Saturday, 11 February 2012 10:06

ያበሻ ነፍስ ባበሻ ገበያ

Written by  በቀለ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

ልክ የዛሬ ሃያ ዓመት ኮፒዮ የምትባል የፊንላንድ ከተማ ውስጥ ባጋጣሚ ያገኘኋት አንዲት ያገሩ ወጣት፣ ኢትዮጵያ ከርማ ኖሮ ያነሳቻቸውን ስላይድ ፎቶግራፎች እያሳየችኝ ስለክራሞቷ ብዙ ብዙ አወጋን። ጥቂት የፈረንጅ እንግዶች እንደሚያደርጉት ለቆየችበት መንደር ሕዝብ ማህበራዊ አኗኗርና የሥነ ልቦና ጉዳዮች ሁሉ ምክንያታዊ መሥፈሪያዎቿን እየደረደረች፣ ፍቅሯንም ሆነ ትዝብቷን ሁሉ ሳትደብቅ አጫወተችኝ። ሲፈርድብኝ እንደብዙ  ኢትዮጵያውያን ሁሉ እኔም በባዕድ ፊት ስለዚህች አገር የሚነሳው ሁሉ ደግ ደጉና ፅድቅ ፅድቁ ብቻ እንዲሆን ከመፈለጌ ብዛት ትዝብቷን ችላ ብዬ በሙገሳዋ ጣልቃ ገባሁና፣ ሌላ ያላየችው  ያበሻ ቸርነት እንዳለ ላሳያት ተንጠራራሁ። በዛሬው ቋንቋ “ገፅታ ግንባታ” ከሚባለው ዘመቻ ጋር ይመሣሠል እንደሆን እርግጠኛ አይደለሁም።

ለማናቸውም በዚያን ወቅት እኔ ኢትዮጵያ ከሄድኩ 5 ዓመት ያለፈኝ ሲሆን እርሷ ገና ዓመት አልሆናትም ከዚያ ከመጣች። “በል ቀጥል” አለችኝ። ኢትዮጵያዊ አልኳት “ኢትዮጵያዊ አንዴ ከወደደሽ ነፍሱንም ጭምር አሳልፎ የሚሰጥሽ ፍጥረት ነው” ከማለቴ ሳቅ አለችና “ስለፍቅራቸውም ሆነ ስለመውደዳቸው በምትለኝ ሁሉ እስማማለሁ። ነገር ግን ስጦታቸው ከሰው ነፍስ ይልቅ ሌላ ውድ ዕቃ ቢሆንልኝ ይሻለኛል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በቆየሁባቸው ዓመታት ካስተዋልኩት ነገር አንዱ የሰው ነፍስ አንተ አሁን የምትለኝን ያህል ውድ ዕቃ ያለመሆኑን ነው።”  አለችና የስሜት ጨዋታዬን  ወደ ሕሊናዬ ሚዛን ወረወረችው። ታዲያ ያገሬ ሰው ያላግባብ ሲሞትም፣ በከንቱ ከሞት ጋር ግብግብ ሲገጥምም ወይም ደግሞ ሞቶ ቀብርና መቃብሩ አቅል አጥቶ ባየሁ ቁጥር የዚህች የፊንላንድ ሴት ንግግር ዘወትር እንዳዲስ ከፊቴ ድቅን ይላል።

 

እውነቱን ለመናገር የሰው ነፍስ ዋጋ ለፈረንጆች የተገለጠውን ያህል ላፍሪቃውያኑ ተጋርዶባቸዋል እንዳልል ደግነቱ ራሳቸው ፈረንጆቹ ስለራሳቸው ፅፈው ካኖሩት የታሪክ ድርሳን የሚነበበው ፈፅሞ ይህንን አያረጋግጥም።

