Saturday, 07 November 2015 09:48

‘በቆሙበት ማንጋጠጥ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(14 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንደምን ከረምክልኝ?
 (አንድዬ ደንገጥ ይላል) ምን አልከኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደምን ከረምክልኝ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡— ይቺን ይወዳል  (አንድዬ በመገረም እጆቹን ያጨበጭባል) ጭራሸ አንተው እኔን እንዴት ከረምክ ትለኝ ጀመር?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ልማድ ሆኖብኝ እኮ ነው። ደግሞ እንዲያውም እንዲህ በማለቴ ልታመሰግነኝ ይገባል፡፡
አንድዬ፡— እንዴት ከረምክ ስላልከኝ ነው የማመሰግንህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ታዲያስ አንድዬ! እንደ ዘንድሮ ቢሆን እኮ ገና ከመጀመሪያው ምን አዲስ ነገር አለ ነበር የምልህ!
አንድዬ፡— እንደ እሱ ብትለኝ ይሻለኝ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አዲስ ነገር አለ እንዴ?
አንድዬ፡— ሊኖር ይችላል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አንተው አይደለህም እንዴ ከምድር በታች ምንም አዲስ  ነገር የለም ያልከው…
አንድዬ፡— እኔው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንተ ካልሆንክ ታዲያ…
አንድዬ፡— እንደው አረቄውን ስትግቱ፣ ሱረቱን ስትምጉ የቀባጠራችሁትን ሁሉ በእኔ ስም አደረጋችሁት
ምስኪን ሀበሻ፡— መስሎኝ ነው አንድዬ፡፡ ግን አዲስ ነገር ያልከው፣ እኛን የሚመለከት ነው እንዴ?
አንድዬ፡— አዎ እናንተን ይመለከታል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ንገረኛ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— ምስጢር ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አንተም ምስጢር ትላለሀ እንዴ!
አንድዬ፡— አዎ…ግን እንደው ደግሞ በዚህ ምክንያት ቆሽትህ ተሰንጥቆ በእኔ እንዳታሳብብ ልንገርህ፡፡ እናንተን በተመለከተ ላልተወሰነ ጊዜ ፈጣሪነቴን ላነሳ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— (ምስኪን ሀበሻ አመዱ ቡን አለ) አንድዬ፣ መቼም ምን እንደሚሆን ለየው ብለህ ነው እንጂ የምርህን አይደለም፡
አንድዬ፡— እንደ ዘንድሮም የምሬን ተናግሬ አላውቅም፡፡ ጭራሸ እናንተ በራሳችሁ ላይ ያመጣችሁትን ችግር አንዳንዶች ‘ምነው እነሱ ላይ እንዲህ ጨከነባቸው’ ሲሉ ስለሰማሁ እኔ አለመሆኔን እንዲያውቁ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይሄንንማ እኛ አንቀበልም…
አንድዬ፡— ሰላማዊ ሰልፍ የምትሉትን ውጡብኛ። ‘ይሄንንማ እኛ አንቀበልም’ አልከኝና አረፍከው! እኔ እኮ እንደምን ከረምክ ስትለኝ ያወቅሁት፡ እንደው ትንሽ ገንዘብ ቢጤ፣ ትንሽ ስልጣን ቢጤ አግኝታችሁ ረጅም ወንበር ላይም፣ ረጅም ፎቅ ላይም ስትሰቀሉ እኔ ቤት የደረሳችሁ መሰላችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ መቼም ከሰው ስህተት አይጠፋም…
አንድዬ፡— ሲቸግራችሁ ቤተ መቅደሴ መጥታችሁ ተደፍታችሁ ታለቅሱብኛላችሁ፡፡ ትንሽ ቀና ስትሉ ደግሞ ጭራሹን የስለት ገንዘብ በተላላኪ ትልኩኛላችሁ፡፡ ጭራሽ ‘እንዴት ከረምክ’ ብለኸኝ አረፍከው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን አለበት እንደ ዘመኑ ምን አዲስ ነገር አለ ከምልህ እንዴት ከረምክልኝ አይሻልም!
አንድዬ፡— ደህና ከርሜያለሁ..እንደሁ ልበል እንጂ…እኔ የምለው እኮ አንዳንዴ ጃፓኖቹ፣ ኮሪያዎቹ ጭንቅላት ውስጥ የከተትኩትን ነገር እነሱ ላይ ሳልከት ረስቼው ይሆን እንዴ እላለሁ፡፡ አንድዬ ባዶ ጭንቅላት ናችሁ እያልከን ነው?
አንድዬ፡— እሱማ በማን ዕድላችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— እንዴት አንድዬ ባዶ ጭንቅላት መሆናችን እንደ ዕድል አየኸው!
