Print this page
Saturday, 24 October 2015 10:03

መንግሥትን ስንጠራው አቤት ይላል፤ወይስ እንደለመደው ጭጭ!?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(19 votes)

በ25 ዓመት ውስጥ የአገር ውስጥ ቪኦኤ መፍጠር አልቻልንም----
በጣም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (ምናልባትም ፓርላማውን ለብቻው የተቆጣጠረው አውራው ፓርቲ፤ አዲስ መንግስት ከመሰረተ በኋላ ሳይሆን አይቀርም!) ለወትሮ ያልተለመዱ ደፈር ደፈር ያሉ መግለጫዎችና መረጃዎች መሰማት ጀምረዋል (ከተሳሳትኩ ግለ ሂስ አደርጋለሁ!) እኒህ መግለጫዎችና መረጃዎች ደግሞ ከምዕራባውያን መንግስታት ወይም ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት አሊያም “ፅንፈኛ ወይም ለዘብተኛ” በሚል በቅርቡ ከተፈረጁት የግል ፕሬሶች የወጡ እንዳይመስላችሁ፡፡ (እነሱማ ማን ሰጥቷቸው?!)
ባይገርማችሁ የመረጃዎቹ ምንጭ ራሱ መንግስት… ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡ (የማይታመን ክስተት ቢሆንም እውነት ነው!) በነገራችን ላይ መንግስት በተለምዶ “የህዝብ መገናኛ ብዙሃን” እየተባሉ የሚጠሩትን፣ እነ ኢቢሲን … አዲስ ዘመንን … ሄራልድን … ወዘተ… በልሳንነት በመፈረጅ “አዝማሪ ሚዲያ አያስፈልገንም” ማለቱን የሰሙ አንዳንድ ወገኖች፤“የት አገር ነው ያለነው?” ሲሉ ግራ በመጋባት መጠየቃቸውን ሰምቻለሁ፡፡(አይፈረድባቸውም እኮ! ያልተለመደ ነዋ!) የሆኖ ሆኖ ግን ---- ያለነው እዛችው የድሮዋ ጦቢያ ውስጥ ነው፡፡ ይልቅስ ጥያቄው እንደ ዘመኑ አራዶች፤ “በሰላም ነው?” የሚል ቢሆን ይመረጣል፡፡ (ኢህአዴግን እኮ ነው!) የእኔ ጥያቄ ደግሞ ኢህአዴግ አሁን በጀመረው መስመር ጸንቶ ይቀጥላል ወይስ መሃል ላይ ‹‹የጥንቱ ትዝ አለኝ›› በማቀንቀን ወደ ድሮው እጥፍ ይላል?... ዋናው ነገር ይሄ ይመስለኛል! እንግዲህ ራሱ መንግስት፣ ራሱ ኢህአዴግ ----- ደጋግሞ ሲናገር (መናገር ብቻ ሳይሆን ሲምል ሲገዘት) እንደሰማነው ከሆነ፣ እጥፍ ወይም ሸርተት ካለ አደጋው ከባድ ነው፡፡ የራሱን ህልውና ዋጋ ያስከፍለዋል (ምን ለማለት ፈልጌ ነው---አውራው ፓርቲ አካባቢ ለውጦች አይቻለሁ!) በእርግጥ ማንም በቀድሞው ጥርጣሬው መቀጠል መብቱ ነው! (ጠርጥር አለ አበሻ!)
