Saturday, 17 October 2015 09:37

“የኢትዮጵያ ግድብ፣ የመስኖ እርሻና ፋብሪካ፣ ለኬንያ አደጋ ነው” ሂዩማን ራይትስ ዎች

Written by 
Rate this item
(23 votes)

በድህነትና በመስኖ እርሻ እጦት ሳቢያ፣ ከ8 ሚ. በላይ ኢትዮጵያዊያን ለረሃብ በተጋለጡበት አመት!

   በመስኖ እርሻ፣ በፋብሪካ፣ በኤሌክትሪክ እጦት... በድህነት ላይ የምትገኝ አገር ላይ፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች “መስኖና ፋብሪካ በዛ” የሚል አለማቀፍ ዘመቻ ሐሙስ እለት ጀምሯል።
ተቋሙ ያሰራጨው፣ ባለ 103 ገፅ ሪፖርት፣ በፓሪስ ለሚካሄደው ‘የአካባቢ ጥበቃ’ ጉባኤ ታስቦ የተዘጋጀ, የዘመቻ፣ ሰነድ እንደሆነ ተጠቅሷል። “አለማቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ”!
የዘመቻው ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ፣ ኢትዮጵያን መወንጀል ነው - ‘በኬንያ ለሚገኘው ቱርካና ሐይቅ ተቆርቋሪ ነኝ’ በማለት። የኢትዮጵያ ግድብ፣ መስኖ እና ፋብሪካ፣... የቱርካና ሐይቅን ይጎዳሉ በማለት ውግዘቱን ይዘረዝራል።
እስካሁን የሐይቁ መጠን እንዳልቀነሰ ግን፣ በሪፖርቱ ውስጥ አልተገለፀም።
በኬንያ የተካሄደው የግድብ ግንባታና የመስኖ እርሻም፣ አንድም ጊዜ በሪፖርቱ አልተነሳም። ታዲያ ለምን፣ የኢትዮጵያ ግድብ፣ ፋብሪካና መስኖ ላይ፣ አለማቀፍ ዘመቻ ይካሄዳል? ለዚያውም፣ የፋብሪካና የመስኖ እጥረት ባለበት አገር ላይ ነው፣ የውግዘት ዘመቻ የተከፈተው።
የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ... ትርጉም
“የአካባቢ ጥበቃ”... ምን ማለት እንደሆነ እስካሁን ያልተገነዘቡ ሰዎች፣ ትርጉሙን... ሂዩማን ራይትስ ዎች ካዘጋጀው የዘመቻ ሰነድ፣ በግላጭ መረዳት ይችላሉ። “የአካባቢ ጥበቃ” ማለት፣... ችግኝ መትከልና የአካባቢን ንፅህና መጠበቅ... ማለት አይደለም።
የመስኖ እርሻንና ኢንዱስትሪን መቃወም ማለት ነው - የአካባቢ ጥበቃ ማለት። ነባር የአካባቢ ገፅታ፣ የሰው እጅ ሳያርፍበት ‘ተጠብቆ’ እንዲቀጥል፤ ነባሩ ኋላቀር አኗኗር ሳይለወጥና ሳይሻሻል መቀጠል አለበት። በተለይ ግድብና የመስኖ እርሻ፣ ኢንዱስትሪና የፋብሪካ ምርት... ዋና ጠላቶች ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ ዋናው ‘የአካባቢ’ ጠላት፣ ‘ሰው እና የሰው ስራ’ ናቸው።
እንግዲህ፣ ለሰዎች መብት እከራከራለሁ የሚለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አሁን “የአካባቢ ጥበቃ” ፊታውራሪ በመሆን ነው - አለማቀፍ የዘመቻ ሰነድ ያሰራጨው።
ሰነዱ፣ በገፅ 12፣ እንዲህ ይላል።    
ኢትዮጵያ፣ ባለፉት አመታት፣ ትላልቅ የግድብ ግንባታዎችን፣ እንዲሁም ለስኳርና ለጥጥ ምርት፣ የመስኖ እርሻዎችን ስታዘጋጅ ቆይታለች። እነዚህ ፕሮጀክቶች፣ ወደ ቱርካና ሐይቅ የሚደርሰውን ውሃ እጅጉን ይቀንሱታል። የመስኖ እርሻዎቹ፣ የወንዙን 50 በመቶ ያህል ውሃ ሊቀንስ ይችላል።...
