Saturday, 24 October 2015 09:51

አቶ አንዳርጋቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሉም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

በሽብርተኝነት ለተከሰሱ ግለሰቦች በምስክርነት እንዲቀርቡ የተፈለጉትን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ፍ/ቤት እንዲያቀርብ የታዘዘው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት፣ አቶ አንዳርጋቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሌሉ ትናንት በደብዳቤው በሰጠው ምላሽ አስታውቋል፡፡
በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከተካተቱ የሽብር ተከሳሾች መካከል አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ናሁን ቤዛ፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁንና አቶ አንሙት የኔዋስ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት ከሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ትገናኙ ነበር በሚል ለቀረበላቸው ክስ ግለሰቡ ቀርበው ምስክርነት እንዲሰጡላቸው መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን ተፈላጊው አቶ አንዳርጋቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሉም የሚል ምላሽ በመስጠቱ፣ ከ4ኛ ተከሳሽ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን በስተቀር ቀሪዎቹ ከዚህ በላይ መጉላላት እንደማይፈልጉ በመጥቀስ በቀጣዩ ሂደት ላይ ብይን እንዲሰጣቸው ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
4ኛ ተከሳሽ አቶ ምንዳዬ በበኩላቸው፤ “ከአንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተህ መመሪያ ተቀብለሃል ስለተባልኩ አቶ አንዳርጋቸው መጥቶ መመስከር አለበት” በማለት አሁንም አቶ አንዳርጋቸው በምስክርነት እንዲቆሙለት ጠይቋል፡፡
ፍ/ቤቱም አቶ ምንዳዬ ያቀረቡትን አቤቱታ መነሻ በማድረግ አቶ አንዳርጋቸው ይገኙበታል ለተባለው ተቋም ትዕዛዝ ለመስጠት ለጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

Read 10151 times