Saturday, 07 November 2015 10:08

የሊቢያ መንግስት እውቅና ካልተሰጠኝ አውሮፓን በስደተኞች አጥለቀልቃለሁ አለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በዚህ ወር ብቻ ከ218 ሺህ በላይ ስደተኞች ባህር አቋርጠው አውሮፓ ገብተዋል

   ራሱን በህጋዊ መንግስትነት የሰየመው ናሽናል ሳሊቬሽን ገቨርንመንት ኦፍ ሊቢያስ ጄኔራል ናሽናል ኮንግረስ ቃል አቀባይ ጀማል ዙቢያ የአውሮፓ ህብረት በመንግስትነት እውቅና የማይሰጠው ከሆነ፣ ኮንግረሱ የአውሮፓ አገራትን በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ተጨማሪ ስደተኞች እንደሚያጥለቀልቅ ማስጠንቀቃቸውን ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ቃል አቀባዩ ለዘ ቴሌግራፍ እንዳሉት፣ ባለፈው አመት የአገሪቱን መዲና የተቆጣጠረው ኮንግረሱ ከህብረቱ የመንግስትነት እውቅና ከተነፈገው፣ በራሱ ወጪ ጀልባዎችን ተከራይቶ አፍሪካውያን ስደተኞችን በሜዲትራኒያን ባህር በኩል በማጓጓዝ አውሮፓን የባሰ በስደተኞች ከማጥለቅለቅ አይመለስም፡፡
ሊቢያ በግዛቷ በኩል አድርገው ወደ አውሮፓ የሚሄዱ የተለያዩ አገራት ስደተኞችን ለማስቀረት በየአመቱ በአስር ሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ ታደርጋለች ያሉት ቃል አቀባዩ፣ የአውሮፓ ህብረት በመንግስትነት እውቅና የማይሰጠን ከሆነ ስደተኞችን እየጫንን አውሮፓን እናጥለቀልቃታለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
ኮንግረሱ አለማቀፍ እውቅና የተሰጠውን የሊቢያ ተወካዮች ምክር ቤት ታማኝ ሃይሎች በጦርነት አሸንፎ መዲናዋን ቢቆጣጠርም፣ የአውሮፓ ህብረት ግን ለኮንግረሱ የመንግስትነት እውቅና ሳይሰጥ መቆየቱን ዘገባው አስረድቷል፡፡
ተመድ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ በዚህ ወር ብቻ ከ218 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ገብተዋል ማለቱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2137 times