ለዚህ የሪፖርቱ አባባል፣ አንድ ጥናት በማስረጃነት ተጠቅሷል - አንድ ጥናት!
ለዚያውም፣ ይሄው ጥናት ራሱ፣ የኢትዮጵያ የመስኖ ፕሮጀክቶች፣ ወደፊት የወንዙን 26% ያህል ለእርሻ ሊያውል ይችላል ነው የሚለው። የሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ይህንን አድበስብሶ ያልፋል። ይህም ብቻ አይደለም። ከኦሞ ወንዝ ውሃ ውስጥ፣ ሰላሳ በመቶ ያህሉ፣ ወደ ግድብ ሳይገባ በቀጥታ ወደ ቱርካና ሐይቅ እንደሚገባ ሳይገለፅ ታልፏል።
ለነገሩ፣ ወደ ጊቤ ግድብ ከሚገባው ውሃ ውስጥም፣ በአብዛኛው ለመስኖ ሊውል አይችልም። ምክንያቱም፣ መፍሰስ አለበት - ኤሌክትሪክ ለማመንጨት። ከፈሰሰ ደግሞ፣ መድረሻው ቱርካና ሐይቅ ነው። ይህም እውነታ፣ በሂዩማን ራይትስ ዎች ሳይጠቀስ ታልፏል።
ደግሞስ፣ ኢትዮጵያ ከኦሞ ወንዝ፣ 50 በመቶ ያህሉ ለመስኖ ብትጠቀም ችግሩ ምንድነው? እንዴት ይወገዛል?
ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን፣ ከማውገዝም አልፎ፣ ለአለማቀፍ ዘመቻ ተነስቷል - ሌሎችም እንዲያወግዙ።  
ለምሳሌ፣ “የኬንያ መንግስት፣ የኢትዮጵያ የግድብ ግንባታን በይፋ መቃወም ትቷል” ሲል ወቅሷል - ተቋሙ። (ገፅ 64)
የቱርካና አካባቢ አስተዳደርም፣ በአብዛኛው በዝምታ የሚመለከትና የመስኖ ልማት እቅድ ውስጥ ስለ ሀይቁ ምንም አይናገርም።
ለጊቤ3 ግድብ ግንባታ፣ ብድር እንዳይገኝ በየአቅጣጫው በተካሄደ ዘመቻ ሳቢያ፣ ቀደም ሲል ቃል ገብተው የነበሩት የአፍሪካ ልማት ባንክና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ብድር ለመከልከል መወሰናቸውን ታስታውሱ ይሆናል። ጭራሽ፣ ኬንያንና ኢትዮጵያን የሚያገናኝ የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት፣ የአለም ባንክ ብድር መስጠቱንም ተቃውሟል - የሂዩማን ራይትስ ዎች ሰነድ።
በዚህ መሃል...    
በቱርካና አካባቢ፣ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ክምችት፣ እንዲሁም የኬንያን የውሃ ፍላጎት ለ70 ዓመታት ሊያሟላ የሚችል የከርሰ ምድር ባህር እንደተገኘ ሪፖርቱ ይጠቅሳል። በዚህ የነዳጅና የውሃ ክምችት ላይ፣ ማንም ኢትዮጵያዊ የይገባኛል ጥያቄ ያቀርባል ተብሎ አይጠበቅም። የቱንም ያህል በነዳጅና በውሃ እጥረት ብንቸገር፣ ኬንያ ውስጥ የሚመነጭ ውሃና ነዳጅ ላይ፣ ጥያቄ እናነሳለን? ኬንያዊያን ይህንን አይጠብቁም። ሙሉ ለሙሉ ራሳቸው ቢጠቀሙበት፣ ውንጀላ አይሰነዘርባቸውም።
ታዲያ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመነጭ ውሃ ላይ፣ ቢያንስ ቢያንስ ግማሽ ያህሉን ለመጠቀም አስባችኋል የሚል ውንጀላ ኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘረው ለምንድነው?   
