Saturday, 17 October 2015 09:24

በቦብ ማርሊ ህይወት ላይ የተመሰረተው ልቦለድ አለማቀፍ ሽልማት አገኘ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በቦብ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ ይተርካል
   በሬጌ ሙዚቃ ንጉሱ በቦብ ማርሊ የህይወት ታሪክ ላይ ተመስርቶ፣ በጃማይካዊው ደራሲ ማርሎን ጄምስ የተጻፈው “ኤ ብሪፍ ሂስትሪ ኦፍ ሰቨን ኪሊንግስ” የተሰኘ የልቦለድ መጽሃፍ “ማን ቡከር ፕራይዝ” የተባለውን አለማቀፍ ሽልማት እንዳገኘ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በ44 አመቱ ጃማይካዊ ደራሲ ማርሎን ጄምስ የተጻፈው መጽሃፉ፤ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ በቦብ ማርሊ ላይ የተቃጣ የግድያ ሙከራን መሰረት አድርጎ እንደተተረከ የጠቆመው ዘገባው፣ በወቅቱ በጃማይካ ስር ሰድዶ የነበረውን የፖለቲካ ሙስና እንደሚዳስስም ገልጧል፡፡
686 ገጾች ያሉት መጽሃፉ፣ ቦብ ማርሊ እ.ኤ.አ በ1976 በአገሪቱ መዲና ኪንግስተን በተዘጋጀ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ ሲል፣ ሙዚቃውን ለመጫወት ባሰበበት ወቅት የተደራጁ ወንጀለኞች በመኖሪያ ቤቱ ላይ ተኩስ እንደከፈቱና ድምጻዊው ለጥቂት ከሞት እንደተረፈ ይተርካል፡፡
ይህን ሽልማት በማግኘት የመጀመሪያው ጃማይካዊ የሆነው ደራሲው፣ ለህትመት ያበቃው ሶስተኛ መጽሃፉ በሆነው በዚህ ስራው 50 ሺህ ፓውንድ እና ዋንጫ እንደተሸለመ የተገለጸ ሲሆን፣ ደራሲው በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የፈጠራ ጽሁፍ መምህር ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

Read 2865 times