Saturday, 07 November 2015 10:30

ክብርቷ ወይዘሮ

Written by  ደራሲ፡- ኬት ሾፒን ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(15 votes)

መጪዎቹ ሁለት ወራት የሰርግ ወራት ስለሆኑ በፍቅር እና በትዳር ዙሪያ በታላላቅ ደራሲዎች የተፃፉ ምርጥ ምርጥ አጫጭር ልብ-ወለዶች እንደ አመቺነቱ እናቀርብላችኋለን፡፡ ሶስቱ ደራሲያን ሴቶች ናቸው፡-ኬይ ቦይል፣ ኬት ሾፒን እና ዶሪስሌሲንግ፡፡ ሁለቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው፡- ኧርነስት ሄምንጊዌይና ጆን ስታንቤክ፡፡ ከነዚህም መሃል ሁለቱ ወንዶችና ሴቷ ዶሪስሌሲንግ የስነ ፅሁፍ ኖቤል ተሸላሚዎች ናቸው፡፡ አጫጭር ልብ-ወለዶቹ አዝናኝ፣ አስደንጋጭ(shocking)፣ አሳዛኝ፣ አከራካሪ፣አመራማሪ …ናቸው፡፡ እንዲህ ባንድ ጉዳይ ላይ (ለምሳሌ እንደ አሁኑ ፍቅር እና ትዳር) የተፃፉ ስራዎችን አሰባስቦማስነበቡ የተለመደ ባለመሆኑ ታሪኮቹን እንደምትወዱዋቸው እናምናለን፡፡

   ወይዘሮ ባሮዳ ባሏ የነገራት ነገር አበሳጭቷታል። ባሏ፣ ጋውቨርኔል የተባለ ጓደኛውን አንድ ወይም ሁለት ሳምንታት እነሱ ጋር እንዲያሳልፍ ጋብዞታል፡፡
ክረምቱን እጅጉን ነበር ሲዝናኑ ያሳለፉት፡፡ ወደ ኒው አርሊየንስ ሄደው አቅማቸው፣ ጊዜያቸው፣ ገንዘባቸው እስኪሟጠጥ ነበር የተዝናኑት፡፡ ምን የተዝናኑት? የቀበጡት እንጂ፡፡ ከዚያ ሲመለሱ ማንንም ሳታገኝ ከባሏ ጋር ብቻ ሆና ረዥም እረፍት ለማሳለፍ ነበር የወሰነችው፡፡ ይሄኔ ነው እንግዲህ ባለቤቷ ጓደኛው እነሱ ጋ ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንት እረፍት እንደሚመጣ የነገራት፡፡ ትንሽ ያበሳጫል፡፡
ይመጣል ስለተባለው ሰውዬ ብዙ ሰምታለች፤ አይታው አታውቅም እንጂ፡፡ ከባሏ ጋር ኮሌጅ አብረው ነው የተማሩት፡፡ አሁን ጋዜጠኛ ሆኗል። ከሰው ጋር መቀላቀል የሚወድ አይነት ሰው አይደለም፡፡  ‘መዝናናት’ ይሉት ነገር የሚያዝናናው አይነትም አይደለም፡፡ ለዚህም ይሆናል አግኝታው የማታውቀው፡፡
