Saturday, 21 November 2015 13:39

በኢትዮጵያውያን ሴት አብራሪዎች የተመራ አውሮፕላን ወደ ባንኮክ በረራ አደረገ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

   የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያውያን ሴት አውሮፕላን አብራሪዎች ብቻ ከአዲስ አበባ ወደ ታይላንድ ባንኮክ የደርሶ መልስ በረራ ከትናንት በስቲያ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ ዋና አብራሪም ሆነ ረዳት አብራሪ፣ ቴክኒንና የበረራ በቦይንግ 767 አስተናጋጆቹ እንዲሁም ተቆጣጣሪዎች ሙሉ በሙሉ ሴቶች ብቻ የሆኑበትን በረራ ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄደው “ቀጣይነት ላለው ልማት ሴቶችን ማብቃት” በሚል መርህ ነው ተብሏል፡፡በበረራው ወቅት ቲኬት ቆራጮች፣ የበረራ ደህንነት ባለሙያዎችና የደንበኞች እቃ ጫኞች ጭምር ሙሉ ለሙሉ ሴቶች ብቻ የነበሩ ሲሆን ተሳፊሪዎቹ ግን አብዛኞቹ ወንዶች እንደነበሩ ታውቋል፡፡
በቦይንግ 767 የተከናወነውን በረራ በዋና አብራሪነት ካፒቴን አምሣለ ጓሉ በረዳት አብራሪነት ሠላም ተስፋዬ መርተውታል፡፡አየር መንገዱ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመት በሚያከብርበት ዋዜማ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ማከናወኑ ታላቅ ስኬት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ፤ ከአየር መንገዱ ሠራተኞች 30 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡በሌላ በኩል የወንዶች የበላይነት የገነነበት እንደሆነ በሚነገርለት የዚምባቡዌ አየር መንገድ ባለፈው ማክሰኞ  ሙሉ በሙሉ በሴቶች የተመራ የአገር ውስጥ በረራ ከመዲናዋ ሀራሬ ወደ ቪክቶሪያ ፏፏቴ ማድረጉ ታውቋል፡፡ቦይንግ 737 – 200 አውሮፕላን በሀራሬ ሰማይ ላይ ያበረሩት ካፒቴን ቺና ማቲምባና ካፒቴን ሲምቢ ጴጥሮስ ሲሆኑ ዋና አብራሪዋ ካፒቴን ማቲምባ ከበረራው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠችው አስተያየት፤ “ታሪክ ሰርተናል” ብላለች፡፡ ረዳት አብራሪዋ ሲምቢ በበኩሏ፤ “እንዲህ ያለውን ታሪካዊ በረራ በማከናወኔ እድለኛ ነኝ” ስትል ስሜቷን ገልፃለች፡፡የሁለቱን እንስቶች የተሳካ በረራ ያደነቁት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን፤ አየር መንገዳቸው የሴቶችን ድርሻ የበለጠ ለማስፋት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡በዚምባቢዌያኑ እንስቶች ኩራት እንደተሰማው የገለፀው አለማቀፉ የሴት አብሪሪዎች ማህበር፤ በአለም ላይ ካሉ አብራሪዎች የሴቶቹ ድርሻ 6 በመቶ ብቻ መሆኑን አመልክቶ፣ አገራት በዘርፉ በርከት ያሉ ሴት ባለሙያዎችን ማፍራት እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡

Read 4803 times