ደግነትና ሥልጡንነት የባለፀግነት ልጆች፤ ጭካኔና ንፍገት ደግሞ የድህነት ውላጆች ናቸው ብለን እንዳንደመድምም ቢያንስ በዛሬው ዓለም የባለፀጎች ጣት በጉልበትና በዕብሪት የሚጓጉጠውን ቁስል ሁሉ ስናይ ግምታችን ሩቅ ሳያራምደን ይቀራል። እንዲያም ሆኖ ግን ይህ ስሌት ግማሽ እውነት እንዳለው መዋሸት አይቻልም። ምናልባትም ዕጦት ለብዙ ውርደት ለብዙ ማዕረገቢስነት አጋልጦ የሚሰጥ ትልቅ ባላንጣ ስለመሆኑ ኖረን አይተነዋል። በመኖር ትርፍና በመሞት ኪሣራ መካከል ያለው ልዩነት ሲጠብና ሲደበዝዝ ተስፋ ትመነምናለች። ያኔ እጅ እጅ ለሚል ኑሮ መጓጓት ይቀርና ለማያውቁት ባዕድ ሞት እጅ ላለመስጠት ብቻ ለነፍስ ማቆያ የዕለት ጉርስ ፍለጋ በዕውር ድንብር መሮጥ። የመኖር ምቾትና ለመኖር ጥንቃቄ፣ የኑሮ መሻሻልና የቁም ሕልም ሁሉ ተጠቅሎ አንድ ቀን አንደኛውን ከሚመጣው ሞት ጋር ሠፈርተኛ እንዲያስተናግደው ለዕድር የተተወ ጣጣ ይመስላል። ከአደጋም ከሕመምም  ቀድሞ በመጠንቀቅ ሕይወትን እያሳመሩ እያደነቁ እየወደዱና እየናፈቁ ትርጉም ያለው ዕድሜ ለመኖር፣ እጅ አጥሮት ተስፋው የተነጠቀን ፍጥረት በቀረችው  አልሞት ባይ ተጋዳይ ኑሮው መለየት አይከብድም። ቢያጣ የዕድር የማያጣውን ወይ ለይቶለት ይቀምሰው አጥቶ የሞተውን ደግሞ መገነዣውን ከነንፍሮ መቀቀያው በቁሙ ቋጥሮት ከሄደው የሸማ ስፌት ውስጥ ከነግድርድርነቱ ታገኘዋለህ።

