Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 February 2012 10:00

ተቃዋሚ ፓርቲ ስልጣን ይይዛል ብዬ አስባለሁ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አቶ ግርማ ሰይፉ-የአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር

ህገመንግስቱ ከዚህ መጽሐፍ ላይ የጨመረም የቀነሰም ይቀሰፋል አይልም…

ህብረተሰቡ አሸባሪ አለመሆናችንን ስለሚያውቅ ችግር አይፈጠርም…

በፓርላማ ሃሳብ ሰጥቼ አንድም ቀን ተቀብለውኝ አያውቁም…

መኮረጅ አንፈራም፤ አሪፍ ከሆነ ከኢህአዴግም እንኮርጃለን…

በተወካዮች ም/ቤት ብቸኛው የተቀዋሚ ፓርቲ አባልና የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ም/ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ጠ/ሚኒስትሩ ሰሞኑን በፓርላማ በሰጡት መግለጫ ዙሪያና በሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

ህገ መንግስቱን በተደጋጋሚ የምትጠቅሱት ስለምታምኑበት ሳይሆን እንደ ሁኔታው ልትጠቀሙበት ስለምትፈልጉ ብቻ ነው ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ተችተዋችኋል…ህገመንግስቱን የምንጠቅሰው ስለሚጠቅመን ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ህገመንግስቱ ቤቴ፣ ቢሮዬ፣ መኪናዬ… ውስጥ አለ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ያለኝን ያህል ህገመንግስቱ አለኝ፡፡ እነሱ የራሳቸውን ፍርድ መስጠታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለምሳሌ እኔ መጽሐፍ ቅዱስ ይሻሻል ብዬ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ መጽሐፍ ላይ የጨመረም የቀነሰም ይቀሰፋል ይላል፤ ይሄ ህገመንግስት ግን እንደዛ አይልም፡፡ በህገመንግስቱ አንቀጽ 104 ጀምሮ ያሉ አንቀፆች ህገመንግስቱ እንዴት መሻሻል አለበት የሚለውን የሚያብራሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ህገመንግስት ይሻሻላል ማለት ነው፤ እኛ ደግሞ ህገመንግስቱ እንደሚሻሻል እናምናለን፡፡ ይሄ ማለት ግን ህገመንግስቱን ጥሩ ነገር የለውም ማለት አይደለም፡፡ ጥሩ ነገሮች አሉት፡፡ ለምሳሌ የዜጐች መብት እንዲከበር ይደነግጋል፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ እኛም እየጠየቅን ያለነው ህገመንግስቱን መንግስት እንዲከበር ነው፡፡ ይሄ ህገመንግስት የተቋቋመው በዋነኛነት የዜጐች መብት እንዲከበር እና የዜጐችን መብት የሚጥሰው መንግስትን በማዕቀፍ ውስጥ ለማስቀመጥ ነው፡፡ መጽሐፉ ህገ ህዝብ አይልም ህገመንግስት እንጂ፡፡ መንግስት ይህንን እንዲያከብር የተሠራ ፍሬም ነው፡፡ ይህ መንግስት እዚህ ውስጥ ያሉትን ድንጋጌዎች እንዲያከብርልን ነው እየጠየቅን ያለነው፡፡ እነሱ ግን አያከብሩትም፤ እንደፈለጉ አድርገው የሚጠቅሷቸው አንቀፆች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንቀጽ 21 ቁጥር 2 ላይ፣ በጥበቃ ስር ያሉ ግለሰቦችን መብት ይመለከታል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ወዳጆቻቸው፣ ከሀይማኖት አባቶቻቸውና ከሀኪም አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና የመጐብኘት መብት አላቸው ይላል፡፡

ይህንን በአዋጅ ማሻሻል፣ በአሠራር ማሻሻል አይቻልም፡፡ የወህኒ ቤቱ መመሪያ እና ቢፒ አሩ የህገመንግስቱን ድንጋጌዎች ተከትለው አይሰሩም፡፡ በዚህም የተነሳ ህገመንግስቱን የሚንዱት እነሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጐች በፍ/ቤት እስካልተወሰነባቸው ድረስ ንፁህ ናቸው እንላለን፤ እነሱ ተነስተው ወንጀለኛ ናቸው ስላሉ ወንጀለኞች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ሊፈርድ የሚችለው ፍ/ቤቱ ነው፡፡ በቦክስ ስለተመታሁ በቦክስ መምታት የለብኝም፤ ፍ/ቤት ነው መሄድ ያለብኝ፤ ስለዚህ እኛ ካጠፋን ፍ/ቤት ነው ሊጠይቀን የሚችለው መንግስት ይሄንን ህገ መንግስት ካከበረልን እኛ ነን የምንጠቀመው ብለን ነው የምናስበው፡፡ አሁን ባለን ሁኔታ ይከበርልን ነው የምንለው፡፡ ይለወጥልን የምንለውም አለ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አሸባሪ መሆናቸውን እናውቃለን ማለታቸውን በተመለከተስ?

መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆነን አሸባሪ መሆናቸውን እናውቃለን ብለዋል፡፡ በመረጃ መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ መረጃ አቅጣጫን ያመለክታል፡፡ በዛ መሠረት ማስረጃ ይገኝና ሰዎች አሸባሪ መሆናቸው ሲረጋገጥ ያን ጊዜ መቶ በመቶ ይሆናል፡፡ አሁን በመረጃ መቶ በመቶ እርግጠኛ ነን ያሉ ማስረጃ ሲያገኙ አንድ ሺህ በመቶ ሊሉ ነው?

አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶች መረጃ ሰብስበው ሌላ ሰውን ያስራሉ አቅጣጫቸው የተሳሳተ መሆኑን በማስረጃ ሲያረጋግጡ ግን ይለቃሉ፡፡

እንዲህ መባላችሁ በፓርቲያችሁ ላይ ችግር አይፈጥርም?

ማህበረሰቡ አሸባሪ አለመሆናችንን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ምንም የሚፈጠር ችግር የለም፡፡ እኔ ሽጉጥ መተኮስ እንኳን አልችልም፤ እንኳን በሽብር ልሰማራ፡፡ የአሸባሪ ስነ ልቦና ባህሪይ ደግሞ አለ፡፡ እኛ ፓርቲያችን ውስጥ አሉ የምንላቸው ሰዎች ከአሸባሪዎች ጋር እንደዚህ አይነት ግንኙነት ያላቸው አይደሉም፡፡ የአሸባሪነት ስነ ልቦና ያላቸው ሰዎች በቤተሰቦቻቸው ፣ በማህበረሰቡ ባህሪያቸው ያስታውቃሉ፡፡

የፓርላማ አባላት በእርስዎ አስተያየት ወይም ለእርስዎ በሚሰነዘር መልስ በተደጋጋሚ ይስቃሉ…

በእኔ ጥያቄ አይመስለኝም የሚስቁት ሆኖም ጠ/ሚኒስትሩ በየስድስት ወሩ አንዴ እየመጡ ቢያስቋቸው ምንም ክፋት የለውም የተመረጡት ለመሳቅ ከሆነ እነሱ ናቸው የሚያውቁት፡፡ እኔ እንደምታዩኝ ቁጭ ብዬ የተመረጥኩበትን አላማ ሠርቼ ነው የምወጣው፡፡

ብቸኛ የፓርላማ ተወካይ ከመሆንዎ አንፃር ምን ይሰማዎታል?

ምንም አይሰማኝም፤ የሚረዳኝ ሰው ቢኖር ደስ ይለኝ ነበር፡፡ አሁን ስራ ይበዛብኛል፤ ብቻዬን ስሆን፡፡

ወደፊት ፓርላማው እንደ ሌሎች አገሮች ፓርላማ የተለያዩ ፓርቲዎች በብዛት የሚቀመጡበት ይሆናል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ?

እኔማ ተስፈኛ ነኝ፤ ይሄ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

በመንግስት ሚዲያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ይካሄዳል ተብሏል፡፡ መድረክ ወይም አንድነት ፓርቲ አይሳተፉም፡፡ ተከልክሎ ነው ወይስ ራሱ አግልሎ?

አልተጠራንም የነገረንም የለም፡፡ እኛ ከህዝብ ጋር ሊያገናኘን በሚችል በማንኛውም ቀዳዳ እንጠቀማለን አንድም የምናባክነው ነገር የለም፡፡ የማይጠሩን ግን ስለሚያውቁን ነው፤ ማን ይከራከረናል ብለው ስለለዩና አማራጫችንን በደንብ አድርገን ለህዝቡ እንደምናሳይ ስለሚያውቁ ነው፡፡

የሊዝ አዋጅ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አጀንዳ ሆኗል በቀጣይ የአዲስ አበባ ምርጫ ዋና ርዕስ የሚሆን ይመስልዎታል?