እስቲ ደፈር ያሉ መረጃዎች ከመሰሉኝ ውስጥ አንዱን ላጋራችሁ፡፡ ባለፈው ረቡዕ ለንባብ የበቃውን የአማርኛ ሪፖርተር ጋዜጣን አይታችሁልኛል? የመክፈቻ ዜናውን ስታነቡት በቃ ፤አዲስ የጸረ ሙስና ዘመቻ የተጀመረ እኮ ነው የሚመስለው፡፡ እናላችሁ ---- “ፍትህን በብሄር ግንኙነት የሚሸጡና ለወሲብ ድርድር የሚያቀርቡ ሙያተኞች እንዳሉ ተነገረ” ይላል፡፡ (የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዘንድሮ “ወንድ” ወጣው----ባዮች እንደሚበዙ አልጠራጠርም!) ጋዜጣው ይቀጥልና፤ “ከፖሊስና ከማረሚያ ቤት በበለጠ ፍርድ ቤት ለሙስና የተጋለጠ መሆኑ ተጠቆመ” በማለት፣ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማንን ጠቅሶ በስፋት ዘግቧል፡፡
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል---እኔ ‹‹ነፍስ ካወቅሁኝ››፣ የሙስና ችግር በዚህን ያህል ግልጽነትና ድፍረት ሲነገር ሰምቼ አላውቅም፡፡ (ደሞ እኮ የጥናት ውጤት ነው!)  ባለፈው ሳምንት ደግሞ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፤መንግስት “አዝማሪ ሚዲያ አያስፈልገንም” ማለቱን ለመጀመሪያ ጊዜ በግላጭ ሰማሁላችሁ፡፡ (ይሄኔ እኮ #እቺ ሰው ተሸወደች;! የሚሉ ከኢህአዴግም ከተቃራኒው ጎራም ተደርድረው ያዩኝ ይሆናል!)
ለማንኛውም እኛ ወጋችንን እንቀጥል፡፡ በነገራችን ላይ ---- ኢህአዴግ ጨርሶ ከማይታማባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ በራሱ ላይ ርህራሄ የለሽ ሂስ ከማድረግ ወደ ኋላ አለማለቱ ነው፡፡ በፓርቲና በድርጅት ብቻም ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ በኢህአዴግ አባላትና ሹማምንት ዘንድም መደበኛ የሂስ ድግስ እንዳለ ይታወቃል - ጸጉረ ልውጥ የማይጋበዝበት፡፡ በተለይ ደግሞ ሂሱን ያደረገው አገራዊ ምርጫ በአስተማማኝ ውጤት ባሸነፈ (በ2 ዲጂት ወይም ከዚያ በላይ ማለት ነው!) ማግስት ከሆነ ኢህአዴግ በራሱ ላይ ሲጨክን አይጣል ነው፡፡ “ከንቱ ነኝ፣የማልረባ፣ደግሜ መመረጥ የማይገባኝ፣የህዝብ አደራ የምበላ፣ለዚህ ጨዋ ህዝብ የማልመጥን!; ------ ማለት ብቻ እኮ ነው የሚቀረው፡፡ የትችት ውርጅብኝ በራሱ ላይ ያወርዳል፡፡ (ያኔ ደግሞ እኛ ብለነው ብለነው በርዶልናል!)
ይሄ ደግሞ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከጥንትም ፓርቲው የሚታወቅበት መለያው ነው፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (መሬት ይቅለላቸውና!) የህውኃት ክፍፍል ሰሞን (የ“እንፍሽፍሹ” ጊዜ ነው የሚባለው!) ድርጅቱ “በስብሷል፤ከአናቱ ታሟል” ----.ወዘተ ኧረ ምን ያልተባለው አለ?! ብቻ ኢህአዴግና የመሰረቱት ግንባሮቹ----ሂስና ትችት የሚችል ትከሻ ነው ያላቸው፡፡ (የኒዮሊበራሎች ሲሆን ግን ያንገሸግሻቸዋል!)