ሕመሙን ሊያስታግስ፤ ቀኑ ያለፈበት መድሐኒት ቢውጥ ያው የመኖርና ያለመኖር ልዩነት ያለቅጥ ደብዝዞ ጨለማ ተጭኖት እንጂ ኪሱና ተስፋው ቢፈቅዱማ የኪኒን ገበያም ምላስና ሠንበር፣ ታላቅና ታናሽ እንዳለው ጠፍቶት አይደለም። ቁርስን አሸጋሽጎ ለምሳ ማጠቃለልን “ቁምሣ” ሲሉ ያሽሟጥጡት የነበሩ ሁሉ፣ አሁን አሁን ሲብስ ምሣንም ጨምሮ ወደ ራት በማሸማቀቅ ያንድ ቀን ውሎ በ”ቁምራ” (ቁርስ ምሳና ራት) ውክልና ይደመደማል እያሉ ሲያሽሟቅቁ ሰምቻለሁ። በዋዜማ ለዶሮ ሽመታ ወጥቶ አቅሙ ከጎመን አላሳልፍ ያለው፣  ባውዳመት አስፋልት ሲሻገር እያርጎመጎመ ግራም ቀኝም አለማየቱ አሁንም ያው ከሥጋና ከጎመን ይልቅ በመኖርና አለመኖር መካከል የደበዘዘው ብርሃን አፍዞት እንጂ ሲንፏቀቅ የደረሰ ዚታዎ በጠራራ ደፍቶት እንደሚያልፍ መች ያጣዋል። ታዲያ በዚህ ሁሉ ልምምጥና እሽሩሩ አልሸነገል ያለች ነፍስ ወይ በችጋር ወይ በአደጋ ሁሌም ቱር ብላ ባመለጠች ቁጥር ለጊዜው የቀሩት ባልንጀራ ነፍሳት፣ ለዚች ነፍስ አሟሟት የሚፈጥሩላት “ማርከሻ” ልበለው “መካሻ” ወግ ራሷ በሕይወት ሳለች ለመሪር ኑሮዋ ትፈጥርለት ከነበረው ማርከሻ ወግ መመሳሰሉንም መስተካከሉንም ልብ ይሏል። እና ባልንጀራ ነፍሳት እንዲህ ይላሉ፤ ……”መቼም እሱ ቆርጦ ካስቀመጣት ቀን ማን ሊያመልጥ ይችላል?! የሱን ቀን ማንም ሊዘላት አይችልም። ከደጅ ቢውሉ ከቤትም ቢሰበሰቡ ቀን ያው ቀን ነው፤ አንዴ ተቆርጧል!!” ሲሉ በጥቅሉ የፈጣሪ ጉዳይ ያደርጉታል። ሲሻቸው ሃላፊነቱን ለፈጣሪ ብቻ ከማሸከም ትርክቱን ወይም ወጉን ተጨማሪ ሌላ የአደጋ ሰበብ በመፍጠር ያደረጁታል። “መቼም ሰይጣን ሁሌም ተኝቶልን አያውቅም….. ይኸው ተዘጋጅቶ ጠብቆ ነው የጠራቸው፤ እንዲያውም ያ ቦታ ልማድ አለው አሉ፤ የሰው ግብር ሲቀበል ይኸው ስንት ዓመቱ? የጥሪ ጉዳይ ነዋ!!”

የዚህ ዳር ዳሩ ኑሮአችንም ሆነ ሞታችን ከኛ ቁጥጥር ውጭ ነው የሚለውን እምነት ያለክርክርና ጥርጥር ራስን የማሳመኛ መንገድ መሆኑ ነው። ሞታችንም ቀብራችንም፣ ገዳያችንም ሆነ አሟሟታችን ሃላፊም ተጠያቂም የለውም፣ ሁሉም ቀድሞ የተፃፈ ተውኔት ነው እንደማለትም ነው። የዛሬው ጉዳዬ ዋና ሐተታ እዚህ ጋ ይጀምራል።

ጥር 8 ቀን 2004 ዓ/ም ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ሲጓዝ የነበረው የስካይ ባስ ኩባንያ አውቶቡስ አባይ በረሀ ገደል ውስጥ ገብቶ ከአርባ በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ማለፋቸው ይታወሳል። የዚህ ግዙፍ አደጋ መድረስ የፈጠረው መሪር ሐዘን፣ ከአደጋው በፊትና በኋላ የተከሰተውና የተፈፀመው ሁሉ እንዲሁ ዛሬም “በአያድርስ” ብቻ ተሸፋፍነን የምናልፈው ሊሆን ባልተገባ ነበር። ከአደጋ እንደተዋዋለ ሰው የቀጠሮአቸው ቀን ቢሆን ነው ብለንስ በምሬታችን ማርከሻ ውስጥ ተሸሽገን መቅረት ይኖርብናል? እንደኔ እንደኔ ቢያንስ ጥቂቶቻችን ያየነውንና የምናውቀውን በመናገር ልንጠይቅ የሚገባንንም በመጠየቅ፣ ቀጣዮቹን መንገደኞች ከሞት መታደግ ይቻላል ባይ ነኝ። ሞቱም ሆነ ኑሮው ቢያምርም ባያምርም ሰው በሰው ልጅነቱ ብቻ ለቁም ማንነቱም ሆነ ለሙት አስክሬኑ ተገቢውን ክብር ሊያገኝ ይገባል። ለዚያውስ ከመካከላችን መንገደኛ ያልሆነ ማን አለ?