የሚገርመው ነገር ሳታስበው፣ ሳይታወቃት፣ ምስሉን በአዕምሮዋ ቀርፃለች፡፡ አእምሮዋ እንዲህ አይነት ሰው ነው የቀረፀው፡- ረዥም፣ ቀጫጫ፣ አሽሟጣጭ ሆኖ መነፅር የሚያደርግ እና ደግሞ እጆቹን ኪሶቹ ውስጥ መሸጎር የሚወድ፡፡ ሳታየው ጠላችው፡፡ ጋውቨርኔልን ስታገኘው አንዱ ግምቷ ብቻ ነው ልክ ሆኖ የተገኘው፡፡ ቀጭን ነው፤ በተረፈ ረዥምም፣ አሸሟጣጭም አይደለም፡፡ መነፅር አያደርግም፡፡ እጆቹንም ኪሶቹ ውስጥ አይሸጉርም፡፡ እንደተዋወቀችው ወደደችው፡፡ ለምን እንደወደደችው ብታብሰለስል፣ ብታብሰለስል አንድም የሚያረካ መልስ አላገኘችም፡፡ ባሏ ጋስቶን ጓደኛው ብሩህ አእምሮ እንዳለው ነግሯታል፡፡ ተስፋ የሚጣልበትና የሚያስመካ ሰውም እንደሆነ ደጋግሞ አውርቶላታል፡፡ ባሏ ከነገራት አንዱንም ባህሪ ሰውየው ላይ አላገኘችም፡፡ እንዲያውም ተለጉሞ ቁጭ ብሎ፣ ያሉትን ሁሉ የሚሰማ ነው። ለእሷ የሚያሳየው ክብር ወግ አጥባቂዎቹ ሴቶች የሚጠብቁትን አይነት ነው፡፡ በምላሹ ግን ከእሷ ይሁንታንና ከበሬታን አይፈልግም፡፡
እርሻቸው ተመችቶታል፡፡ በረንዳቸው ጋ ካሉት ቋሚዎች አንዱ ጥላ ስር ቁጭ ብሎ በግድ የለሽነት ሲጋራውን እያጨሰ፣ የባሏን ወሬ በሙሉ ትኩረት ያዳምጣል፡፡ ባሏ ስለ ሸንኮራ እርሻቸው ያወራለታል።
“ኑሮ ይላሉ ይኼ ነው፡፡” ይላል የባሏ ጓደኛ ከሸንኮራው ማሳ የሚመጣው ሞቅ ያለ፣ የሚጣፍጥ መዐዛ ያለው ነፋስ ሲዳብሰው፡፡ ትልልቆቹ ውሾችም ተመችተውታል፤ እነሱም ይኼ ገብቷቸው በፍቅር ይተሻሹታል፡፡  ባሏ ጋስቶን ሊያዝናናው አስቦ አሳ እናጥምድ ቢለው፣ ወፎች እናድን ቢለው ኬረዳሽ አለ፡፡
የጋውቨርኔል ባህሪ ወይዘሮ ባሮዳን አወዛግቧታል። እንዲያም ሆኖ ግን ወዳዋለች፡፡ እርግጥም ሰውየው ተወዳጅና አንዳችም ክፋት የሌለው ነው፡፡ ብትል፣ ብትል ሰውየው አልገባ ሲላት መወዛገቧን ተወችው። እጅግ ቅር ብሏታል ግን፡፡ በተቻለ መጠን ባሏና ሰውየው ያሉበት መድረስ ተወች፡፡ ጋውቨርኔል ሆን ብላ እንደራቀችው አልገባውም፡፡ ኧረ እሱ መራቋ እራሱ አልታወቀውም፡፡ ይህን ስታውቅ ተመልሳ ትቀርበው ጀመር፡፡ ወደ ሸንኮራ ወፍጮአቸው ሲሄድ አብራው ትሄዳለች፡፡ ወደ ወንዙ ሲሄድም ከጎኑ አለች፡፡ እራሱን ከአጠረበት የዝምታ ምሽግ ልታወጣው ደጋግማ ሞከረች፡፡ አልቻለችም፡፡
“መቼ ነው የሚሄደው ይኼ ጓደኛህ?!” ብላ ባሏን ጠየቀችው፡- “እኔ በበኩሌ ስልችት ብሎኛል፡፡”
“ከሳምንት በፊት አይሄድም የኔ ውድ፡፡ ለምን እንደጠየቅሽኝ አልገባኝም፡፡ የሚያስቸግር አይነት ሰው አይደለም፡፡ አላስቸገረምም ደግሞ፡፡”  
