Saturday, 14 November 2015 08:59

‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(16 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
     እኔን የምለው… አንዳንድ ቦታዎች መከራችንን አይተን የምንገዛት ዳቦ እያነሰች፣ እያነሰች የድሮዋን ‘ደስታ ከረሜላ’ ልታክል ምንም አልቀራት፡፡ ሌላው ደግሞ ችግር ምን መሰላችሁ… ‘ወፍራም’ ዳቦ ትገዙና ቆረስ ስታደርጉት ውስጡ ምን ቢሆን ጥሩ ነው… ቅልጥ ያለ ‘ዋሻ’! የምር እኮ ኮሚክ ነው፡፡ ዳቦ መሀል ያንን የመሰለ ‘ዋሻ’!ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዕንቁላል ስንገዛ አስኳሉን ለመለየት ወደ ብርሀን ከፍ አድርገን እናያለን፡፡ እናማ…
የዳቦው ቡጥ ይኖር አይኖር ለመለየትም በጸሀይ አቅጣጫ ከፍ ማድረግ ሊኖርብን እኮ ነው! ልክ ነዋ…
 ‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’ የሆንን መአት አለን፡ የምር እኮ የሚገርም ነው…በመረጃና በእውቀት ዘመን እንትንን የሚያስንቅ ‘ዋሻ’፡፡‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’ የሆነ ንግግር አለላችሁ፡፡ አለ አይደል…የድርጅቱ ኃላፊ ሲያዩት እንደ አለባበሱና ‘አኮሰታተሩ’ ከአንደበቱ አንዲትም ቁም ነገር ያልሆነች ንግግር የማታመልጠው ይመስላል፡፡ እናላችሁ…“ክቡራንና ክቡራት…” ምናምን ብሎ ሲጀምር… አለ አይደል…‘ቁም ነገሩን
ዘረገፈው’ ብላችሁ ትጠብቃላችሁ፡፡ ከዛላችሁማ…የተለመደችውን… “የዛሬውን ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው…” የምትለውን ‘ኮምፐለስሪ’ ሀረግ ያስከትላል፡፡ እናማ… ስላለፈው ስርአት አስከፊነት፣ ስለ ምናምን ዲጂት ዕድገት፣ ስለ ቁርጠኝነት ምናምን የመሰሉ ሌሎች ‘ኮምፐልሰሪ’ ለመሆን የተጠጉ ነገሮች ለአሥር
ደቂቃ ያወራና ሁሉም በትጋት እንዲሠራ ‘አሳስቦ’ ቁጭ ይላል፡፡ የስብሰባ መሪው ሲያስተዋውቀው እኮ… “…ስለ ድርጅቱ እንቅስቃሴና የወደፊት ዕቅድ ንግግር ያደርጉልናል…” ምናምን ነው ያለው!
እናላችሁ…ዘንድሮ ‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’ የሆኑ ንግግሮችና ስብሰባዎች መአት ናቸው፡፡
የምር እኮ…አንዳንድ ጊዜ “እንዲህ፣ አንዲህ ለማድረግ በቁርጠኝነት ተነስተዋል…”
“…አጠናክሮ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ተነስቷል…”
ምናምን ሲባል…“ጎሽ…” ከማለት ይልቅ “ሂዱና የአዘርባይጃን ቱሪስት ብሉ…” አይነት ነገር የሚመጣልን… አይነት ነገሩ ሁሉ ‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’ እየሆነብን ነዋ!
እኔ የምለው…ምርምሮች ሁሉ ‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’ ሊሆኑብን ነው እንዴ! ግራ ገባና!… ይሄ የሰሞኑ የወተት ነገር ግራ ገብቶናል፡፡ “አይዟችሁ ምንም ጣጣ የለውም…” ምናምን መባሉ አሪፍ ነው፡፡ ግን በመጀመሪያም በ‘ጥናት’ ተደርሶበት ተብሎ ‘የተመረዘ’ ሊሆን የሚችል ነገር
አለው ተባለ፡፡ እንደገና ደግሞ በ‘ጥናት’ ተደረሰበት ተብሎ ምንም አይነት ’የመመረዝ’ ነገር የለውም ተባለ፡፡ ማንን እንመን! ሳይንስ ስንት ‘ጉድ’ የሚባሉ ነገሮች እያሰማን ባለበት ነገር በአንድ ተመሳሳይ ነገር ላይ በተለያዩ አካላት ‘የተጠና ጥናት’ ውጤት እንዴት እንዲህ ጽንፍና ጽንፍ ይሆናል!