የሐይቁ መጠንና ጥልቀት አልቀነሰም!
የሐይቁ ጥልቀት፣ በ1970 ዓ.ም ከነበረበት ደረጃ፣  በ6 ሜትር ቀንሷል... የሚል መረጃ ልታዩ ትችላላችሁ። ጥልቀቱ፣ በየጊዜው ከፍና ዝቅ እንደሚል ግን፣ ሳይጠቅሱ ያልፉታል። ከ1930ዓ.ም እስከ 1965 ዓ.ም  ከነበረው ጥልቀት ጋር ሲነፃፀር፣ አሁን ያለው የሃይቁ ጥልቀት ይበልጣል(World Lakes Database)።
እንዲያውም፣ ጊቤ1 ግድብ ስራ ከመጀመሩ በፊት ከነበረው ጥልቀትም፣ አሁን ያለው ጥልቀት ይበልጣል። እነዚህ መረጃዎች፣ በሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ውስጥ፣ ሳይጠቀሱ ተዘለዋል።
ይህም ብቻ አይደለም።
ወደ ሐይቁ የሚገባው ውሃ፣ በአብዛኛው (90%) ያህል፣ ከኢትዮጵያ... ማለትም ከኦሞ ወንዝ የሚመጣ ነው ይላል - የሂራዎ ሪፖርት። ይህን ልብ በሉ።
የዩኤንዲፒ ጥናት ደግሞ፣ ቀደም ሲል፣ የኦሞ ወንዝ ድርሻ 80% እንደነበር ይጠቅሳል። ድሮ ድሮ፣ ወደ ሐይቁ የሚገባው ውሃ፣ 80% ከኦሞ ወንዝ፣ 20% ደግሞ እዚያው ኬንያ ከሚገኙ ወንዞች (በተለይም ከቱርክዌል ወንዝ) የሚመጣ ነበር።
ታዲያ፣ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?
 የዛሬ 25 ዓመት፣ ኬንያ ውስጥ ግድብ ተገንብቷል - በቱርክዌል ወንዝ ላይ። ለምን? ኤሌክትሪክ ለማመንጨትና ለመስኖ። በዚህም ምክንያት፣ ከኬንያ ወንዞች ወደ ሐይቁ የሚገባው የውሃ መጠን ቀንሷል።
ይሄ እውነታ፣ በሂራዎ የ103 ገፅ ሪፖርት ውስጥ አንዴም አልተጠቀሰም። ኬንያ ውስጥ ግድብና መስኖ ሲገነባ፣ ምንም ጥያቄ አይነሳበትም። አይወገዝም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግድብና መስኖ ከተገነባ ግን፣ ‘ትልቅ የሰብአዊ መብት ረገጣ’ የሚሆነው በምን ምክንያት ነው?
ኢትዮጵያዊያን ወራሪዎች ናቸው?