እናላችሁ … ኢህአዴግ በራሱ ላይ የሰላ ሂስ ማድረግ በርግጥም የከረመበት ባህሉ ነው ቢባል ሃሰት አይደለም፡፡ ኢህአዴግን የሚተቹ ቀኝ አክራሪዎች ግን #ምን ዋጋ አለው?; ሲሉ፣ ኢህአዴግ በራሱ ላይ የሚያደርገውን ሂስ ያጥላሉታል፡፡ እንዴት ሲባሉ? #ወንጀሉንም ይሁን ኃጢያቱን በፓርቲ ተደራጅቶ በጋራ የመሸከም ባህል በማጎልበቱ፣ በግለሰብ ሹማምንቶቹ ላይ የከረረና የመረረ እርምጃ አይወስድም … ቢበዛ አማካሪ ያደርጋቸዋል እንጂ” … ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ኢህአዴግ በራሱ ላይ የመረረ ሂስ ከማድረግ የማይመለሰውን ያህል በግለሰብ ደረጃ አባላቱን ለህዝብ አሳልፎ ከመስጠት (ከማሳጣት) የመጠበቅ ወይም የመከላከል ልማድ እንዳለውም ነው ተቺዎቹ የሚያስረዱት፡፡ (ተማምለዋል እንዴ?) ለዚህም ነው ከዓመት ዓመት በመልካም አስተዳደር ትርጉም ያለው ለውጥ ወይም መሻሻል የማይታየው ሲሉ ይደመድማሉ፤ የአውራው ፓርቲ ተቺዎች፡፡ ይህንን ትችት በተመለከተ ራሱ ኢህአዴግ ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን? (መቼም እንደ ድሮው የፀረ-ልማት ሃይሎች መሰረተ- ቢስ አሉባልታ ነው እንደማይል ተስፋ እናደርጋለን!!) በእርግጥ ተስፋችን የመነጨው ነገሩ፤ “መቶ በመቶ” እውነት ይሆናል በሚል ሳይሆን ኢህአዴግ ለተቺዎቹ ያለው አመለካከት እንደተለወጠ በማመን ነው (የቀድሞ አመለካከቱማ አልጠቀመውም!)
እኔ የምለው ግን----በአዲሱ የኢህአዴግ መንግስት፣ አዳዲስ የሚኒስቴር መ/ቤቶችና የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪዎች ለምን እንዲህ በዙ? (ወይስ ዓይኔ ነው?) ሰሞኑን ደግሞ ተጨማሪ አራት አዳዲስ ኮርፖሬሽኖች እንዲቋቋሙ መታዘዙን ሰማሁ! (አገሪቱ እንደ አዲስ ፈርሳ ነው እንዴ የምትገነባው?!) አንዳንድ ጭፍን የኢህአዴግ ደጋፊዎች ወይም ፍሬሽ ካድሬዎች እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ስታነሱ፤“1ሺ የሚኒስቴር መ/ቤት ቢቋቋም አንተ ደግሞ ምንህ ተነካ?” የሚሉት ፈሊጥ አላቸው (“እየመጣሽ ተኚ” ማለት ይሄኔ ነው!) የምናወራው እኮ የጋራ ቤታችን ስለሆነችው ስለ ጦቢያ መስሎኝ! እናም… እነሱን ችላ በሏቸውና የአገራችሁን ጉዳይ እስከ ጥግ ድረስ ጠይቁ፤ ነዝንኑ፤ ተሟገቱ፡፡ (ጠ/ሚኒስትር መለስ ዳያስፖራዎችን ያንበረከኳቸው፤“እናንተ አማራጭ የላችሁም፤ ያላችሁ አንድ አገር ብቻ ነው” በሚል አንጀት የሚበላ ንግግር እንደነበር አይረሳኝም!)
