Saturday, 21 November 2015 13:36

ዳሽን ቢራ - ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን ያስተሳሰረ ፋብሪካ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

    ባለፈው ሳምንት በደብረብርሃን ከተማ የተመረቀው ግዙፍና እጅግ ዘመናዊ የተባለው ዳሽን ቢራ ፋብሪካ፣ ጥረት ኢንዶውመንት ዱዌት - ቫሳሪ ከተባሉ ሁለት የእንግሊዝ ኩባንያዎች ጋር በእኩል 50፣ 50 የአክሲዮን ድርሻ የተቋቋመ ፋብሪካ ነው፡፡ የዛሬ 20 ዓመት የተቋቋመው ጥረት ዳሽን ቢራ ፋብሪካን ጨምሮ ተመጋጋቢ ፋብሪካዎችንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማቋቋሙ ስኬታማ አድርጎታል ተብሏል፡፡ጥረት የዛሬ 15 ዓመት በጎንደር ከተማ ዳሽን ቢራ ፋብሪካን መሰረተ፡፡
እዚያው ጎንደር ከተማ ለቢራ ፋብሪካው ብቅል የሚያቀርብ የብቅል ፋብሪካ በባህርዳር ከተማ፣ ለቢራ ፋብሪካው የጠርሙስ ሳጥን የሚያመርት ተክራሮት የተባለ ፋብሪካ፣ በኮምቦልቻ ቆርኪ የሚያመርት ዋሊያ ቆርኪና ጣሳ ፋብሪካ አቋቋመ፡፡
ከውጭ አገር የሚገዙ ዕቃዎችን አምባሰል የንግድ ድርጀት ያቀርባል፡፡ ወደብ ላይ የደረሱ ዕቃዎችን ክሊራንስ በለሳ ያከናውናል፡፡ ዕቃዎቹን ከወደብ አንስቶ ወደ አገር ውስጥ የሚያጓጉዘውና በየፋብሪካው የሚያደርሰው ደግሞ ጥቁር አባይ የተባለው የትራንስፖርት ድርጅት ነው፡፡
 ጥቁር አባይ የዳሽን ፋብሪካ ምርቶችንም ለደንበኞች ያደርሳል ብለዋል፤ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ታደሰ ካሳ፡፡ በክብር እንግድነት ተገኝተው ፋብሪካውን የመረቁት ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ እጅግ ዘመናዊ በሆኑ መሳሪያዎች የተደራጀው ዳሽን ቢራ ፋብሪካ የአገራችን የግል ድርጅቶች፣ ከዓለም አቀፍ ታዋቂ ድርጅቶች ጋር በመጣመር ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የኢንዱስትሪ አመራር እውቀትና ክህሎት ለመጎናፀፍ በሚያስችል ደረጃ ላይ መሆናቸውን ያመለክታል አርሶ አደሮችንም ምርታማ ያደርጋል ብለዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም፣ ፕላስቲክ፣ ቆርኪና ጠርሙስ አምራች ከሆኑና በደቡብ አማራ ክልል ከተገነቡ ተቋማት ጋር የምርት ትስስር የፈጠረ እንደሆነ ጠቅሰው፣ “ቢራ በማምረት ላይ ብቻ ሳይወሰን የአገራችንን ባህል በዓለም ደረጃ በማስተዋወቅ የአርሰናል ታዋቂ ተጫዋቾችን ሳይቀር እስክስታ ያስወረደ ቢራ ፋብሪካ ነው” በማለት ዳሽን ቢራ ፋብሪካን አሞካሽተዋል፡፡
ፋብሪካው ግብር በመክፈል አርአያ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው፡፡ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ቤልጂየምና ቻይና ከሚገኙት የቢራ ፋብሪካዎች ቀጥሎ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸው እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች የተገጠሙለት ሦስተኛው ቢራ ፋብሪካ ነው ያሉት የዳሽን ደብረብርሃን ፋብሪካ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ መኮንን፤ ግንባታው ሁለት ዓመት ከመንፈቅ መውሰዱን፣ የፋብሪካው አጠቃላይ ወጪ 3 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 2 ቢሊዮን ብር ለመሳሪያዎች ግዢ፣ 1 ቢሊዮን ብር ለውጭና ለአገር ውስጥ አማካሪዎች፣ ለግብአት አቅርቦትና ለሥራ ማስኬጃ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው፣ በ2 ሚሊዮን ሄክቶሊትር (1 ሄክቶሎትር 100 ሊትር ነው) ወደ ገበያ እንደሚገባና ትንሽ ማሻሻያ ተደርጎለት 3 ሚሊዮን ሄክቶሊትር እንደሚያመርት ጠቅሰው፣ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር አሁን የጎንደር ፋብሪካ ከሚያመርተው 1.5 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ጋር በአጠቃላይ 4.5 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ በዓመት ያመርታል ብለዋል፡፡
 አቶ ደሳለኝ፣ ፋብሪካው 40 ሺህ ኩንታል ብቅል መያዝ የሚችሉ 8 የሳይሎን፣ 4ሺህ 800 ሄክቶ ሊትር የመያዝ አቅም ያላቸው 12 የጥንስስ ጋኖች፣ ቢራው ወደ ሙሌት ከመሄዱ በፊት የሚቆይበት እያንዳንዳቸው 2 ሺህ 400 ሄክቶ ሊትር የሚይዙ 5 ታንኮች እንዳሉት ጠቅሰው፣ በሰዓት 45 ሺህ ጠርሙሶች የሚሞሉ ሁለት መስመሮች፣ (90 ሺህ) በሰዓት 100 ሊትር የሚሞላ የድራፍት መሙያ ማሽን እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ በግንባታ ወቅት 1200 የአካባቢው ነዋሪዎች የተለያየ የሥራ መስክ የተሳተፉ ሲሆን፣ በ245 ቋሚና በ450 ጊዜያዊ ሠራተኞች ሥራ እንደሚጀምር የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

Read 3950 times