አንድዬ፡— ቢያንስ ባዶ ጭንቅላት የሆነ ነገር ለመቀበል ቦታ አለው፡፡ የእናንተ ጭንቅላት እኮ ተጨናንቆ በሩ አልከፈት ያለ መጋዘን ሆኗል፡፡ (አንድዬ ከት ብሎ ይስቃል)  ግዴለህም፣ ትንሽ ቆይቶ እንደ እናንተ በማለዳ ኮረፌዬን ሳልጠጣ አልቀርም፡፡ እኔ እኮ አንድ ሰሞን ገና ጎህ ሲቀድ በየመሸታ ቤቱ በረንዳ ላይ ተሰብስባችሁ ብቅልና ገብሳችሁን ስትገለብጡ እነኚህ ሰዎች አዲስ አይነት ወተት ፈጠሩ እንዴ ብዬ ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ታዲያ በምን እናስምጠው?
አንድዬ፡— ምኑን ነው የምታሰምጡት?
ምስኪን ሀበሻ፡— ሀሳባችንን ነዋ!  እንደዛ በማለዳ ስንጠጣ ደልቶን መሰለህ…አንድዬ፣ የችግራችን ብዛትማ በቃ የቻይና ህዝብ ቁጥር በለው…
አንድዬ፡— በህዝብ ቁጥር እንኳን እናንተም አትታሙም፡፡ ራሳችንን መቀለብ አቃተን እያላችሁ ልጆቹን በረሀብ ልትፈጁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አንተ እያለህ እንዴት በረሀብ ይፈጃሉ! አንድዬ፣ አሁንም ዓለምን እርዱን ራበን ስንል ዝም ብለህ ታየናለህ!
አንድዬ፡— እና ምን ላድርጋችሁ! እኔ ወርጄ መሬቱን ልረስልህ! እኔ ወርጄ ከብቱን ላርባልህ! እኔ ወርጄ ድንጋዩን ልፍለጥልህ! አንዲት ጠጠር እንኳን ሳትፈነቅሉ እጃችሁን አጣምራችሁ እኔን ትጨቀጭቁኛላችሁ። ለራሳችሁ አትሥሩና ያው እንደለመዳችሁት የካናዳን የስንዴ ምርት እንዳበዛ እኔኑ ለምኑ እንጂ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ይልቅ ምን መሰለህ…ሌላ ስጋት ገብቶናል…
አንድዬ፡— ከስጋት ወጥታችሁ ታውቃላችሁ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አይ ምን መሰለህ… ብቻ አንተን ለምን አስቸግርሀለሁ…
አንድዬ፡— ግዴለም አታስቸግረኝም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አጠቃላይ የዓለም ሁኔታ እየሳሰበን ነው፡፡
አንድዬ፡— (አንድዬ ሳቁን ያፍናል) እውነት! የዓለም ሁኔታ እያሳሰባችሁ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— በጣም እንጂ አንድዬ፣ አንተ እኮ ከቁም ነገር አትቆጥረንም፡፡
አንድዬ፡— እሱን ተወውና…የዓለም ነገር ምኑ ነው ያሳሰባችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደምታየው ሁሉ ቦታ ተኩስ ብቻ ነው፡፡ አሁንማ ማን ከማን ጋር እየተዋጋ እንደሆነ እንኳን ለማወቅ ያስቸግረን ጀምሯል፡፡
አንድዬ፡— እኮ ምኑ ነው እናንተን ያሰጋችሁ!  የደረሰባችሁ፣ ጦር የሰበቀባችሁ አለ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ቢነሳስ!…እኛ ምስኪኖቹ የት እንገባለን! ሌሎቹ እኮ በምድር ስር የሚደበቁበት ሁሉ ገንብተዋል፡፡
አንድዬ፡— እኮ፣ ምን ቤት ናችሁ? የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች ነው ታተራምሳለች የምትሉት ተረት አላችሁ አይደል! ሙሶሊኒን እንደሁ ከመቃብር አላወጣው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አይ አንድዬ የሙሶሎኒን ነገር ካነሳኸውማ ራሳችን ውስጥ ስንት ሙሶሊኒዎች አሉ መሰለህ…
አንድዬ፡— ይሄን ጣት መቀሳሰራችሁን ጀመርከኝ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ጊዜው እንደዛ ነዋ!…
አንድዬ፡— ለዛሬው ይብቃን፣ እኔ የሰለቸኝ ነገር ቁም ነገር የሚመስል ነገር ማውራት ትጀምሩና እኔም አሁንስ ልብ ግዙ ብዬ ላዳምጣችሁ ስጀምር ዘላችሁ እርስ በእርስ መረጋገም ትጀምራላችሁ፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— ነገርኩህ፡ እኔ በእናንተ መሀል አልገባም። እንደፍጥርጥራችሁ፡፡ በል ደሀና ሁን…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ ምስኪን ሀበሻን በቆመበት ጥሎት ተሰወረ፡፡ ምስኪን ሀበሻ አሁንም እዛችው ቦታ ላይ ‘ቆሞ እንዳንጋጠጠ’ ነው፡፡
በቆምንበት ከማንጋጠጥ ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 5319 times