“አይ አላስቸገረኝም፡፡ አስቸጋሪ ቢሆን ይሻለኝ ነበር፡፡ እወደው ነበር፡፡ እንደ ሌሎች ሰዎች የሚፈልገውን በግልጽ የሚናገር ቢሆን ኖሮ፣ ምን እንደሚመቸው፣ ምን እንደሚያስደስተው አውቄ አዘጋጅለት ነበር፡፡”
ጋስቶን የባለቤቱን የምታምር ፊት በሁለት መዳፎቹ ይዞ፣ እየሳቀ የተረበሹ አይኖቿን አየ፡፡
“አያልቅብሽ ብዬሻለሁ፣ የኔ ቆንጆ፤ አያልቅብሽ ነገር ነሽ፡፡ ሁሌ እንደገረምሽኝ ነው፡፡”  አለ፡- “ እኔ እንኳ በምን ሁኔታ ምን እንደምታደርጊ መገመት አልችልም፡፡”  
ስሟት ከረቫቱን ለማስተካከል ወደ መልበሻው መስታወት ዞረ፡- “ይታይሽ እንግዲህ…” ቀጠለ ባሏ፡- “ምስኪኑ ጋውቨርኔል ይመቸው-አይመቸው፣ ደስተኛ ይሁን-አይሁን አላወቅሁም ብለሽ ትጨናነቂያለሽ፡፡ ቀወጢ ትፈጥሪያለሽ፡፡ እሱ ከዚህ በላይ ምንም አይፈልግም፡፡”
“ቀውጢ ትፈጥሪያለሽ ነው ያልከው!” ቀወጠችው፡፡ “ቀሽም! እንዴት እንዲያ ትላለህ? ታውቃለህ ግን ብልህ ነው ብለኸኝ ነበር፡፡”
“እና ታዲያ፤ ነውና! ግና ምስኪኑ ጓደኛዬ በስራ ብዛት ደንዝዟል፡፡ ለዚያም ነው እኛ ጋ መጥቶ እረፍት እንዲወስድ ያደረግሁት፡፡”
“ሀሳብ እሱ ጋ በሽ ነው ትል ነበር፡፡” አለች ጮሃ፤ ጥላቻዋን እንደታቀፈች፣ በአልረታ ባይነት፡- “አንዳችም ደስ የሚል፣ የሚማርክ ነገር አልሰማሁም። አላየሁበትም፡፡ ለፀደይ ወራት የገዛሁትን የመኝታ ልብስ ላሰፋ ነገ ወደ ከተማ እሄዳለሁ፡፡ ጓደኛህ አቶ ጋውቨርኔል ሲሄድ ላክብኝ፤ እስከዚያው ድረስ አክስቴ ኦክታቪያ ጋር እቆያለሁ፡፡”
የዚያን ቀን ምሽት የጠጠር መንገዱ ላይ ያለ ትልቅ ዛፍ ስር ያለ መቀመጫ ላይ ብቻዋን ሄዳ ቁጭ አለች፡፡
እንዲህ ተወዛግባ አታውቅም፡፡ ሀሳቦቿ እንዲህ ተዘባርቀው አያውቁም፡፡
ጠጠሮቹን ቀርጨጨጭ፣ ቀርጨጨጭ እያደረገ የሚመጣ የእግር ኮቴ ሰማች፡፡ ጨለማ ነው፤ ባለኮቴውን መለየት አልቻለችም፡፡ ትንሽ ቆይቶ እሳት ታያት፣ የሲጋራ ጫፍ ላይ እሳት፡፡ ባሏ አያጨስም፤ ጋውቨርኔል እንደሆነ አወቀች፡፡ ምነው ባላየኝ ብላ ብትመኝም የለበሰችው ነጭ የምሽት ልብስ እየመራ ወደ እሷ አመጣው፡፡ ሲጋራውን ወርውሮ አጠገቧ ቁጭ አለ፡፡ እንኳን አጠገቧ እንዲቀመጥ፤ ወዳለችበት እንዲመጣ እንዳልፈለገች አላወቀም፡፡
“ወይዘሮ ባሮዳ፤ ይህን ባለቤትሽ አድርስላት ብሎ ልኮኝ ነው፡፡” አለ አልፎ፣ አልፎ እራሷና ትከሻዋ ላይ ጣል የምታደርገውን ነጭ ስካርቭ እያቀበላት፡፡ ተቀብላ፣ አመሰግናለሁ የሚል ቃል አጉረመረመች። ስካርቩን አልለበሰችውም፤ ታፋዋ ላይ አኖረችው፡፡
