመቀበል ወደ ፓሪስ ሊጓዝ ነበር

    ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገው ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የተሰኘ አለማቀፍ ተቋም፣ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ከእስር ከተለቀቁት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞች አንዱ የሆነውን ዘላለም ክብረት፤ ከአገር እንዳይወጣ መከልከሉ እንደሚያሳስበው አስታወቀ፡፡
የዞን ዘጠኝ ጦማርያን በዘንድሮው የሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት “የሲቲዝን ጆርናሊስት” ዘርፍ አሸናፊ ሆነው መመረጣቸውን ያስታወሰው ተቋሙ፣ ዘላለም ክብረት ጦማርያኑን ወክሎ ሽልማቱን ለመቀበል ባለፈው ሰኞ ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ ሊሄድ ሲል፣ በኢትዮጵያ መንግስት የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች ፓስፖርቱን በመቀማት ወደ አውሮፕላኑ እንዳይገባ መታገዱን ገልጿል፡፡ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫው፡፡
የኢሚግሬሽን ባለስልጣናቱ ዘላለምና ሌሎች የዞን ዘጠኝ ጦማርያን ከዚህ በፊት ታስረው መቆየታቸውን በምክንያትነት በመጥቀስ ከአገር መውጣት አትችልም እንዳሉት የጠቆመው ተቋሙ፣ በጦማሪው ላይ የተጣለውን የጉዞ እገዳ በተመለከተ በአዲስ አበባና በፓሪስ ከሚገኙ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም እንዳልተሳካለት ገልጿል፡፡“በዘላለም ክብረት ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ ያልጠበቅነው ነው፤ አስደንግጦናል፡፡ ከእስር በተፈታበት ወቅት እንቅስቃሴውን የሚገድብ ምንም አይነት ክልከላ አልተጣለበትም፣ የተቀሩት የዞን ዘጠኝ አባላትም ባለፈው ጥቅምት ከተመሰረተባቸው የሽብር ክስ ነጻ ተደርገዋል፤ ፓስፖርቱን የተቀማበት ምክንያት አልገባንም፣ የሚመለከታቸው አካላት የተጣሱትን የዘላለምን መብቶች በአፋጣኝ  እንዲያስከብሩ እንጠይቃለን” ብለዋል የተቋሙ የአፍሪካ ዴስክ ሃላፊ ክሊ ካን ስራይበር፡፡ ዘላለምፓስፖርቱን በተቀማ ማግስት ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄድ በተሰጠው መመሪያ መሰረት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማምራቱን፣ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝና ምርመራው እስካልተጠናቀቀ ድረስም ፓስፖርቱየማይመለስለት እንደተነገረው ተቋሙ በመግለጫ አስታውቋል፡፡


Read 3577 times Last modified on Saturday, 21 November 2015 14:40