Saturday, 31 October 2015 09:25

‘ጥበብ ስትጠራ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

የጋዜጠኛዋና የአርቲስቷ ቃለምልልስ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
‘ጋዜጠኛዋ’ና ‘አርቲስቷ’ እያወሩ ነው፡፡
‘ጋዜጠኛ’፣— የፊልም ተዋናይነት እንዴት ነው?
‘አርቲስት’፡— ምን ልበልሽ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ እኔ እንደውም ምነው ቀደም ብዬ በገባሁበት ነው ያልኩት፡፡
‘ጋዜጠኛ’፣— አዲሱን ፊልም ስትሠሪ የገጠመሽና የምታስታውሽው ፈተና የለም?
‘አርቲስት’፡— ፈተናማ በጣም አለ፣ ምን መሰለሽ… ካራክተሯ በጣም ነው የፈተነችኝ፡፡ (‘ካራክተሯ’ እኮ ወይ ቡቲክ ወይ ምናምን ውስጥ ዕቃ ሻጭ ነች! “እዛ’ጋ የተሰቀለውን ቀሚስ እስቲ አውርጂው…” እየተባለች ከማውረድ ያለፈ ሚና የላትም፡፡)
‘ጋዜጠኛ’፣— በቀደም የተመረቀውን ፊልም ስትሠሩ በመካከላችሁ የነበረው የሥራ መንፈስ እንዴት ነበር?
‘አርቲስት’፡— በጣም ደስ የሚል ነበር፡፡ በቃ ልክ ለረጅም ዘመን አብረን የኖርን ነው የምንመስለው፡፡ ሰባት ወር ሙሉ ስንቀረጽ አንድ ቀን እንኳን ከፍቶኝ፣ ወይ ከሰው ጋር ክፉ ተነጋግሬ አላውቅም፡ (ኧረ ተይ! ኧረ ተይ! ስንት ጊዜ ነው ‘እነሆ በረከት እንባባል’ የተባልሽው! “ዕድሌ ሆኖ ነው እንጂ ሲጋራ የሚላከው እንኳን ሳይቀር አይጠይቀኝ መሰለሽ!” ምናምን ብለሽ ለጓደኛሽ አቤቱታ ያቀረብሽውስ! “ጠባይሽን ካላሳመርሽ ሁለተኛ ፊልም የሚሠራበት ቦታ ዝር አትያትም!” የተባልሽውስ!)
‘ጋዜጠኛ’፣— የህዝቡስ አቀባባል እንዴት ነው?
‘አርቲስት’፡— የህዝቡንማ ምን ልበልሽ፡፡ በቃ… እንግዲህ አርቲስት ማለት የህዝብ ሀብት                         አይደል…ባለፍኩበት ቦታ ሁሉ በጣም ደስ ደስ የሚል አስተያየት ይሰጡኛል፡፡
‘ጋዜጠኛ’፣— የወከልሻትን ገጸ ባህሪይ በደንብ ተጫውቻታለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ?
‘አርቲስት’፡— ይሄን የሚወስነው ተመልካች ቢሆንም አኔ በጣም ጥሩ ሠርቻታለሁ ነው የምለው፡፡ ጓደኞቼ፣ ቤተሰቦቼ ሁሉ በጣም ነው ደስ ያላቸው፡፡ የሰፈራችን ሰው ሁሉ በጣም ነው ደስ ያለው፡፡  
 ‘ጋዜጠኛ’፣— የሠራሽውን የመጀመሪያ ፊልም ታስታውሻለሽ? (እሷዬዋ እኮ ገና ሁለት ፊልም ላይ ብልጭ ብላ ሦስተኛዋን ለማግኘት ደጅ እየጠናች ነው፡፡ ‘የመጀመሪያው’ ምናምን ሲባል አሥራ አምስተኛዋን ፊልም ሠርታ አሥራ ስድስተኛውን እያጠናች ያለች እንዳያስመስለው ብለን ነው፡፡)
‘አርቲስት’፡— እ… ‘ስሞኝ አመለጠ’ የሚለው ፊልም ላይ ነው፡፡ አርእስቱን ሲነግሩኝ እንዴት ደስ እንዳለኝ አልነግርሽም!