ጋውቨርኔል  በዚህ ወቅት ያለው የምሽት ነፋስ ለጤና ጥሩ እንዳይደለ ተናገረ፡፡ ይህን ማንም ተራ ሰው ያውቀዋል፡፡ በኋላ ጨለማው ላይ አተኩሮ፣ በአብዛኛው ለራሱ በሚመስል ጉርምርምታ ይህን አለ፡-
“አንተ ምሽት ሆይ
የደቡቡ ነፋስ የወለደህ
በግዙፍ ግን ጥቂት ክዋክብት የደመቅህ
ሰላምተኛው ምሽት ሆይ …”
(ስንኞቹ የተወሰዱት ከ Walt Whitman Song of Myself የሚል ግጥም ላይ ነው- ተርጓሚው)
ለተቀነጨበው ግጥም ምንም መልስ አልሰጠችም፡፡ እሷን አይደለማ ያዋራት፡፡
ጋውቨርኔል ጨርሶ እራሱን ተጠራጥሮ አያውቅም፤ መቼ ስለ እራሱ አስቦ ያውቅና ነው ደግሞ እራሱን የሚጠራጠረው፡፡ ዝም የሚለው እንኳ ይሁነኝ ብሎ፤ አቅዶ፣ ዝምታ መልካም ነው ብሎ፣ መመሪያ፣ ህጉ ሆኖ አይደለም፡፡ እንደ ስሜቱ ነው፡፡ በቃ ዝም ሲል ዝም ነው፤ ማውራት ሲፈልግ ያወራል፡፡ አሁን ወይዘሮ ባሮዳ አጠገብ ተቀምጦ እራሱን ሲያገኘው ዝምታው በኖ ጠፋ፡፡
ነፃ ሆኖ አወራት፡፡ ልክ እንደ ቅርቡ ሰው አወራት፡፡ የሚያወራው ዝግ ባለ፣ በሚያመነታና በሚጎተት ድምፅ ነው፡፡ ሲሰሙት ግን ድምጹ ለጆሮ አይደብርም፡፡ ከጋስቶን ጋር ስለነበራቸው የኮሌጅ ጊዜና አንዱ የሌላው ህይወት እንዲሰምር እንዴት ይረዳዱ እንደነበር አወራት፡፡ በወጣትነታቸው በየዋህነት ይመኟቸው የነበሩትን የማይጨበጡ ምኞቶች፣ ያልሟቸው የነበሩትን የማይደረስባቸው ታላላቅ ግቦችን፣ አወራት፡፡ “…አሁን የቀረ ነገር የለም፡፡ አሁን በሀሳብ ደረጃ ያለውን ነገር ተቀብዬ መኖር ነው የምሻው፤ መኖር እንዲፈቀድልኝ ብቻ ነው የምፈልገው፡፡ አልፎ አልፎ የእውነተኛ ህይወት ጠረን አወድ ቢያረገኝ አልጠላም፣ ልክ እንዲህ እንደአሁኑ…” አላት፡፡
ከሚናገረው ነገር አእምሮዋ ጋ የሚደርሰው የከፊል ከፊሉ ነው፡፡ ስጋዋ ከአእምሮዋ ገዝፏል። ሁለንተናዋ ስሜት ብቻ ሆኗል፡፡ የሚናገራቸውን ቃላት ትርጉም አይደለም ትሰማ የነበረው፤ የድምጹን ቃና ነበር እያጣጣመች የነበረው፡፡ በጨለማው ውስጥ እጆቿን ዘርግታ በስስ ጣቶቿ፣ ስሜት የበለጠ ባሳሳችው ጣቶቿ ልትነካው ፈለገች፤ ፊቱን ወይ ከንፈሮቹን፡፡
እጅጉን ተጠግታው ጉንጮቹ ላይ በስሱ ማንሾካሾክ ከጀለች፡፡ እነኚህንም ሌላም ነገር ብታደርግ ወደደች፡፡ ምን ያደርጋል ግን?! የተከበረች ወይዘሮ ናት!!
