Saturday, 14 November 2015 09:46

በስኳር በሽታ የሚያዙ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(9 votes)

     ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ፣ የስኳር ህመምተኛ የሆነ ልጅን ማሳደግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ ራስን በቦታው ላይ አድርጎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለህመሙ የሚስማሙ (የሚፈቀዱ የተወሰኑ ምግቦችን ብቻ ለማግኘት ያለው ጭንቅ፣ በየጊዜው ከሚከሰተው ድንገተኛ ህመምና ችግር ጋር መጋፈጡ፣ ከአሁን አሁን ልጄን ምን ያጋጥመው ይሆን እያሉ በስጋት መናጡ ሁሉ… እጅግ ፈታኝ ነው፡፡
“ልጄ የስኳር ህመም እንዳለበት ያወቅሁት ገና በስድስት ዓመት ዕድሜው ላይ ነበር፡፡ በዚህ ዕድሜው አብሮት በሚዘልቅ ህመም መያዙ በጣም ቢያሳዝነኝም ሁኔታውን ተቀብዬ፣ ለልጄ ማድረግ የሚገባኝን ማድረግ እንዳለብኝ ራሴን በማሳመን፣ በመርፌ የሚሰጠውን መድኀኒት እንዲጀምር አስደረግሁት፡፡ ዛሬ ልጄ 11 ዓመቱ ሲሆን የ5ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ የኢኮኖሚ አቅሜ ደካማ በመሆኑ፣ ልጄን በግል ትምህርት ቤት አስገብቼ ለማስተማር ባልችልም በመንግስት ት/ቤት ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል፡፡ የገቢዬ ደካማ መሆን ከሁሉ በላይ የጎዳኝ ለልጄ አስፈላጊ የሆኑ ምግቦችና መድኀኒቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ እንዳልችል በማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ራሱን ከትምህርት ቤት ይዘውልኝ ሲመጡ መፈጠሬን እስከመጥላት እደርሳለሁ፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የስኳር ህመም ትኩረት አግኝቶ የአደባባይ መነጋገሪያ መሆኑ ለእኔና እንደእኔ ላሉ እናቶች ትልቅ እፎይታን ሰጥቶናል፡፡ አሁን መድኀኒቶቹም በገበያ ውስጥ እንደልብ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁሉ ለእኛ ምን ማለት እንደሆነ ልገልፅልሽ አልችልም፡፡”   
እንዲህ እያሉ ችግራቸውን ያወጉኝ የ11 ዓመት የስኳር ህመምተኛ ልጅ ያላቸው ወ/ሮ ገነት ታደሰ ሲሆኑ ያገኘኋቸውም ሰሞኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የአለም የስኳር ህመም ቀን አስመልክቶ፣ የኢትዮጵያ የስኳር ህመም ማህበር ባዘጋጀውና “የሚራመዱት ለእኔ ነው” በሚል መርህ ባለፈው እሁድ በተካሄደው የእግር ጉዞ ላይ ነው፡፡ በዚህ የእግር ጉዞ እንደ እሳቸው ሁሉ ህፃናት ልጆቻቸው በስኳር ህመም የተያዘባቸው ወላጆችና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ፕሮግራሙ በስኳር ህመም ላይ የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግና በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ መጠን እያደገ የመጣውን የህፃናት በስኳር ህመም መያዝ አስመልክቶ ግንዛቤ ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
የዓለም አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዓለማችን በአሁኑ ወቅት 387 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 20 ሚሊዮን ያህሉ የሚገኙት በአፍሪካ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከህሙማኑ 2.1 ሚሊዮን የሚሆኑት የሚገኙባት አገር ሆናለች፡፡ የስኳር ህመም ከህፃናት እስከ አዋቂ የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስኳር በሽታ የሚያዙ ህፃናት ቁጥር እያደገ መምጣቱን መረጃው አመላክቷል፡፡
በ2025 እ.ኤ.አ በአፍሪካ በስኳር ህመም የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ እንደሚጨምር ያመለከተው የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠቁ አገራት ተርታ እንደምትመደብ ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር አህመድ ረጃ እንደሚናገሩት፤ በዓለማችን ከስኳር ህመም ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ አንደኛው ዓይነት የስኳር ህመም በተለይም በህፃናትና በወጣቶች ላይ በስፋት ይታይ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም፣ በህፃናቱ ላይ በስፋት መታየት መጀመሩ ሁኔታው እጅግ አሣሣቢ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡ በስኳር ህመም የሚጠቁ ህፃናት በአብዛኛው ከመጠን በላይ ወፍራም የሆኑ፣ በቤተሰባቸው የስኳር ህመም ታሪክ ያላቸው፣ የአመጋገብ ሥርዓታቸው ያልተስተካከለና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማያደርጉ ልጆች መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር አህመድ፤ ህፃናቱን ከበሽታው ለመከላከል ቅባትና ቅመም የበዛባቸው ምግቦችን እንዲሁም ጣፋጭና ፈጣን ምግቦችን ከመመገብ እንዲቆጠቡ ማድረግ፣ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን እንዲከተሉና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እንዲያዘወትሩ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡  