ጠ/ሚኒስትሩ እንደማያሻሽሉት ገልፀዋል፤ እንግዲህ በምርጫ ጊዜ “የማትሰሙን ከሆነ ይሄንን እናደርጋለን” ብለን መግለጽ ይኖርብናል፤ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ እነሱ የሚፈልጉት ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሁላችንም ኮንዶሚንየም ቤት ውስጥ እንድንኖር ነው፡፡ እዛ ኖረን 20 ፐርሰንት ከፍለን፣ 80 ፐርሰንት ደግሞ የ20 አመት ዕዳ ውስጥ እንድንገባ ነው የሚፈልጉት፡፡ የመንግስት እዳ ያለበት የመንግስት ጭሰኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንድ ነገር ብታደርጊ “ከቤትሽ አስወጣሻለሁ” እያለ ያስፈራራል ማለት ነው፡፡ ከቀበሌ ቤት አስወጥተው ወደ ዘመናዊ የቀበሌ ቤት (ኮንዶሚንየም) ያስገባሉ ማለት ነው፡፡ በዚህም የ20 አመት ዕዳ ያለበት የኢህአዴግ አባል ይሆናል፤ ይሄ ረጅም ዕቅድ ነው፡፡

አዋጁ ላይ ጥሩ ነው የሚሉት ነገር አለ?

አለ ለምሳሌ መረጃ ያልተሟላለት ቦታን ለሊዝ ጨረታ የሚያቀርብ ኃላፊ ይጠየቃል የሚል አለ፡፡ የሊዝ ጊዜው ይራዘምልኝ ብሎ የጠየቀ ይሄ ሳይደረግለት ለሚከሰት ችግር ሀላፊው ይጠየቃል ይላል፡፡ ይሄ ነው የሀላፊነት ተጠያቂነት የምንለው፡፡ ከዚህ አንፃር ጥሩ ነው እላለሁ፤ ግን እሱን አሳይተው ህዝቡን ጭሰኛ ለማድረግ መሞከር ጥሩ አይደለም፡፡

እኔና አንድ ቻይና ወይም ህንድ የምንለያየው በምንድነው?

እኔ ደሀ ስለሆንኩ ኮንዶሚኒየም ታዞልኛል፤ እነሱ ግን የፈለጉትን ቦታ ሰርተው ይወስዳሉ፡፡ እኔ እቺ ሀገር ያንተ ናት ከተባልኩኝ ቢያንስ ከቻይና እና ከህንድ እኩል መሆን አለብኝ፡፡

በፓርላማ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ከቀረቡት ጉዳዮች ስለተወሰነ የሚደሰቱበትና የሚቆጡበት?

እኔ ማስተካከያ ሀሳብ ሠጥቼ አንድ ቀንም ተስተካክሎልኝ አያውቅም፡፡ ትክክል የሆነ እና ምንም ቢያደርጉት ዐረፍተነገሩን የማይለውጥ ስም እንኳን እንዲደረግ ሃሳብ ብሰጥ አይቀበሉም፡፡ ለምሳሌ የጡረታ አዋጅ ሲወጣ የመንግስትና የግል ነው የሚለው፤ ለምሳሌ ቤተክርስቲያን፣ የሀይማኖት ተቋም፣ ኤንጂኦ የግል አይደለም፤ የግል የሚለው አይገልፀውም፡፡ ስለዚህ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋሞች የጡረታ አዋጅ ይባል ብዬ አስተያየት ሰጠሁ፤ እቺን እንኳን ለማስተካከል ፈቃደኞች አይደሉም፡፡

አዋጅ እኛ ጋ ከመጣ ማጽደቅ ብቻ ነው፤ ማስተካከል የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ በእርግጥ ተቀብዬ ያፀደቅኳቸው አሉ፡፡ ያረጋል አይሸሹም ይከሰስ ሲባል ይከሰስ ብዬ እጄን አውጥቼ ደግፌያለሁ፡፡ የንግድ ማህበረሰቡ የምዝገባ ጊዜ ይራዘም ሲባል ተቀብዬአለሁ፡፡

አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት በሙስና እየታሰሩ ነው…

አንዳንዶቹን የሚያስረው ሌላውን ለማስፈራራት፣ እንትናም ገብቷልና ተጠንቀቅ ለማለት  ነው፡፡ በሙስና የተጨማለቁም አሉ፡፡ ይሄ ሙስናን ለመዋጋት የሚደረግ ነው መሆን ያለበት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ሲናገሩ በሙስና ተጨማልቀናል ነው ያሉት፤ በመሬት፣ በግብርና የመሳሰሉት… እነዚህ የተጨማለቁት መታሰር አለባቸው፡፡ ሆኖም ቀድሞ የሚታሰሩት ነጋዴዎቹ ናቸው፡፡ እንደዚህ አይነት ነገር ሲመጣ መጠየቅ ያለበት ከአናት ነው፡፡ ለምን ከስር ይርመሰመሳሉ፤ መጠየቅ ከተጀመረ እስከ ላይ ድረስ መጠየቅ አለበት፡፡

የቢዝነስ መዳከምና የኑሮ ውድነትስ… ለምሳሌ የኮንስትራክሽን ስራዎች ዘንድሮ በ25% ገደማ ቀንሷል፡፡ ምንድነው ችግሩ?