እናማ… ሳይንሱም እኛ ዘንድ ሲደርስ ‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’ ነገር ሊሆንብን ነው እንዴ ያሰኛል፡፡
እግረ መንገዴን…ሌላ ደግሞ ‘ብዙ ከብት እየታመመ ነው’ ምናምን የሚባል ነገር አነበብን፡፡ እና ሥጋ ስንገዛም…አለ አይደል… “አንተ ብቻ ጠብቀኝ…” እያልን ልንለማመን ነው ማለት ነው! ጥያቄ…ከብቶቹ ታመዋል አልታመሙም? ነገሮች አልገባን እያሉ እኮ የምንጠይቀው
ሁሉ እያጣን ነው፡፡ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንዶቻችን ነገር የሚገባን ቆይቶ ነው፡፡ ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ቴሌቪዥን
እያየ ሳለ በር ይንኳኳል፡፡ በሩን ሲከፍተውም አንድ ቀንድ አውጣ ያያል፡፡ ይናደድና ቀንድ አውጣውን ብድግ አድርጎ አሽቀንጥሮት በሩን ይዘጋል፡፡
ከሦስት ዓመት በኋላ እንዲሁ ሰውየው ቴሌቪዥን እያየ ሳለ በሩ ይንኳኳል፡፡ ተነስቶ በሩን ሲከፍት ማንን ያገኝ መሰላችሁ…ያንኑ ቀንድ አውጣ፡ ቀንድ አውጣው ሆዬ ተናዶ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ለምንድነው የወረወርከኝ!” (ከሦስት ዓመት በኋላ!)አንዳንዶቻችን…አይደለም በሦስት በአሥራ ሦስት ዓመትም ነገር የሚገባን አይመስልም፡፡ እናማ…የቀንድ አውጣ ‘ኩላሊት’ ከእኛ ፈጥኖ
‘ማሰብ’ ሲጀምር…አለ አይደል…“ኧረ ምን ጉድ ነው!” ያስብላል፡፡ (እግረ መንገዴን…‘አንዳንዶች’ የሚለው ለግለሰብም፣ ለተቋምም እንደሚሆን ልብ ይባልልንማ፡፡ መልእክቱ ተላልፏል!)
እናማ… ብዙ ነገር ‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’ ነገር እየሆነብን ነው፡፡ ስሙኝማ…ውበት ላይ እንኳን  ፈረንጅ ‘ኋት ዩ ሲ ኢዝ ኋት ዩ ጌት’ የሚላት ነገር መሥራት ካቆመች ከረመች፡፡ እነ ማስካራ፣ እነ ፋውንዴሽን፣ እነ ሄር ዳይ ምናምን የሚሏቸው ነገሮች እያሉ ‘ቡጡ’ን የት እንየው!
እንደ ድሮው… “ብታያት እኮ ደሟ በጉንጫቿ ስር ሲሯርጥ! በማርና በቅቤ ሲወለውሏት ውለው የሚያድሩ ነው የሚመስለው!” ብሎ ነገር
አይሠራም፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘፈን ለመዝፈንም፣ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ… አለ አይደል…የሆነ ኤፍ.ኤም.
ሬድዮ ጣቢያ እንደውላለን፡፡
“ሀሎ አድማጫችን ማን እንበል…”
“ጆኒ ከሚሊተሪ ተራ…”
“እሺ ጆኒ…ሙዚቃ ለመምረጥ ፈልገህ ነው?”
“አዎ…”
“ምን የሚሉት ሙዚቃ ይደረግልህ?”
“የሙሉቀን መለሰን የጎፈሬሽ ዳር ዳሩ…የሚለውን ዘፈን ለጓደኛዬ ልመርጥላት ፈልጌ ነው፡፡”
“ጓደኛህ ጎፈሬዋ እንዴት ነው…”
“ጸጉሯ ብታዩት ወገቧን አልፎ እግሯ ሊደርስ ምንም አይቀረው…”
ይሄኔ ኤፍ.ኤሞች… አለ አይደል… ምን ጥያቄ መጠየቅ አለባቸው መሰላችሁ…
“የእሷ ፀጉር እውነተኛ መሆኑን በምን አረጋገጥክ?”
ልክ ነዋ… አገሩ ሁሉ ‘ዞማ’ በሆነበት ጊዜ፣ መጠየቅ አስፈላጊ ነዋ!