በስኳር ህመምተኛ ህፃናት ላይ በስፋት ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ የሆነው በደም ውስጥ ስኳር ማነስ (ሀይፓግላይስሜያ) በርካታ ህፃናትን ለከፋ ችግርና ጉዳት እየዳረገ መሆኑን የሚገልፁት ዶክተር አህመድ፤ ችግሩ በተለይ ኢንሱሊን በሚወስዱ የስኳር ህመምተኛ ህፃናት ላይ በስፋት እንደሚታይና ህብረተሰቡ ስለችግሩ በቂ ግንዛቤ ኖሮት፣ ህፃናቱ ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ እርዳታ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የደም ውስጥ ስኳር ህመምተኛ ህፃናት ላይ በስፋት እንደሚታይና ህብረተሰቡ ስለችግሩ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ህፃናቱ ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ እርዳታ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የደም ውስጥ ስኳር ማነስ (ሀይፓግላይስሜያ) ሲከሰት ታማሚዎቹ ከሚያሳይዋቸው ምልክቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ማንቀጥቀጥ፣ ማላብ፣ የልብ ምት መጨመር፣ የፊት መገርጣት፣ የድካም ስሜት ማሳየት፣ ማቅለሽለሽ፣ መቃዠትና ራስን መሳት እንደሆኑና እነዚህ ምልክቶች በታዩ ጊዜ የስኳር መጠንን ለማስተካከል የሚረዱ ጣፋጭነት ያላቸውን መጠጦች መስጠት እንደሚገባ ዶክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ለስኳር መጠን መቀነስ የሚሰጠው ህክምና ዓላማው፣ የስኳርን መጠን ወደ ትክክለኛው መጠን መልሶ ማስተካከልና ምልክቶቹን ማጥፋት ነው፡፡ ጣፋጭነት ያላቸውን መጠጦች በመስጠት የልጁን የስኳር መጠን ለማስተካከል ያደረግነው ሙከራ ካልተሳካ ወይም ጣፋጭ መጠጡን ከወሰደ ከ15 ደቂቃ በኋላ የስኳር መጠኑን ለክተን የሚያንስ ከሆነ፣ ሌሎች አማራጮችን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ የልጁ የስኳር መጠን በጣም ዝቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ መብላትና መጠጣት ካቃተው፣ በደም ስሩ 10 በመቶ ወይም 25 በመቶ ጉሉኮስ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ልጁ በስኳር ማነሱ ሳቢያ ራሱን ከሳተ፣ በጎን አስተኝቶ የአየር ቧንቧው እንዳይዘጋና የትንፋሽ ማጠር ችግር እንዳያጋጥመው ማድረግ ይገባል፡፡ የስኳር ህመም ያለባቸው ልጆች፤ የስኳር መጠን መቀነስ ችግር የሚያጋጥማቸው ምግብ ሳይመገቡ ከቀሩ አሊያም የተመገቡት ምግብ መጠኑ አነስተኛ ከሆነ ወይም ኢንሱሊኑን ከወሰዱ በኋላ ምግብ ሳይበሉ ከዘገዩና የህመም ስሜት ኖሮአቸው የምግብ ፍላጎታቸው ከቀነሰ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ የስኳር ህመም ያለባቸው ልጆች በአጭር ቆይታ ቶሎ ቶሎ እንዲመገቡ በማድረግና ኢንሱሊን ከወሰዱ ከ30 ደቂቃ በኋላ ምግብ መመገባቸውን በማረጋገጥ ችግሩ እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል፡፡
የስኳር ህመም መዳን የማይችል ቢሆንም መቆጣጠርና ሰላማዊና የተስተካከለ ህይወትን መምራት ይቻላል፡፡ አንድ ሰው በስኳር ህመም ለመያዙ ዋንኛ ምልክቶቹ ያልተለመደ የምግብ ፍላጎት መጨመር፣ ውሃ ቶሎ ቶሎ መጠጣት፣ ሽንት አሁንም አሁንም መሽናት፣ የሰውነት ክብደት መቀነስና የአፍ መድረቅ ናቸው፡፡ ሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም ግን ምንም አይነት ምልክት የሌለው ሲሆን የበሽታው መኖር የሚታወቀው የጤና ሁኔታችን የከፋ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚለው፤ በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ለመጣው የስኳር ህመም ዋንኛ ምክንያቶቹ የከተሞች መስፋፋትና የዘመናዊ መጓጓዣዎች መብዛት፣ ሰው ልጅ እንቅስቃሴን መገደባቸው፣ ቢሮ ውስጥ ተቀምጠው በኮምፒዩተርና በዲጂታል ሲስተም የሚሰሩ ስራዎች መበራከታቸው፣ ጉልበት የሚጠይቁ ስራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መተካታቸው፣ የፈጣንና ጣፋጭ ምግቦች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሄድ፣ የአመጋገብ ስርዓቱ ወደ እንስሳት ተዋፅኦ ማድላቱና አካላዊ እንቅስቃሴ አለማዘውተር ናቸው፡፡
የዘንድሮው የዓለም የስኳር ህመም ቀን መሪ መልዕክት፤ “ጤናማ አኗኗርና የስኳር ህመም” የሚል ነው፡፡

Read 11215 times