Saturday, 31 October 2015 08:41

ኔፓል ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዚዳንት መረጠች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ለኔፓል ሴቶች መብቶች መከበር ለረጅም አመታት በጽናት መታገላቸው የሚነገርላቸው የኔፓል ዩኒፋይድ ማርክሲስት ሌኒኒስት ኮሙኒስት ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር  ቢደሃያ ዴቪ ባንዳሪ፤ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ባለፈው ረቡዕ በኔፓል ፓርላማ በተከናወነው የድምጽ አሰጣጥ ውጤት መሰረት፤ የኔፓል ኮሙኒስት ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት ዴቪ ባንዳሪ 327 ድምጽ በማግኘት በፕሬዚዳንትነት ሲመረጡ፤ ተፎካካሪያቸው 214 ድምጽ ማግኘታቸውን ዘገባው ገልጿል፡፡
ዴቪ ባንዳሪ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡም ሆኖ፣ በአገሪቱ ህግ መሰረት የመሪነቱን ሚና የሚጫወተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ ሴትዮዋ እንግዳ ከመቀበል ያለፈ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉበት ስልጣን እንደማይኖራቸው ዘገባው አስረድቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ካድጋ ፕራሳድ ኦሊ፤ በዚህ ወር መጀመሪያ የተቋቋመውን የአገሪቱ ጥምር መንግስት እንዲመሩ መመረጣቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው ወር የጸደቀው የኔፓል ህገ መንግስት አዲስ ፕሬዚዳንት መመረጥ እንዳለበት በደነገገው መሰረት፣ ረቡዕ ዕለት በተካሄደው ምርጫ የ54 አመቷ ቢደሃያ ዴቪ ባንዳሪ መመረጣቸውን ገልጿል፡፡
አዲሱ የኔፓል ህገ መንግስት ከፓርላማ አባላት አንድ ሶስተኛ ያህሉ ሴቶች መሆን እንዳለባቸው እንዲሁም ፕሬዚዳንት ወይም ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የሚመረጡት የፓርላማ አባል፣ ሴት መሆን እንዳለባቸው የሚያስገድድ አንቀጽ እንዳካተተም ዘገባው አስታውሷል

Read 1288 times