Saturday, 17 October 2015 09:38

4ቱ የዞን 9 ጦማርያን በነፃ ተሰናበቱ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(9 votes)

ጦማሪ በፈቃዱ ኃይሉ፤ የሽብር ክሱ ወደ ወንጀል ዞሮለታል

  የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ በትላንትናው ዕለት ጦማርያን ናትናኤል ፈለቀ፣ አቤል ዋበላ፣ አጥናፉ ብርሃኔና ሶልያና ሽመልስን በነፃ አሰናበተ፡፡ ጦማሪ በፈቃዱ ሐይሉ፤ ከሽብር ክሱ ነፃ የተደረገ ቢሆንም፤ በምርመራ ወቅት ለፖሊስ በሰጠው ቃል፣ ጽሑፎቹ የማነሣሣት ፀባይ እንዳላቸው አምኗል በመባሉ ክሱ ወደ ወንጀል ክስ እንዲዞር ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡በፈቃዱ የዋስትና ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ዋስትና ይሰጠው ወይም አይሰጠው የሚለውን ለመወሰን ለጥቅምት አሥር ቀጥሮታል፡፡
ክሷ በሌለችበት ሲታይ የነበረው 1ኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ በሌለችበት በነፃ ተሰናብታለች፡፡ ጦማርያኑ በነፃ የተሰናበቱት፣ “የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች የቀረበውን ክስ በሚገባ አላስረዱም” በሚል ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ሲሆን አራቱም መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ በይኗል፡፡
ከአንድ ዓመት ከአምስት ወራት በፊት በድንገት ተይዘው ከታሰሩት 10 ጋዜጠኞችና ጦማርያን ውስጥ አምስቱ ሐምሌ 1 እና 2፣ 2007 ዓ.ም በድንገት መፈታታቸው ይታወሳል፡፡ ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ የተከሰሱት፤ የፀረ ሽብር አዋጁን በመተላለፍ፤ የህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ደህንነት ለከፍተኛ አደጋ በማጋለጥ፤ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በማሰርና በማነሳሳት ሙከራ እንዲሁም፣ ከግንቦት 7 ጋር ተንቀሳቅሳችኋል፤ ሥልጠናም ወስዳችኋል በሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡   

Read 5123 times