አደጋ ላገራችን የመጀመሪያ አይደለም። አያሌ የመኪናም ሆነ ያውሮፕላን አደጋዎች ከዚህ ቀደም ታይተዋል። ተወልጀ ባደግሁበት የደብረ ዘይት ከተማ የጦርና የማጓጓዣ አውሮፕላኖች በደረሱባቸው አደጋዎች እየተከሰከሱ በየጊዜው ከአርባና ከአምሳ በላይ መንገደኞች የተቃጠሉባቸው አጋጣሚዎች በቀላሉ የሚጠፉ ሥዕሎች አይደሉም። በዚያው መጠን የምስራቅ አዲስ አበባው መውጫ የደብረ ዘይቱ ጎዳና በተሽከርካሪ ጤና ችግር፣ በአሽከርካሪዎች የማሽከርከር ሥርዓት ብልሹነት የተቀሰፉና እየተቀሰፉ ያሉ የሰው ልጆችን አደጋም ደጋግሜ ተመልክቻለሁ። የመኪናው አደጋ አሰቃቂም ቢሆን የሚሸፈን አስከሬን መትረፉ አይቀርም። የአውሮፕላን ቃጠሎ ግን በልቶ የሚያስቀረው ነገር ብዙ ባይኖርም የቤተዘመድ የሐዘን ገመድ እንዲቆረጥ ለማድረግ ሲባል ግን ተቃጥሎ ባለቀው መንገደኛ ልክ አመዱ በየሳጥኖች ተከፋፍሎ፣ በቤተ ዘመዱ ፊት የሚፈፀመው የቀብር ሥነ-ሥርዓት ፍፁም ደማቅና የሁሉንም ክብር የሚጠብቅ እንደነበር አንዱ ምስክር ነኝ።

በርግጥ ከርቀት ሰማይ ወድቆ በመከስከስና በምድር ተገለባብጦ በመድቀቅ መካከል የመብረሪያውና የመሽከርከሪያው ዕቃ ኪሣራ ይለያይ እንጂ በሚጠፋው የሰው ሕይወት መካከል የጉዳት ልዩነት የለም። በመኪናም ይሁን ባውሮፕላን የተከሰተን ሞት ያው ተመሣሣይ ሞት እንጂ የመሞትና በጣም የመሞት ደረጃ ልናወጣለት አንችልም። ሁለቱም ያው የሕይወት ዕጦት፣ የዚህ ዓለም ስንብት ናቸው። እናም ያውሮፕላንን ጤና ለበረራ ቅድመ ሁኔታና ለበረራ ምቾት እንዲሁም አደጋ ሲደርስና ካደጋ በኋላ ስለሚፈፀም ለሰው ልጅ ሕይወት ክብር ለሚሰጥ ሥነ-ሥርዓት የምንጨነቀውን ግማሹን እንኳ ያህል ተውሰን በተሽከርካሪ አገልግሎትና ጥንቃቄ ላይ መሻሻል ማድረግ ለምን አቃተን? አደጋን መቀነስስ ማስቀረትስ አይሞከርም ወይ?….  በበኩሌ አዎን ሳይውሉ ሳያድሩ መቀነስም ማስቀረትም ይቻላል ነው መልሱ፡፡ ማስረጃው  ህልቆ መሣፍርት ተሽከርካሪ እየፈሰሰባቸው፣ እዚህ ግባ የማይባል አደጋ የሚከሰትባቸውን የተሽከርካሪና የመንዳት ሥርዓት ያሰፈኑ ብዙ ሀገሮችን መመልከት በቂ ነው።