ደግሞላችሁ…አለ አይደል….ግጥሙን ለመለወጥ እንኳን አይመችም፡፡
የጎፈሬሽ ዳር ዳሩ፣ የጎፈሬሽ ዳር ዳሩ
አቤት ዊግሽ ማማሩ
አይባል ነገር፡፡ የዊጉ ማማር የእሷ ጉዳይ ሳይሆን የሠራው ፋብሪካ ጉዳይ ነዋ፡፡ ደግሞላችሁ…
እቴ አውዪኝ ልዋል፣ እቴ አውዪኝ ልዋል
በጎፈሬሽ መሀል
…እንዳይባልም አስቸጋሪ ነው፡፡
እቴ አውዪኝ ልዋል፣ እቴ አውዪኝ ልዋል
በዛ ዊግሽ መሀል…
ብሎ ቀድሞ የሚዘፍን ዘፋኝ…ምን አለ በሉኝ…የዊግ ፋብሪካዎች ስፖንስር ያደርጉታል፡፡ እናላችሁ በ‘ደም ግባት’ና ፀጉር እንኳን ነገሩ

ሁሉ ‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’  እየሆነብን መለየት እየቸገረን ነው፡፡ስሙኝማ…በፊት እኮ እንትናዬ እንትናዋን የምትጠይቀው… አለ አይደል…

“ለጸጉር ማሠሪያ ሀምሳ፣ ስድሳ ብር ስጠኝ…” ምናምን ብላ ነበር፡፡ እናማ…አሁን “ስማ ለዊግ መግዣ ብር ስላነሰኝ አንድ ሦስት ሺህ ብር ጨምርልኝ…” ምናምን ሊባል ነው ማለት ነው! እናማ…ልጄ ዘንድሮ ውበት የዘዴ ጉዳይ ሆኗል፡ ልክ ነዋ…ዕድሜ ለዊግና ለፋውንዴሽን!
‘ቆንጆ ፍለጋ’ እግር እስኪነቃ መሄድ ድሮ ቀርቷል፡፡ እናማ… ብልጦቹ እንዴት ቆንጆ እንደሚኮን ገብቷቸዋል፡፡ (ምንም እንኳን ነገርዬው
ሁሉ ‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’  ቢሆንም ማለት ነው፡፡)የብልጥነት ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ብልጥ ነኝ ባይ ነው፡፡ እናማ፣ ይቺን ዓለም ሲሰናበት… አለ አይደል… 99.9% የምንሆነው ‘ዌይቲንግ ሊስት’ ውስጥ ወደተካተትንበት ገሀነም ይሄዳል፡፡ ሳጥናኤል በሩ ላይ ያገኘውና ሦስት በሮች ያሳየዋል፡፡ በመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ሰዎቹ ሁሉ እስከ አንገታቸው ድረስ ቆሻሻ ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡
ሰውየው…  “የሌላኛውን ክፍል አሳየኝ…” ይላል፡፡  ሁለተኛው ክፍል ውስጥ ያሉት ሰዎች እስከ አፍንጫቸው ድረስ ቆሻሻ ውስጥ ተከተዋል፡፡ ሰውየው… “ይህን አልፈልግም፣ ሦስተኛውን አሳየኝ…” ይላል፡፡ ሳጥናኤልም ወደ ሦስተኛው ክፍል ይወስደዋል፡፡ ሦስተኛው
ክፍል ውስጥ ሰዎቹ እስከ ጉልበታቸው ድረስ ቆሻሻ ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ ግን ቡና እየጠጡ ኬክ እየበሉ እያውካኩ ነበር፡፡ ሰውየውም…
“እዚህ ነው የምገባው…” አለ፡፡ ሳጥናኤልም… “እሺ፣ ግባ…” ይለዋል፡፡ ሰውየው ልክ እንደገባ ሳጥናኤልም በሩን እየዘጋ ምን ቢል ጥሩ ነው… “የአሥር ደቂቃ የሻይ እረፍት ስላበቃ ሁልሽም በጭንቅላትሽ ቆሻሻ ውስጥ ግቢ!” ብሎ አዘዘ፡፡ብልጥ ሲሆኑ መበለጥ እንዲህ ነው፡፡እናማ…ገና ቡና እየተጠጣ ኬክ ሲበላ ስለታየ፣ ሁሉም ነገር አሪፍ ነው ማለት አይደለም፡፡ ነገርዬው ‘የሌለ የዳቦ ቡጥ’ ሊሆን ይችላል፡፡  ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6050 times