‘ጋዜጠኛ’፣— ‘ስሞኝ አመለጠ’…እሱን ፊልም አይቸዋለሁ፡፡ ደስ የሚል አርእስት ነው፡፡ ሮማንቲክ ኮሜዲ ነው፣ አይደል!
‘አርቲስት’፡— እ…አዎ…
‘ጋዜጠኛ’፣— እሱ ፊልም ላይ ዋናዋን ገጸ ባህሪይ ነው የተጫወትሽው? (‘ጆርናሊስቷ’ ምን ነካት!  ፊልሙን አይቸዋለሁ አላለችም እንዴ!)
‘አርቲስት’፡— አይደለም…ዋናዋ ገጸ ባህሪይ የምታዘወትረው ካፌ ውስጥ አሳላፊ ሆኜ ነው፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ብርጭቆ የሚሰበርብኝ ቦታ አለ፡፡ እንዴት ፈታኝ ፓርት መሰለሽ!
የመሳም ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን አንድ ጊዜ አውርተናት የነበረችውን ስሙኝማ፡፡ እሷዬዋ ለጓደኛዋ… “አንድ የማላውቀው ሰው ካልሳምኩሽ አይለኝ መሰለሽ!” ትላታለች፡፡
“ምንም የማታውቂው ሰው?”
“አይቼው የማላውቀው ሰው፡፡ አይገርምሽም?”
ጓደኝዬዋም በእውነት ትገረምና…  
“እና በቃሪያ ጥፊ አጠናገርሽው!” ስትላት ልጅት ሆዬ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው…
“ልክ ስሞኝ እንዳበቃ፣ አጠናገርኩት፡፡”  
አሪፍ አይደል! ‘ስሞኝ አመለጠ’ ፊልም ላይ ቢጠቀሙበት ቅር አይለኝም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
‘ጋዜጠኛ’፣— አርቲስት ባትሆኚ ኖሮ ምን የምትሆኝ ይመስልሻል?
‘አርቲስት’፡— ምን መሰለሽ… በቃ ታሪክ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ አርቲስት ባልሆን የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪ እሆን ነበር፡፡
‘ጋዜጠኛ’፣— ደስ ይላል፡፡ የሉሲን ታላቅ እህት ታገኚልን ነበራ!
‘አርቲስት’፡— ሉሲ… ሉሲ ማናት?
‘ጋዜጠኛ’፣— ሉሲ… አፋር ውስጥ በቁፋሮ የተገኘች የመጀመሪያዋ የሰው ልጅ…
‘አርቲስት’፡— እሷን ነው እንዴ! እኔ ደግሞ ፊልሙ ውስጥ ሉሲ የምትባል ሴት አለች ወይ ብዬ ድንግጥ አልል መሰለሽ!
‘ጋዜጠኛ’፣— እና የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪ ብትሆኚ ኖሮ በቁፋሮ የእሷን ታላቅ እህት ታገኚልን ነበር፡፡ እንደውም ባሏንም ጭምር ታገኚልን ነበር፣ አይደል!
‘አርቲስት’፡— ጥርጥሩስ… (‘ጋዜጠኛ’ እና ‘አርቲስት’ ይሳሳቃሉ)
‘ጋዜጠኛ’፣— ታዲያ እንዴት ወደ አርቲስትነቱ ገባሽ?
‘አርቲስት’፡— ጥበብ ጠራችኝ፡፡ ምን አለፋሽ ምግብና መጠጥ እስኪያስጠላኝ ድረስ የጥበብ ፍቅር ትንፋሸ አሳጣኝ፡፡ ባይገርምሽ ቤተሰቦቼ ሁሉ የታመምኩ መስሏቸው፡ ሆስፒታል ካልወሰድናት፣ የለም ጠበል ነው የሚሻለው እያሉ ሲጨቃጨቁ ነበር፡
‘ጋዜጠኛ’፣— አንቺ ታዲያ ጥበብ እንደጠራችሽ አትነግሪያቸውም?
