Saturday, 14 November 2015 09:35

ባቡሩ በቀን 400 ሺህ ብር እያስገባ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

በግማሽ አቅሙ ብቻ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት፤ በቀን እስከ 400 ሺህ ብር ገቢ እያስገባ ነው ተባለ፡፡ የዛሬ ሁለት ወር ባቡሩ ከቃሊቲ ሚኒልክ አደባባይ በተዘረጋው መስመር  አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ ባለፈው ማክሰኞ ሁለተኛው መስመር፣ ከአያት አደባባይ ጦር ኃይሎች፣ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
በመስመሩ ከተመደቡት 21 ባቡሮች 10ሩ ብቻ ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን የጠቆሙት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ ቦጋለ፤ ከቃሊቲ ሚኒሊክ አደባባይ በተዘረጋው መስመርም ከተመደቡት 20 ባቡሮች በአሁን ወቅት እንደተገልጋዩ መጠን እስከ 15 የሚደርሱ ባቡሮች ብቻ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ መስመሮቹ በርካታ የእግረኛና የተሽከርካሪ ማቋረጫ ያላቸው በመሆኑ ባቡሮች ከትራፊክ ፍሰቱ ጋር እስኪቀናጁ ቅድመ ጥንቃቄ ለመውሰድ ሲባል ነው ብለዋል፡፡
ሙሉ ለሙሉ መናበብ ከተፈጠረ በኋላ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በሙሉ አቅም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል፡፡የባቡር ትራንስፖርትአገልግሎቱን የሚሰጡት የቻይናዎቹ ኩባንያዎች ግንባታውን ያከናወነው CREC እና ሼንዙ ሜትሮ በጋራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሄኖክ፤ ኩባንያዎቹ የ3 ዓመት ከ6 ወር ኮንትራት ወስደው አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረገው የቴክኒክ ችግር ቢያጋጥም ግንባታውን ያከናወነው ኩባንያ የጥገና ኃላፊነቱን እንዲወስድ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ለ41 ወራት ኮንትራትም ለቻይና ኩባንያዎች 116 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በቅድሚያ መፈፀሙን ጠቁመው፤ ኮንትራቱ ባቡሮችን መጠገንና መገንባት እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን አቅም መገንባትን የሚያካትት ነው ብለዋል፡፡
በግማሽ አቅሙ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ፤ በአሁን ወቅት በሁለቱ መስመሮች በቀን በአማካይ እስከ 400 ሺህ ብር ገቢ እያስገኘ እንደሆነና ገቢውም ሙሉ ለሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ባቡር ዝግ ሂሳብ በቀጥታ እንደሚገባ ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
 ፕሮጀክቱ የተከናወነበትን ከቻይና የተገኘ ብድር ለመክፈል አሁን ያለው የቲኬት ሽያጭ ፈፅሞ የሚያዋጣ አይደለም ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ በቲኬት ሽያጭ ብድሩ ይከፈል ከተባለ ቢያንስ ለአንድ ጉዞ አንድ ተገልጋይ ከ25 እስከ 30 ብር ክፍያ መጠየቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ይህ የማይቻል በመሆኑ ለብድር አመላለሱ ሁለት የድጎማ አማራጮች ቀርበው ኮርፖሬሽኑ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፤ አንደኛው አማራጭ በየባቡር ጣቢያዎች የንግድና የሲኒማ ማዕከሎችን ያካተቱ ስቴሽን ሞሎችንና አፓርትመንቶችን ገንብቶ በማከራየት ከሚገኝ ገቢ ለመክፈል የታሰበ ሲሆን በሁለተኛ አማራጭነት ደግሞ የባቡር ትራንስፖርት ራሱ ዜሮ የካርፖን ልቀት ያለው በመሆኑ ለአየር ፀባይ ለውጥ መከላከል ባቡሩ ለሚኖረው አስተዋፅኦ ከሚገኝ አለማቀፍ ገቢ ብድሩን ለመመለስ ታቅዷል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በሁለተኛው ምዕራፍ የባቡር ፕሮጀክት ማስፋፊያውን ለማከናወን በእቅዱ ላይ የፓርላማው ውሳኔ እንደሚጠበቅ የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ቀደም ሲል በእቅድ ደረጃ 32ሺ ሜትር የሚረዝም በሁለት አቅጣጫዎች የሚዘረጋ የሃዲድ መስመር ለመገንባት መታቀዱ መገለፁ የሚታወስ ነው፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ ይጀመራል ተብሎ ከተያዘው እቅድ ከመገናኛ - በቦሌ - ሳሪስ ለቡ የሚደርሰውና ከፒያሳ ሚኒልክ አደባባይ - በቸርችል ጎዳና - ሜክሲኮ - አፍሪካ ህብረት አድርጎ ለቡ የሚደርሰው በዋናነት የተጠቀሰ ሲሆን ከአያት ለገጣፎ፣ ከሚኒሊክ አደባባይ - ሽሮ ሜዳ፣ ከጦር ኃይሎች - ለቡ - አለም ባንክ በማስፋፊያ እቅዱ ውስጥ ተካተዋል፡፡  


Read 8844 times