Saturday, 07 November 2015 10:05

የሩማንያው ጠ/ሚኒስትር በፈቃዳቸው ስልጣን ለቀቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

- ባለፈው ወር በሙስና ተከስሰው፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ነው
- የመዲናዋ ከንቲባና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩም ስልጣን ለቀዋል

   በሩማኒያ መዲና ቡቻሬስት ውስጥ በሚገኝ አንድ የምሽት ክለብ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ32 በላይ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸው የቀሰቀሰው ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ጠ/ ሚኒስትር ቪክቶር ፖንታ በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣን እንደለቀቁ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ከ20 ሺህ በላይ ሩማንያውያን ባሳለፍነው ማክሰኞ በከተማዋ ጎዳናዎች እየተዘዋወሩ መንግስት ሙሰኛ ነው፤ የደህንነት ክትትል አሰራሩም ደካማ ነው በማለት ተቃውሟቸውን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን እንዲለቁ መጠየቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ፖንታም በነጋታው ስልጣን መልቀቃቸውን በይፋ እንዳስታወቁ ጠቁሟል፡፡
ለ3 አመት ከመንፈቅ በስልጣን ላይ የቆዩት ጠ/ ሚኒስትር ቪክቶር ፖንታ ባለፈው መስከረም ወር ላይ በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው፣ ጉዳያቸው በአገሪቱ ፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ዘገባው ጠቁሞ፣ በስልጣን ላይ እያሉ በታክስ ማጭበርበር፣ በሙስና እና ከህገወጥ ገንዘብ ጋር በተያያዘ በክስ የተመሰረተባቸው የመጀመሪያው የአገሪቱ ጠ/ ሚኒስትር እንደሆኑም ገልጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡባቸውን ክሶች በሙሉ ክደው መከራከራቸውንና ክስ የመሰረቱባቸውን አቃቤ ህጎች ፍጹም ሙያዊነት የጎደላቸው ሲሉ መተቸታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው ረቡዕ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባስተላለፉት መልእክት ከስልጣን መልቀቃቸው ጎዳና ላይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ያሰሙትን ዜጎች ያስደስታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መናገራቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ አገሪቱን ከብጥብጥ ለማዳንና ተተኪ መንግስት ማቋቋም የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ ስብሰባ ማድረጉ ተነግሯል፡፡

Read 1090 times