የኮንስትራክሽን ስራ የሚሰራው መሬት ላይ ነው አይደል… መሬቱ የመንግስት ከሆነ እንዴት እዛ ላይ ንብረት ማፍራት ይቻላል? እኔ እምመርጠው ወርቅ መግዛት ነው፤ እሱ በየጊዜው ይጨምራል፡፡ መሬት ላይ ቤት ከሠራን ግን እያደር እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ የሚቀንስ ነገር ላይ ማን ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ ህዝቡ አይገዛም አይሸጥም፤ ሲሚንቶ እንዳይባል ዋጋው ከ200 ብር በታች ሆኗል፤ እንደውም ማቴሪያል ቀንሷል፡፡

የእርስዎ ፓርቲና በአጠቃላይ የተቃዋሚዎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይመስልዎታል?

የተቃዋሚ ፓርቲ ስልጣን ይይዛል ብዬ አስባለሁ፡፡ እጣ ፈንታችን ተቃዋሚ ፓርቲ ሲባል አንድ ነው፤ ፓርቲው ደካማ ከሆነ ህዝቡ እየደገፈው አይደለም ማለት ነው፡፡ ተቃዋሚው ጠንካራ ከሆነ ህዝብ እየደገፈው ነው ማለት ነው፡፡ የእኛ ጠንካራና ደካማ ጐናችን የሚታየው ህዝቡ በሚሰጠን ድጋፍ ነው፤ ግን ተቃዋሚዎች ደካሞች ነው ካልሽ… እኔ ምን ሰርቼ ነው ብለሽ መጠየቅ አለብሽ፡፡ ጐበዝ ብለውን የእኛን ጋዜጣ ይዘው መሄድ ከፈሩ ይሄ ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ በውጪ አገር በሽብርተኝነት ተፈርጀው የሚገኙ ግለሰቦች ይቅርታ ከጠየቁ ነፃ ናቸው ብለዋል፡፡  ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

እኔ እቺ ይቅርታ የምትባል ነገር አሪፍ የፖለቲካ መጫወቻ ትመስለኛለች፡፡ አስቤበት ሌላ ጊዜ በደንብ ብናገር ይሻለኛል፡፡ የይቅርታ ስርአቱን እራሱ ፈተና ውስጥ የከተተ ነው የሚመስለኝ፡፡ ምንድነው የሚለውን ነገር አሁን ባልናገር ደስ ይለኛል፡፡ የአንድነት አመራሮች መግለጫ ስትሰጡ በአንድ አይነት አለባበስ ነው፤ እንደ ዩኒፎርም፡፡ አንዳንዶች ከእንግሊዝ ሌበር ፓርቲ የተኮረጀ ነው ይላሉ፡፡ ከእንግሊዝ ሊበራል ፓርቲ ምንም አልወሰድንም፡፡ በአጋጣሚ ጥቁር ሙሉ ልብስ ለብሰን ይሆናል፡፡ በእርግጥ ካቢኔ ሲመረጥ አስበን ተመሳሳይ ልብስ ለብሰናል፡፡ ከእንግሊዝ ሌበር ፓርቲ የተባለው አጋጣሚ ይሆናል እንጂ አስበን ያደረግነው አይደለም፡፡ እኛ መኮረጅ አንፈራም፤ አሪፍ ከሆነ ከኢህአዴግም እንኮርጃለን፡፡ ኩረጃ መጥፎ የሚሆነው ት/ቤት ነው፡፡

በምን ይዝናናሉ?

እኔ ዘፈን አልወድም፡፡ ሆኖም በቅርቡ አንድ ሰው ካሴት መኪናዬ ውስጥ ትቶ ነበር፡፡ እሱን ስሰማ በጣም ወድጄዋለሁ፡፡ የሀይሌ ሩትስ ነው፡፡ ሁሉም እንደሱ ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ መጽሐፍም አነባለሁ፡፡

 

 

 

Read 15098 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 12:20