የሰሞኑስ አደጋ በ”ይባስ አታምጣና” በ”ተቆረጠላቸው ቀን ነው ያለፉት” ሰበብ ውስጥ ከማንቀላፋት ከአደጋው በፊት መጠንቀቅ ይቻል ነበር ወይ ብሎ መጠየቅ አይገባም? አደጋውስ ከደረሰ በኋላ የሰለባዎቹ የመጨረሻ ሽኝት ቤተዘመድና ወዳጅ ባስቀየመና ባሳዘነ መንገድ፣  የሰውን ልጅ ክብርና የመጨረሻ መብት በዘነጋ አኳኋን መፈፀም ነበረበት ወይ ብሎ መጠየቅ አያስፈልግም? የዚህ ሁሉ መአት ሃላፊና ተጠያቂስ ማን ነው? የሚሉ ተገቢ ጥያቄዎችን ማንሳት መብትም ግዴታም ነው። ከዜግነትም በላይ የሥነ-ፍጥረት።

ማክሰኞ ጥር 8 ቀን 2004 ዓ/ም አደጋ የደረሰበት የስካይ ባስ ኩባንያ አውቶቡስ፣  የጧት ጉዞ ከቀደምቶቹ ጥቂት ዓመታት የጉዞ ግልጋሎቶች የተለየ አልነበረም። ከአዲስ አበባ መነሻው ከባከኑ ጥቂት ሰዓታት በኋላ ተነስቶ፣ ለዓባይ ድልድይ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀረው እስከገባበት ገደል ድረስ 15 ከተሞችን ማለፍ የሚጠበቅበት አውቶቡስ፤ የተጓዘበትን ፍጥነት በማስላት ያደጋውን ሰበብ መገመት እንችላለን። ግልጋሎቱ ባንድ ጊዜ ለብዙ ሰዎች የሆነ ተሽከርካሪ፣ ከግል መኪኖች በብዙ እጅ በተሻለ ተከታታይ እና የማያቋርጥ ጥንቃቄም ቁጥጥርም ሊደረግለት ይገባል። የዚህ ኩባንያ ግልጋሎት ታሪክ ግን ይህንን አያሳይም። ዛሬ በስፋት የተገልጋይን ጆሮና አይምሮ ሞልቶ የተረፈው ዝና፣ በስንት ሰዓት ተነስቶ በምንም ዓይነት የአደጋ ኪሣራ በስንት ሰዓት ፈጥኖ የመድረሱ ወሬ ብቻ ነው።

ከዚያ ያለፈውን የሚጠይቁ፣ የሚጠረጥሩ እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ሆኖም በዚህ መጓጓዣ ከተገለገሉ ውስጥ ሁሉም የሚመሠክሩት ሹፌሮቹ አውቶቡሱን ከነተሳፋሪው በሚያሽከረክሩበት ወቅት በማናቸውም መንገድ ላይ የሚያጋጥምን ዕክል ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ሳንካ ወደጎን ትቶ በከፍተኛ ፍጥነት ጥሶና አቋርጦ  ከሥምሪት ክፍሉ በሚወረወር የስልክ ማስጠንቀቂያ እየተጎተጎቱ በግዱ በሚያሽከረክር ሾፌር ከንፎ መድረስ መሆኑን ይናገራሉ።

የክልሉ መርማሪ ፖሊሶች መረጃ እንዳረጋገጠው፤ ሕገ-ወጥ የፍጥነት መጠን የጥር 8ቱ አሰቃቂ አደጋ ሰበብ ነው። በርግጥ የአውቶቡሱ ቃጠሎ በመገለባበጥ ብቻ የተፈጠረ ነው? የናፍታ መኪኖች ሜካኒካል መዋቅር ያለሌላ ሰበብ በመገለባበጥ ብቻ ለእሳት የሚያጋልጥ ነው?