‘አርቲስት’፡— ባይገርምሽ እንደውም ‘ጥበብ ጠርታኝ ነው’ ስላቸው ነው…‘ይቺ ልጅ ባሰባት’ ብለው የእናቴም የአባቴም ነፍስ አባቶች እቤት ድረስ የመጡት፡፡
‘ጋዜጠኛ’፣— እንዴት ነው ትዳር ምናምን…
‘አርቲስት’፡— (ፊቷ ይቀላል፡ በሆዷም “ባገባ ባላገባ ምን ይኮነስራታል!” ምናምን ትላለች፡፡) አ…አዎ መንገድ ላይ ነኝ፡፡ ግን መጀመሪያ በፊልሙ ውስጥ ትንሽ መግፋት እፈልጋለሁ፡፡
‘ጋዜጠኛ’፣— የማንን ፊልም ማየት ደስ ይልሻል?
‘አርቲስት’፡— እ…አንጀሊና ጆሊ….ደግሞ እ… (ሌላ ስም ከየት ይምጣ!)  በቃ አንጀሊና ጆሊ ደግሞ ሌሎቹ ደስ ይሉኛል፡፡
‘ጋዜጠኛ’፣— ከውጪ ፊልምስ የምታደንቂው?
‘አርቲስት’፡— (ጉድ ፈላ)  ይሄ ማነው…ይሄ ተደባዳቢው ማነው…
‘ጋዜጠኛ’፣— ሽዋዚንገር…(ኧረ ስሙ በትክክል ይጠራ!)
‘አርቲስት’፡— አዎ ሸዋዚንገር…  የእሱን ፊልም አይተሽልኛል፡፡ አቤት ታሪኮቹ ልብሽን እኮ ቀጥ ነው የሚያደርጉት፡፡ እኔማ አንዴ ማልቀስ ከጀመርኩ አላቆምም፡፡
‘ጋዜጠኛ’፣— የሀገራችን ፊልም እያደገ ነው ትያለሽ?
‘ጋዜጠኛ’፣— በጣም እንጂ፣ በጣም ነው ያደገው! እኔ እንደውም በሦስት ወይም በአራት ዓመት ውስጥ ከሆሊዉድ እኩል የምንሆን ይመስለኛል፡፡
‘ጋዜጠኛ’፣— (አድማጮቻችን እስካሁን ስናወራ የነበርነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘች የመጣችውን ወጣት አርቲስት ትርንጎ በዛብህን ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ትርንጎን በዛብህን ጓደኞቿ የሚጠሯት ቴሪ ቢ ብለው ነው፡፡ እንግዲህ ገና በወጣትነቷ በስኬት ጎዳና ላይ ያለችውን ይቺን ጥበብ የጠራቻትን ወጣት በርቺ ልንላት ይገባል፡፡)ስሙኝማ…በተለይ ከአርቲስቶችና ከስፖርተኞች ጋር የሚደረጉ ቃለ መጠይቆች ከመብዛታቸው የተነሳ አገሪቱ ውስጥ ሌላ ሰው የሌለ ሊመስል ምንም አልቀረው፡ እንደዛም ሆኖ ቃለ መጠይቆቹ… አለ አይደል…ትንሽ ብስለት ቢጨመርባቸው አሪፍ ነበር፡፡ አንዳንዴ ጠያቂዎቹም የሚጠይቁትን፣ ተጠያቂዎቹም የሚመልሱትን የሚያውቁ አይመስልም፡፡ መልሶቹ ከጥያቄዎች የሚወጡ ሳይሆን መልሶቹ ከተጻፉ በኋላ ጥያቄዎች የሚወጡ ነው የሚመስለው፡፡በተለይ ጠያቂዎች የቤት ሥራችሁን ሥሩማ! ጥያቄ አለን…ጥበብ ስትጠራ ምን አይነት ስሜት ነው የሚሰማው? ልክ ነዋ…ምናልባት ‘ጥበብ ጮሃ እየጠራችን’ እያለ ያላወቅን ልንኖር እንችላለና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 6454 times