Saturday, 31 October 2015 08:45

ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት የኢኮኖሚ ዕድገት ይቀንሳል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘንድሮና ቢያንስ በ7 በመቶ ያድጋል ተብሏል

     አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ፤ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የ2015 የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስና ባለፉት ስድስት አመታት ከተመዘገቡት የአካባቢው
የኢኮኖሚ ዕድገቶች ዝቅተኛው እንደሚሆን መተንበዩን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ተቋሙ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው የአካባቢው የግማሽ አመት የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ እንዳለው፣ አምና 5 በመቶ የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት ዘንድሮ ወደ 3.75 በመቶ ዝቅ እንደሚል የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ መቀነስ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከልም የነዳጅና የሸቀጦች ዋጋ መቀነስ እንዲሁም በቻይና ኢኮኖሚ ላይ የታየው መቀዛቀዝ ይገኙበታል፡፡ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት የዘንድሮ የኢኮኖሚ ዕድገት ከአገር አገር የተለያየ እንደሚሆን የጠቆመው ተቋሙ፤ ኮትዲቯር፣ ኢትዮጵያና ታንዛኒያን የመሳሰሉ አገራት ዘንድሮና በቀጣዩ አመት የ7 በመቶ እና ከዚያ በላይ ዕድገት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ብሏል፡፡የነዳጅ ዋጋ ከ2014 አጋማሽ ጀምሮ ከግማሽ በላይ መቀነሱ፣ ናይጀሪያ እና አንጎላን የመሳሰሉ የነዳጅ ላኪ አገራትን በተለየ ሁኔታ ተጎጂ አድርጓል ያለው ተቋሙ፤ ዛምቢያ፣ ጋና እና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ የሚኒኔራል ላኪ አገራትም በሸቀጦች ዋጋ ቅናሽ ክፉኛ እንደተጎዱ ገልጧል፡፡ከቅርብ አመታት ወዲህ በአለማችን ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አካባቢዎች ተርታ መሰለፍ የቻለው ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት መንግስታት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ቅናሹ የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለመቋቋም የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉም አይ ኤም ኤፍ አሳስቧል፡፡

Read 1312 times