እናላችሁ … የሚኒስቴር መ/ቤቶች ያለቅጥ መብዛት፣ የኮርፖሬሽኖች መበራከት፣የመንግስት ኢኮኖሚው ውስጥ ዘሎ መግባት (የዘበኛነት ሚና ይጫወት አልወጣንም!) የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪዎች መብዛት-----ተገቢ ነው? ትክክለኛ ጥናት ተደርጎበታል? ወይስ ድንገተኛ (ግብታዊ እርምጃ ነው?) ----- ብለን ከመጠየቅ ፈፅሞ ወደ ኋላ ማለት የለብንም፡፡ አያችሁ … ብዙዎቹ የአገራችን ውድቀቶች ወይም ድቀቶች መንስኤያቸው ቀድሞ ካለመጠየቅ (ያለተጠያቂነት እንዳሻው ከመወሰንና ከመተግበር) የመጡ ናቸው፡፡ መንግስትም በሉት ኢህአዴግ አግዙኝ ያሉት እኮ በእነዚህ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ (መሪውማ በእጃቸው ነው!) ሌላው ቢቀር---- ያለ ጥናትና ያለ እቅድ በነሲብ እየገነቡ የማፍረስ አካሄድ በሁለት ሳይሆን በብዙ ዲጂት መቀነስ ይኖርበታል (“ጠዋት ያደናቀፈህ ድንጋይ---” ይባል የለ!) ስለዚህ እንደ ተማሪ ያልገባንን ነገር ሁሉ እንጠይቃለን፡፡ አሁን ለምሳሌ በኢህአዴግ የ25 ዓመታት የሥልጣን ዘመን ውስጥ አንድ የአገር ውስጥ ቪኦኤ እንኳን እንዴት መፍጠር አልቻልንም? (በደርግም ቪኦኤ፤በኢህአዴግም ቪኦኤ?) የሬዲዮ ወይም የጋዜጣ ፈቃድ ጥያቄ አላነሳሁም፡፡ ቆይ ዜጎች ተበደልን ብለው ሲያስቡ ለምንድነው በደላቸውን ለአገራቸው ኢቢሲ ከመንገር ይልቅ ለቪኦኤ መንገር የቀለላቸው? (መልሱን ያገኘ ለጦቢያ ከፊል ችግር መፍትሄ እንዳገኘ ይቁጠረው!) እናላችሁ … ግልፅ ያልሆኑልንን አሰራሮች መንግስትን እስኪሰለቸው ድረስ (ስንጠራው አቤት ይላል ወይስ እንደለመደው ጭጭ?!) መጠየቃችንን እንቀጥላለን፡፡ (ጥያቄ አያስፈርጅም ብለን እኮ ነው!) እናም ---- መጠየቃችንን ምንጊዜም አናቆምም፡፡ ሁሌም መልስ መስጠት ደግሞ የመንግስት ፋንታ ነው፡፡ (የመረጥነው መልስ ሊሰጠን መስሎኝ!?)
በነገራችን ላይ ሚዲያዎች በተለይ የመንግስቶቹ ግምኛ እየተወቀሱ ያሉት በአድርባይነትና ከልሳንነት ባልዘለለ ሚናቸው እንደሆነ ከሰሞኑ የወጡ ጥናቶችና የመንግስት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመልካም አስተዳደርና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የረባ ሥራ አልሰሩም በሚልም ተተችተዋል፡፡ (ህዝባዊ ወገንተኝነት በአንድ ጀንበር ይፈጠራል እንዴ?!)
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ የተሰጣቸው ጣቢያዎችም ቢሆኑ ሙዚቃና ስፖርት ላይ በማተኮር ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ቦታ አልሰጡም በሚል ነቀፋ ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ (አንዳንዶቹ፤ “ኢህአዴግ ለምን ቀድሞ አልነገረንም?” ብለዋል!) ኢህአዴግ ደግሞ ይሄ ከመንግስት የሚነገራቸው ወይም የሚቸራቸው ሳይሆን “ህገ መንግስታዊ መብታቸው” እንደሆነ ማወቅ አለባቸው … ባይ ነው፡፡ (ለነገሩ አሁንም እኮ ጊዜው አልፈረደም!)
 በእርግጥ የኢህአዴግን የአመለካከት ለውጥ አሁንም በጥርጣሬ የሚመለከቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ (አንደበቱን አላመኑትም!) የሆኖ ሆኖ ግን “አዝማሪ ሚዲያ አያስፈልገንም” ብሏል፤በአደባባይ! (የሚፈልግበት ቀን ይመጣ ይሆን እንዴ?) እኔ የምለው --- በአገራቸው ጉዳይ በፍርሃትም ይሁን በአድርባይነት ዝምታን የመረጡ ምሁራንስ? ተሳትፎአቸው አይፈለግም እንዴ? (ሁሉንም አባል አድርጓቸዋል እንዳትሉኝና እንዳልስቅ!?) እሱንም ቢሆን እንጠይቅና ትክክለኛ መልሱን ከራሱ ከመንግስት አንደበት እናገኘዋለን፡፡ እናም መንግሥትን ስንጠራው --- አቤት ይለናል፤ወይስ እንደለመደው ጭጭ!? (ሳንጣላው ጭጭ?!)

Read 4423 times