Saturday, 21 November 2015 13:36

አሣታሚዎችና ብርሃንና ሠላም አልተግባቡም

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“በህገ መንግሥቱ የተደነገገውን የሳንሱር ክልከላ
የሚተገብር ውል ነው” አሳታሚዎች

   ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት፤ ጋዜጣ አሳታሚዎች እንዲፈርሙ ያዘጋጀው የህትመት ውል በህገመንግስቱ የተደነገገውን የሳንሱር ክልከላ የሚተገብር ነው ሲል የተቃወመው ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማህበር፤ ጉዳዩን መንግስት በአጽንኦት እንዲመረምረው በደብዳቤ ማመልከቱን አስታወቀ
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በበኩሉ፤ የተዘጋጀው ውል ከሳንሱር መቅረት ህግ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብሏል፡፡
ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት በማተሚያ ቤቱ ለሚጠቀሙ የጋዜጣ አሣታሚዎች ህዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ፤ የተወሰኑ አሣታሚዎች ማተሚያ ቤቱ ያወጣው ደንብ ላይ የጋራ ውይይት እንዲደረግ በጠየቁት መሠረት በተደጋጋሚ ውይይት ተደርጐ ድርጅቱ ከአሣታሚዎቹ በተነሱ ነጥቦች ላይ ተገቢ ማብራሪያ የሰጠ ቢሆንም አሣታሚዎች እስካሁን ድረስ ውሉን እንዳልፈረሙ ጠቁሞ፣ እስከ ህዳር 30 ቀን 2008 ዓ.ም ውሉን ፈርመው እንዲልኩ አሳስቧል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በውሉ ጉዳይ መወያየቱን ያስታወቀው የአሣታሚዎቹ ማህበር፤ ድርጅቱ ውል እንፈራረም ማለቱ ተገቢ መሆኑንና እንደሚያምንበትም ገልፆ፤ ነገር ግን በውሉ ከተዘረዘሩት አንቀፆች ውስጥ በህገመንግስቱ አንቀፅ 29 የተነሳውን ቅድመ ምርመራን የሚቃረን አንቀፅ በመካተቱ ውሉን ለመፈረም እንቸገራለን ብሏል፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 የአመለካከትና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት በንኡስ አንቀፅ 3 በተራ ቁጥር ሀ፤ “የቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ ነው” የሚለውን የጠቀሱት አሳታሚዎቹ፤ የብርሃንና ሠላም ውል ይሄን ህግ የሚጥስ ነው ብለዋል፡፡
ማህበሩ የተቃወመው የውሉ አንቀፅ 10ኛ ቁጥር 1፤ “አታሚው በአሣታሚው እንዲታተም የቀረበለት የጽሑፍ ስክሪፕት ህግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ ለማመን በቂ ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው” የሚለውንና በአንቀፁ ቁጥር 2፤ “አሣታሚው የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውጣት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማቋረጥ ወይም ለመሰረዝ ይችላል” የሚለውን ነው፡፡
ማህበሩ በውሉ ውስጥ የተካተቱትን እነዚህን ሁለት ንኡስ አንቀፆች እንደማይቀበልና ከውሉ መውጣት አለባቸው ብሎ እንደሚያምን ጠቁሟል፡፡
ለመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በላከው ደብዳቤም፤ እነዚህ የውል አንቀፆች በህገ መንግሥቱ የተከለከለውን ቅድመ ምርመራን የሚተገብሩ ስለሆነ መንግስት ጉዳዩን በአጽንኦት መርምሮ አንቀፆቹ ከውሉ እንዲወጡለት ጠይቋል፡፡
ማህበሩ ለብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት በላከው ደብዳቤ፤ ቀደም ሲል በተካሄዱ ውይይቶች ላይ እነዚሁ አንቀፆች እስካልተወገዱ ድረስ ውሉን ለመፈረም እንደማይችሉ መግለፃቸውን በማስታወስ፣ በድጋሚ ፈርሙ የሚል ማሳሰቢያ መተላለፉ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ቀጣይ ውይይት እንዲካሄድም ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
በማተሚያ ድርጅቱ የተዘጋጀው ውል ለፊርማ ከቀረበ ወደ 4 ዓመት ገደማ ሲሆነው አሳታሚዎችና ማተሚያ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ ውይይት ቢያደርጉም በውሉ ላይ ሙሉ ለሙሉ መግባባት አልቻሉም፡፡
የማተሚያ ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተካ አባዲ በበኩላቸው፤ የተዘጋጀው ውል አለማቀፍ ባህሪ ያለው መሆኑ ታምኖበት ሁሉም የመንግሥት ማተሚያ ድርጅቶች ተወያይተውበት ተግባራዊ የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
አሳታሚዎቹ የተቃወሙት አንቀፅ፤ “አገርን የሚያፈርስ ዘገባ ካለ አላትምም” የሚል ነው ያሉት አቶ ተካ፤ እንደ አንድ የመንግሥት ተቋም፣ የህዝብንና የሀገርን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ስላለብንና በህግም ስለምንጠየቅ ውሉን ለማስፈረም እንገደዳለን ብለዋል፡፡ “ውሉ በህገ መንግሥቱ ከተደነገገው የሣንሱር መቅረት ህግ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤ ሌሎች የመንግሥት ጋዜጦች ውሉን ፈርመው አገልግሎት እያገኙ ነው” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የግል ፕሬስ ባለቤቶችም ጉዳዩን የፖለቲካ ፍላጎት ማንፀባረቂያ ሊያደርጉት አይገባም ብለዋል፡፡
“አሁንም ያለ ውል መስራታችን ተገቢ አይደለም፤ ውሉን በተመለከተ ያቀረቡትን ቅሬታ የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ይመክርበትና ይወስናል፤ ከመንግሥት የሚሰጥ አቅጣጫ ካለም እናያለን” ብለዋል፤ አቶ ተካ አባዲ፡፡

Read 2424 times