ከዚህ ሌላ በአደጋው ዕለት ጥቂት ሰዓታት በኋላ በቦታው የደረሱ የተጎጂ ዘመዶች ወደ አደጋው የቃጠሎ ሥፍራ እንዳይደርሱ በምስል እንዳይቀርፁ ተከልክለዋል። አባይ ድልድይ ላይ ያደሩት እነዚህ የተጎጅ ቤተዘመዶች መገልበጥና መሞት ሳያንሰው፣ እሳት የበላው የዘመዶቻቸው ገላ ገና ዕጣው ሳይለይለት የቀጣዩ ቀን የኩባንያው አውቶቡስ ሌላ ተሳፋሪ ጭኖ፣  ትኩስ እንባ በሚያፈልቀው ዓይናቸው ፊት የዘወትር ጉዞውን መቀጠሉ በበደል ላይ በደል፣  በንቀት ላይ ንቀትን ፈጥሯል። ኋላም ሙሉ ለሙሉ የተቃጠለውንም ያልተቃጠለውንም አስክሬን የት ይቀበር የት ይወሰድ ውሳኔ ላይ የአባይ ወዲህ ማዶና ወዲያ ማዶ የፀጥታና ያስተዳደር አለቆች፣ ቤተዘመዱን አግልለው በራሳቸው የፈጠሩት አምባጓሮና የደረሱበት ስምምነት የሕግና የሞራል ጥያቄ አይነሳበትም ወይ?

ከሁሉ በላይ ደግሞ የተጎጂ ቤተዘመዶች ተጨማሪ ጉዳት የሆነው፣ ፍፁም ይቅርታ የማይባል የጭካኔ ተግባር ነው።

የሰው አካል በእሳት ሲጋይ የአስክሬን አያያዝና የቀብር አፈፃፀሙ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ለሐገራችን አዲስ አይደለም። በዚህ አደጋ ወቅት ግን ይህ የኢትዮጵያ በሣል ማህበራዊ ሥርዓት እንዳይፈፀም የከለከለ የአሕዛብ ችኩልነት ለምን እንደተመረጠ ባይገባኝም፣  ቀብሩም ያለባለቤቱ ፈቃድ ከተወሰነና አስክሬን አያያዙም ያለሥርዓቱ ከተፈፀመ በኋላ ቢያንስ መደምደሚያው ቀብር ላይ ቤተዘመድ እንዲገኝ ያለመደረጉ ነው ጭካኔው። መሞት ከዚያም በእሣት መጋየቱ ለቋሚው በቂ ሐዘን ሆኖ ሳለ፣ የሐዘኑ እንባና ሰቀቀን መጨረሻ እንዳይኖረው ቀብሩን እንዳይታደም ሆነ። ይህንን ጥልቅና ድርብርብ ሐዘን ትቶ ያለፈውን ድርጊት፣ የትኛው ሸንጎ መቼ እንደሚያነሳው እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ ሕግ እዚህ ላይ ጥያቄ እንዳለው ግን አልጠራጠርም። የሚገርመው ደግሞ እስከዚህ ደቂቃም ድረስ የፀፀትም ሆነ የጥፋተኝነት ፅዋን በጨዋነት ያነሳ ክፍል አለመታየቱ ነው።

በርግጥ ለጋራ ፀሎት መትጋት የፅድቅ ሥራ ቢሆንም ጉዳትህ አሳዝኖኛል ብሎ በሚያየው ወንድሙ ፊት በይፋ ሊፀፀት ያልወደደ ሰው፣ አይቶት በማያውቀው ፈጣሪ ፊት ለፀሎት ቢንበረከክ ንስሐው የፌዝ ስለመሆኑ ቅዱሱ መፅሐፍ ቀድሞ ተናግሮታል። ወዳጅ ዘመድ በሌለበት ወዳጅ ዘመድ ሆኖ ያዘነውና የቀበረው የደጀን ሕዝብ ግን ምሥጋና ሲያንሰው ነው።

የሆነው ሁሉ ሆኖ ለስህተት ይቅርታ፣ ለጥፋትም ቅጣት የግድ በማይሆንበት ሥፍራ በርግጥም የሰው ነፍስ ከርካሾቹ ስጦታዎች ተርታ መሰለፏን ትቀጥላለች።

 

 

Read 3026 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:11