Saturday, 17 October 2015 09:23

የአለማችን የሃብት ክፍፍል ልዩነት መስፋቱን ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    - ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአለማችንን ሃብት የተያዘው፣ ከህዝቡ 1 በመቶ በሚሆኑ ባለጠጎች ነው
           - ግማሹ ድሃ የአለም ህዝብ፣ ከአለማችን ሃብት 1 በመቶ ብቻ ይደርሰዋል
  በያዝነው የፈረንጆች አመት 2015 ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአለማችን ሃብት፣ ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ 1 በመቶ ያህል ብቻ በሚሆኑ የተለያዩ አገራት ባለጠጎች እጅ ውስጥ እንደሚገኝና በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኘው ግማሹ የአለማችን ህዝብ ከአጠቃላዩ የአለም ሃብት 1 በመቶውን ብቻ እንደያዘ በጥናት መረጋገጡን ዘ ኢንዲፔንደንት ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡ክሬዲት ሲዩሴ የተባለው ተቋም በ200 የተለያዩ የዓለማችን አገራት ዙሪያ የሰራውንና ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገውን አለማቀፍ የሃብት ስርጭት አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከአለማችን አገራት መካከለኛ ገቢ የሚያገኙ በርካታ ዜጎች ያሏት ቀዳሚዋ አገር ቻይና ሆናለች፡፡ከአለማችን ህዝብ 14 በመቶ የሚሆነው ወይም 664 ሚሊዮን ያህሉ፣ መካከለኛ ገቢ እንደሚያገኝ የጠቆመው ጥናቱ፣ 109 ሚሊዮን ያህል መካከለኛ ገቢ የሚያገኙ ዜጎች ያሏት ቻይና፣ አምና ቀዳሚ የነበረችውንና ዘንድሮ 92 ሚሊዮን መካከለኛ ገቢ የሚያገኙ ዜጎች እንዳሏት የተረጋገጠውን አሜሪካ ቀድማ የመጀመሪያውን ስፍራ መያዟን ገልጧል፡፡
እስካለፈው ግንቦት በነበሩት 12 ወራት በአለማችን የሃብት ክፍፍል ረገድ የሚታየው ክፍተት ክፉኛ መባባሱን የገለጸው የተቋሙ ሪፖርት፣ ከአለማችን ህዝብ 71 በመቶው ከ10 ሺህ ዶላር በታች፣ 21 በመቶው ከ10ሺህ እስከ 100 ሺህ ዶላር፣ 7.4 በመቶው ከ100 ሺህ እስከ  1 ሚሊዮን ዶላር፣ ቀሪው 0.7 በመቶ ህዝብ ደግሞ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሃብት አለው ብሏል፡፡
የአለማችን አጠቃላይ ሃብት አምና ከነበረበት የ12.4 ትሪሊዮን ዶላር ቅናሽ በማሳየት፣ ዘንድሮ 250 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል ያለው ሪፖርቱ፣ ከዚህ ሃብት 16 በመቶውን የያዘችው ቻይና ስትሆን፣ አሜሪካ በ12 በመቶ፣ እንግሊዝ ደግሞ 4 በመቶውን ይዘዋል ብሏል፡፡

Read 1507 times