በኢትዮ ኬንያ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ከብት አርቢዎችን በሚመለከት ጥናት የሚያካሂዱ ሰዎች፣ በየጊዜው ግጭቶችና የከብት ዝርፊያዎች እንደሚፈፀሙ ይገልፃሉ። በጎሳ ተቧድኖ ግጭትና ዝርፊያ መፈፀም፣ የኋላቀርነት ምልክት መሆኑ አያጠራጥርም። መቅረትም አለበት።
የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ግን፣ ከሌሎች ሪፖርቶች ይለያል። የጅምላ ውንጀላ ላይ ያተኮረ ነው። በቃ... ኬንያ ውስጥ፣ በጎሳ ተቧድኖ ፣ግጭት የሚቆሰቁስና ዝርፊያ የሚፈፅም አንድም ሰው የለም። ሁሌም ተጠቂዎች ናቸው። ሁሌም በጎሳ ተቧድነው ወረራና ዝርፊያ የሚፈፅሙት፣ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ናቸው - በኬንያዊያን ላይ።አንድ የሰብአዊ መብት ተቋም፣ እንዲህ አይነት፣ የጅምላ ውንጀላዎችን በጭፍን ሲያሰራጭ በጣም ያሳዝናል። ለነገሩ፣ ሰብአዊ መብትን ትቶ፣ “የአካባቢ ጥበቃ”ን ማንገብ የጀመረ ተቋም፣ ውሎ አድሮ ወደ ጭፍንነት መግባቱ እንዴት ይቀርለታል? “የባህል ጥበቃ ተቆርቋሪ” በሚል ሽፋን፣ “በጎሳ የተቧደነ ጥንታዊ የድህነት አኗኗር” ለዘላለም እንዲቀጥል ዘመቻ ማካሄዱም አይገርምም።
እንዴት?
“ሁሉም አካባቢ፣ የሰው እጅ ሳያርፍበት፣ የቀድሞ ገፅታው ‘ተጠብቆ’፣ ለዘላለም መቀጠል አለበት”... የሚል የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ፣ ማንኛውንም ግንባታ፣ በመስኖ እርሻም ይሁን በኢንዱስትሪ መስክ፣ ማንኛውንም የኢኮኖሚ እድገት መቃወሙ የማይቀር ነው። የሂራዎ ሪፖርት፣ ከዳር እስከ ዳር፣ በዚህ የጥፋት ዘመቻ የተቃኘ ነው።
እስቲ አስቡት። ከድህነት መላቀቅና ወደ ብልፅግና መራመድ፣... የተቃውሞ ዘመቻ ሊካሄድበት ቀርቶ፣ ከነጭራሹ ጥያቄ ውስጥ መግባት የሌለበት ጉዳይ መሆን ነበረበት። ትልቁ ችግራችን፣ ከድህነት አለመላቀቃችን አይደለም እንዴ? የመስኖ እርሻ እና የፋብሪካ ስራ አለመስፋፋቱ አይደለም እንዴ? በዘመናዊ እርሻና በኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ ኢንቨስትመንት በፍጥነት አለማደጉ አይደለም የቸገረን?
አዎ፤ በኦሞ ወንዝ የሚገነቡ የጊቤ ግድቦች፣ በተለይ ደግሞ፣ የስኳር ፋብሪካዎችና የመስኖ እርሻዎች... በመንግስት ስር ከሚሆኑ ይልቅ፣ በግል ኢንቨስትመንት ቢከናወኑ ኖሮ፣ የብክነትና የመጓተት ኪሳራዎችን ለመቀነስ፣ እንዲሁም ይበልጥ ውጤታማና ጠቃሚ ለመሆን በተቻለ ነበር። ነገር ግን፣ ሂራዎ፣ የግል ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ይቃወማል - በጅምላ ‘የመሬት ወረራ’ በማለት ያወግዛል።
ሂራዎ፣ “የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪና የመስኖ እርሻ እድገት፣ ለቱርካና ሐይቅ አደጋ ነው” በማለት አለማቀፍ ዘመቻውን የጀመረው ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ፣ መራራነቱ ብዙም ላይሰማን ይችል ይሆናል።
 ዛሬ፣ በዝናብ እጥረት ምክንያት ከ8 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የምግብ ተመፅዋች በሆኑበት፣ ከወትሮው የከፋ አመት ላይ፣ ለዚያውም በሚቀጥሉት ወራት፣ እስከ መጪው ክረምት የተረጂዎቹ ቁጥር 15 ሚሊዮን እንዳይደርስ በተሰጋበት አስጨናቂ ዓመት ላይ፣ ግድብንና የመስኖ እርሻን፣ እንዲሁም ኤሌክትሪክንና ኢንዱስትሪን በጭፍን የሚያወግዝ ሪፖርት ማዘጋጀት፣ በጣም መራራ ነው።       

Read 6469 times