ስሜቷ እንድትጠጋው በገፋፋት ቁጥር በትንሹ ጠጋ ትላለች፡፡ ጠጋ የምትለው ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ነው፡፡ በትንሽ፣ በትንሹ ጠጋ፣ ጠጋ እያለች ሳይነቃባት እራቀችው፡፡ በቂ ከሸሸችው በኋላ ለመሄድ ተነሳች፡፡ ብቻውን ጥላው ሄደች፡፡
እሷ ወደ ቤቷ እየሄደች፣ ጋውቨርኔል ሲጋራ ለኩሶ የመጀመረውን የግጥም ቁራጭ ጨረሰው፡፡
ወይዘሮ ባሮዳ የዚያ ቀን ምሽት ለባለቤቷ፣ ባለቤቷ ጓደኛዋም ጭምር ነውና፣ የሰፈረባትን የሚያጃጅል መንፈስ ለመንገር ዳድቷት ነበር። አውሪ፣ አውሪ ብሎ የገፋፋትን ስሜት እንደ ምንም ብላ ተቋቋመችው። የተከበረች ወይዘሮ ብቻ አይደለችም፣ አዋቂም ጭምር ናት፡፡ በህይወት ውስጥ ለብቻ የሚጋፈጡት ጦርነት እንዳለም አስታወሰች፡፡
ጋስቶን ጠዋት ከእንቅልፍ ሲነሳ ባለቤቱን አላገኛትም ፤ ሄዳለች፡፡ በመጀመሪያው ባቡር ነው የሄደችው፡፡ እንዳለችውም ጋውቨርኔል ካልሄደ እንደማትመለስ ታወቀው፡፡
ጋስቶን ጓደኛው የሚቀጥለውን ክረምት እነሱ ጋ ቢያሳልፍ ደስ እንደሚለው ለሚስቱ ነገራት፤ አምርራ ተቃወመች፡፡ የሚስቱን ፍላጎት አክብሮ ተቀበለ፡፡
ክረምቱ እየተቃረበ ሲመጣ ግን ወይዘሮዋ፣ ጋውቨርኔል መጥቶ ቢጎበኛቸው ፍቃደኛ እንደሆነች ለባሏ ነገረችው፡፡
ባልዬው ደንቆታል፡፡ ነገርየው ከእሷ በመምጣቱ እጅግ ደስ ብሎታል፡፡
“የኔ ክብርት፤ ጥላቻው ለቀቀሽ አይደል? በጣም ደስ ይላል፡፡ ጋውቨርኔል እኮ የሚጠሉት አይነት ሰው አይደለም፡፡”
“ዝም ብዬ ነው ባክህ፡፡” አለች እየሳቀች፣ ከንፈሮቹን በስሱ፣ ዘለግ ላለ ጊዜ ሳመቻቸው፡- “ሁሉ ነገር ለቆኛል፡፡
ታየኛለህ ደግሞ በአሁኑ ሲመጣ እጅግ መልካም ነው የምሆንለት፡፡”
(የእንግሊዝኛው ርእስ፡ -A Respectable Woman)
ስለ ደራሲዋ፡-
ኬት ሾቲን እ.ኤ.አ. በ 1850 ዓ.ም. ተወልዳ በ1904 ዓ.ም. የሞተች አሜሪካዊት የአጫጭርና የረዣዥም ልበ-ወለዶች ደራሲ ናት፡፡
በደራሲነቷ ብቻ ሳይሆን በሴቶች መብት ተቆርቋሪነቷም ትታወቃለች፡፡
አንዳንዶች እንዲያውም የሴቶች መብት ተቆርቋሪነቷን  በብዕሯ አደባባይ ይዛ በመውጣት ቀዳሚዋ ናት ይሏታል፡፡



Read 4299 times