Saturday, 31 October 2015 08:44

ኢራን ከ1ሺህ በላይ ሰዎችን በስቅላት ለመግደል አቅዳለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

       የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ጸሃፊ አህመድ ሻሂድ ሰሞኑን ባወጡት ሪፖርት፣ የኢራን መንግስት በዚህ አመት ብቻ ከ1ሺህ በላይ ሰዎችን በስቅላት ለመግደል አቅዷል ማለታቸውን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የኢራን መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች በስቅላት የሚገድላቸው ሰዎች ቁጥር ባለፈው አመት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ያሉት ሻሂድ፣ የአገሪቱ መንግስት ካለፈው ጥር ወር አንስቶ 700 ያህል ሰዎችን በስቅላት መግደሉን ተናግረዋል፡፡ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ አለማቀፍ ህጎችን በመጣስ፣ ሁለት ወጣት ጥፋተኞችን በስቅላት የገደለው የኢራን መንግስት፤ በሌሎች  ወጣቶች ላይም ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ሻሂድ፣ ስቅላት የተፈረደባቸው አብዛኞቹ ወጣቶች በሰው ላይ ያደረሱት ጉዳት የለም፤ አደንዛዥ ዕጽ በመጠቀም ስለተወነጀሉ ብቻ ነው ቅጣቱ የተጣለባቸው ብለዋል፡፡የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች፤ ኢራን አለማቀፍ ህጎችን በመጣስ የራሷንና የውጭ አገራትን
ጋዜጠኞች ታንገላታለች በሚል በተደጋጋሚ ሲተቹ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ሻሂድም
ብዙ ጋዜጠኞች አመለካከታቸውን በማንጸባረቃቸውና ዘገባ በመስራታቸው ብቻ በአገሪቱ መንግስት
የከፋ ቅጣት እየተጣለባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በማህበራዊ ድረገጾች፤ ዜናዎችንና የተለያዩ ጽሁፎቻቸውን በማሰራጨታቸው ብቻ የሞት ቅጣት የተጣለባቸው ጋዜጠኞችም እንዳሉ ሻሂድ ገልጸዋል፡፡ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄም፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ከ30 በላይ ጋዜጠኞች
በኢራን እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ ማስታወቁን ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡

Read 1529 times